
ባሕርዳር፡ ጥር 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የጨለመውን እንዲያበራ፣ የፈረሰውን እንዲሠራ፣ ያለቀሰውን እንባውን እንዲያብስ፣ አስፈሪውን ዙፋን እንዲመልስ፣ በኀያልነት እንዲነግሥ፣ ለጭንቅ ቀን የተመረጠ፣ በኀይሉ ከሁሉም የበለጠ፣ አሥፈሪ ግርማ የተላበሰ፣ በመከራ ጊዜ የደረሰ፣ በግርማ የነገሠ። ፈጣሪ በማሕፀኗ ከአንድ ልጅ በሥተቀር ሌላ ያልሰጣት፣ አንዱን ግን የመረጠላት፣ የባረከላት፣ እንደ አንድ ተፈጥሮ እንደ ሺህ ያደረገላት፣ ለጭንቁ ቀን ፈዋሽ ልጅ ከማሕፀኗ እንደሚወጣ አስቀድሞ ያዘጋጃት አንዲት ሴት ነበረች። ጠቢብ ፣ ጀግና ፣ ደፋር ልጅ እንድትወልድ የተዘጋጀች፣ ከባላባቱ ወገን የሆነች፣ ነብሷን በመልካሙ መንገድ የመራች፣ ስጋዋን የቀጣች። ከማሕፀኗ በሚገኘው መልካም ልጅ ስሟ እስከ ዘላለም እንዲጠራ አስቀድማ የተባረከች፣ የተመረጠች፣ ማሕፀኗ ከአንድ በላይ ሌላ ፍሬ ለማፍራት አልታደለም፣ ከአንድ ውጭ ሌላ ለመፀነስ አልተመረጠም፣ አንድ ጊዜ ትፀንሳለች ፣ አንድ ጊዜ ትወልዳለች ፣ አንድ ጊዜ ታሳድጋለች፣ ከአንድ በላይ አትፀንስም። ከአንድ ጊዜ ወዲያ ልጅ አታገኝም፣ አንድ ጊዜ ከፀነሰች ፣ አንድ ጊዜ ከወለደች፣ አንድያ ልጇንም ካሳደገች በኋላ ግን በአንደኛው ልጇ አብዝታ ትኮራለች፣ ለምን ካሉ አንደ አንድ ተፈጥሮ እንደ ሺህ ይኖራልና።
እናቱ ታናሽም ታላቅም ትወልድለት ዘንድ ምኞቷ ነበር። እንደ ጋሻ የሚመክትበት፣ የሚመካበት፣ የሚኮራበት ወንድም፣ የሚያጌጥባት፣ ዓለም የሚያይባት፣ ሲርበው የሚጎርስባት፣ ሲጠማው የሚጠጣባት፣ ሲደክመው የሚያርፍባት ፣ ጭንቅ ሲለው መላ የሚፈልግባት እህት ይኖረው ዘንድ ፈጣሪዋን ተማፅናለች። ዳሩ ከአንድ ውጭ አልተፈቀደላትም። እርሷ ድጋሜ ልጅ ትወልድ ዘንድ አልቻለችም ። እርሱ ግን በጀግንነቱ ክሷታል፣ በምግባሩ ሀዘኗን አስረስቷል። አንድ ሆኖ ተወልዶ ተባርኳልና፣ አንድ ሆኖ ተወልዶ የሺህዎች ግምት ሆኗልና፣ ይህች ሴት በነበረችበት በዚያ ዘመን አሥፈሪው ዙፋን ተዳክሞ፣ ኃያላን ነን የሚሉት ተበራክተው፣ በየፊናቸው ነፍጥ እያነሱ፣ ሠራዊት እያዘመቱ የሚጋጩት በዝተው ሀገሬው ተጨንቆ ነበር። ያ ግርማው የሚያስደነግጠው ዙፋን አቅም አጥቷል፣ እምብኝ የሚለውን መሣፍንት ሁሉ ተው የሚል ጠፍቷል፣ የሀገሬው መከራ ተበራክቷል፣ ለመጣው ሁሉ መገበር ተሰላችቷል። ዙፋን በሚከበርበት ፣ ንጉሥ በሚወደድበት፣ ሠንደቅ ከሕይወት በላይ በሚታይበት ሀገር የዙፋኑ ግርማ ማጣት፣ የንጉሡ አለመፈራት ጭንቅ ሆኗል። ጠንካራ ዙፋን ሲታጣ በዳር በድንበሩ እያንዣበበ ድንበር ላፍርስ፣ እርስት ልወረስ፣ ቀዬ ላርክስ፣ ታሪክ ልደምስስ የሚለው ብዙ ነውና።
ዙፋኑ ተዳክሞ በነበረበት በዚያ ወቅት ታዲያ ድንበር ለማፍረስ፣ ወሰን ለመጣስ፣ ቀዬ ለማርከስ፣ እርስት ለመውረስ፣ ታሪክ ለመደምሰስ የሚከጅሉት በዝተው ነበር። ባሕር እየሰነጠቁ፣ የብስ እያቆራረጡ መቅረብ ጀምረዋል ። አጥሩ የተዳከመ ሲመስላቸው፣ ጀግና እንደ ሌለ ሲሰማቸው ሠራዊታቸውን ያስጠጋሉ፣ ሳንጃቸውን ይስላሉ፣ ጦራቸውን ያሾላሉ፣ ጠመንጃቸውን ይወለውላሉ፣ ፈረሶቻቸውን ያዘገጃጃሉ፣ ጀበርናቸውን ያስተካክላሉ። እነሆ በዚያ ዘመን መሳፍንቱ አሻፈረኝ ብለዋል፣ የውጭ ጠላቶችም ኢትዮጵያን ሊውጡ ተቻኩለዋል፣ ቋምጠዋል፣ በውስጥ በደሉ የበዛበት፣ ጭንቁ የጠናበት ፣ በውጭ ጠላት ያንዣበበበት፣ አቤት የሚልበት ንጉሥ ያጣው፣ በሠንደቁ ሥር የሚሰበሰብ ጀግና ንጉሥ የናፈቀው የሀገሬው ሕዝብ ደግ ንጉሥ ይሰጠው ዘንድ ፈጣሪውን እየለመነ ነበር። ለወትሮው ታቦቱን ከመንበሩ ንጉሡን ከወንበሩ አኑርልን እያለ የሚማፀነው ደገኛ ሕዝብ ከወንበሩ የሚቀመጥ ጠንካራ ንጉሥ ሲያጣ፣ ፈጣሪ የተወው መስሎታልና ተጨንቋል፣ ተጠቧል። ሀዘኑም በዝቷል። እረኞች በዋሽንታቸው ዜማ እየታጀቡ፣ በጋራ በሽንተረሩ እየተመላለሱ፣ ጅራፋቸውን እያጮሁ፣ ዜማ እያዜሙ፣ ዓለም አጫዋቾች በማሲንቋቸው እየተቀኙ ስለሚነሳው ንጉሥ ትንቢት ይናገራሉ። የሚነሳው ንጉሥ ንግግሩ የሚያምር፣ ለማንም የማይበገር ፣ ፈጣሪውን የሚያከብር፣ ለሠንደቋና ለሀገሩ ክብር የሚኖር ጀግና፣ ደፋር፣ ኩሩ ቆራጥ እንደሚሆን ይተነብያሉ። በዚያ ዘመን የእረኛ እና የዓለም አጫዋቾች ትንቢት ጠብ አይልም እየተባለ ይታመናልና የሚነሳው ንጉሥ እየተጠበቀ ነው። መሣፍንቱና መኳንንቱ፣ የጦር አበጋዞቻቸው ወዮላችሁ በጦር የማይመለስ፣ ሁሉንም አሸንፎ የሚነግሥ ንጉሥ ይነሳል እየተባለ እየተነገረ ነው። ከእኛ በላይ ኀያል የለም የሚሉት ሰግተዋል። በሚነሳው ንጉሥ ተጨንቀዋል። አንዳንዶቹ ስጋታቸውን ሳይነግሩ በውስጣቸው ይጨነቃሉ፣ ገሚሶቹ የእረኞችን እና የዓለም አጫዋቾችን ትንቢት ያናንቃሉ፣ ሌሎቹ የሚሆነውን ለመቀበል በዝምታ ይጠብቃሉ። የእረኞችን ትንቢት የሚሰማው የሀገሬው ሰው የጭንቁ ዘመን ያልቅ ዘንድ ቀርቧል እያለ ተስፋ አድርጓል።
በቀን በማታ መልካም ንጉሥ ይሰጣቸው ዘንድ አብዝተው መለመናቸውንም አላቋረጡም። ፈጣሪም የደገኞችን ልመና ሰማ። አስፈሪውን ዙፋን ወደ ክብሩ የሚመልስ፣ የተጎዳውን ሕዝብ የሚክስ፣ የመከፋፈልን ዘመን የሚደመስስ ደገኛ ሰው በምድሯ ሊያነግሥ ወደደ። ያቺ አስቀድማ የተመረጠችውን እናት ማሕፀኗን ባረከ፣ ፍሬዋንም አሳመረ። ቋረኛው ደጅ አዝማች ኃይሉ፣ ከእሜቴ አትጠገብ ጋር ተገናኙ፣ ከንፁህ አልጋ ላይ በንፅሕና ተዋወቁ ፣ ደግ ፍሬ ተሰጣቸው፣ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ በአልጋ ላይ የተዋወቁት ፍሬ አልነበረውም። ፍሬው አንድ ቀን ተሰጣቸው። እሜቴ አትጠገብ ፀነሰች፣ ደጅ አዝማች ኃይሉ ተደሰቱ። እሜቴ አትጠገብም ማሕፀኗ ፍሬ አፍርቷልና ፈጣሪዋን አመሰገነች። አስቀድሞ የተነገረው ዘመን ቀረበ። ቀናት ተቆጠሩ፣ ወራት ተተካኩ፣ እሜቴ አትጠገብ የመውለጃ ጊዜዋ እየደረሰ ነው። በዚያ ጊዜ የልደት በዓል ተከብሮ የጥምቀት በዓልን ለማክበር ሽር ጉድ እየተባለ ነው። እረኞች፣ ወይዛዝርቱና ጎበዛዝቱ በጥምቀት ቀን ደምቀው ለመዋል መዋዋብ ጀምረዋል። አንደኛው ከሌላኛው ልቆ ለመገኘት ፉክክሩ አይሏል። ሴቶች ሹርባ ይሠራሉ፣ እንሶስላ ይሞቃሉ፣ አልቦና ድሪያቸውን ያሳምራሉ፣ ወንዶች ደግሞ ጎፈሬያቸውን ይነቅሳሉ፣ አለባበሳቸውን ያሳምራሉ። ብቻ በበዓሉ ቀን ደምቆ ለመታየት እና ትኩረት ለመሳብ ሽርጉዱ በዝቷል። ፅንሷ የገፋው እመቤት ደግሞ ወልዳ ስትተኛ የምትታረስበት መሰናዶ እንዲኖራት በዝግጅት ተጠምዳለች። የመውለጃዋ ነገር ከወረሃ ጥር እንደማይዘል ልቧ ነግሯታል፣ የሆዷ ልጅም ገፍቶ እንደፈለጋት እንዳትሆን አድርጓታል። ቀኑ ደረሰ። ለበዓል ዝግጅት በተጧጧፈበት ወቅት እሜቴ አትጠገብ ምጥ ተይዛ ተኛች። ጎረቤት ተጠራ፣ ሰው ተሰበሰበ፣ ምጡ እየገፋ መጣ። እሜቴ አትጠገብ ተጨነቀች፣ አይዞሽ የሚለው በዙሪያዋ ከቧል። ያስጨነቀው ምጥ መጣ። እሜቴ አትጠገብ ወንድ ልጅ ተገላገለች ። እልልታው ቀለጠ፣ ቤቱ በደስታ ተዋጠ፣ የእሜቴ አትጠገብ ልብ በደስታ ተመላ፣ ወንድ ተወልዷልና፣ ደጋግማችሁ እልል በሉ ተባለ። እልል ተባለ፣ ደስታ ሆነ። እሜቴ አትጠገብ ልጇን በስስት ተመለከተች፣ የተበደለው ሀገር ይካስ ዘንድ ካሳ ስትል ስም አወጣችለት። በስም የወጣለት፣ አስቀድሞ ትንቢት የተነገረለት የተበደለውን የሚክስ፣ የታጣውን የሚመልስ ልጅ ነውና።
እሜቴ አትጠገብ አንድያ ልጇን በስስት አሳደገችው። መልካሙንም መንገድ አሳየችው፣ ፍቅርን አስተማረችው ። ቀስ በቀስም አደገ። እሜቴ አትጠገብም ልጇ ፊደል እንዲቆጥር ፣ ምስጢራትን እንዲመረምር ለመምህር ሰጠችው። አዕምሮው ፊደል ለመቁጠር ፣ምስጢራትን ለመርመር አስቀድሞ የተዘጋጀ ነበርና አስተማሪዎቹ እስኪደነቁ ድረስ ለትምህርት የተመረጠ ሆነ። እናቱ ደስታዋ ወደር እያጣ ሄደ። ፊደል ቆጠረ፣ ዳዊት ደገመ። እናቱ ራሱን እየዳበሰች፣ ግንባሩን እየሳመች፣ በእቅፏ ውስጥ ፍቅርን እየሰጠች፣ ጥንካሬን ሹክ አለችው፣ ተሰናክሎ እንዳይወድቅ፣ ራዕይ እንዲሰንቅ መንገዱን አሳየችው። ካሳ ከመምህሩ እግር ሥር ቁጭ ብሎ ትምህርቱን እየቀፀለ ሌላ ነገር ተመለከተ። መንገድ የጠፋበት፣ ችግር የበዛበት የሀገሬው ሰው አሻጋሪ እንደሚፈልግ አስተዋለ። ራዕይ ሠንቆ፣ ወገቡን አጥብቆ፣ የሰንዴ ዛላ መሳይ ሹርባ ተሠርቶ በረሃ ወረደ። ቋረኛው የተበላሸውን መንገድ ሊቃና ቆርጦ ተነሳ። ስሙ ናኘ። ካሳ ካሳ ይባል ጀመር። ጎበዛዝቱ በጀግንነቱ እና በራዕዩ እየተሳቡ ተከተሉት፣ የካሳ ክንድ ጠነከረ፣ ስሙ ከዳር ዳር እያስተጋባ መጣ።
በእፍኙ የሚሞላ ወንድ ጠፋ፣ የገጠመው ሁሉ ይጠፋ ጀመር። ማነው ወንዱ ሲሉ የነበሩት መሳፍንቱና መካንንቱ ስጋት ገባቸው፣ በትንቢት ተነስቷልና። መላ ኢትዮጵያን ጠቅልሎ የሚገዛው ንጉሥ እርሱ ነው እየተባለ ነውና ትንቢቱ እንዲፈፀም የሚሻው ናፈቀ፣ እንዳይፈፀም የሚሻው ተጨነቀ። በጦር አይቻልምና የሚደፍረው ጠፋ። የራስ አሊ እናት እቴጌ መነን ተጨነቁ። ክንዱ እየበረታ የሄደውን ካሳን በጦር ወግቶ ይይዝላቸው ዘንድ በጦር መሪነቱ የሚታወቀውን ዳጃች ወንድይራድን ላኩት። ወንድይራድ ፎክሮ ተነሳ። ካሳን ያሸነፈ እንደሆነ ተዋበችን ሊያገባ ቃል ተገባለት። ልእልቷ ተዋበች ያያትን ሁሉ የምታፈዝ፣ ጦር የምታማዝዝ ውብ ነበረችና ወንድይራድ ተዋበችን ታገኛለህ ሲባል ደስታው ወደር አጣ። ካሳን አሸንፎ ጀግና ሊባል፣ ከተዋበች ጋርም ሊቀማጠል ስለ ቸኮለ ካሳ ወዳለበት ገሰገሰ። ድል ግን ሳይቀናው ቀረ። የካሳ ክንድ በቀላሉ አይቀመስም ነበርና። ይባስ ብሎ ለወንድይራድ ትሰጥ ዘንድ የተመረጠችው ተዋበች የካሳ ዝና፣ ጀግንነት እና ራዕይ ሳባት። እቴጌዋ የካሳ ግስጋሴ እንዲገታ፣ በእነርሱ ላይም ክንዱን እንዳያነሳ ካሳን ሊዛመዱት ፈለጉ። ተዋበችንም ዳሩለት። ካሳ ራዕዩን የሚያሳካበት፣ ትንቢቱን የሚፈፅምበት ውብ ሚስት አገባ። ብልህ ሴት ለባሏ ዘውድ ናት እንደተባለ ካሳ ዘውዱን አስቀድሞ አገኘ። ራዕዩን ወድዳውአለችና ሹርባውን እየዳበሰች፣ ሰፊ ደረቱን እያሻሸች ካሳ ተነስ ታጠቅ አለችው።
ካሳ ፈጣሪውን አመሰገነ። በተዋበችም ፈፅሞ ደስ ተሰኘ። እስከሞት ድረስ የማያወልቀውን ትጥቁን ታጠቀ። “እንግዳ አክባሪ ነው በማተቡ ኗሪ
ጀግና ደፋር እንጂ አያበቅልም ፈሪ” የተባለለት ሀገር የጀግኖች ጀግና በቀለበት። የቋራ በረሃዎች በካሳ ግርማ ተሞሉ። ዘራፊዎችና ወንበዴዎች ደግሞ ከካሳ በትር ለማምለጥ የት እንግባ አሉ። ካሳ ገሰገሰ። የእረኞች ትንቢት ቀረበ። ካሳን የሚያቆም መስፍን ጠፋ። ሁሉም እየገጠሙት ተሸነፉ፣ ከእግሩ ሥር ወደቁ። ካሳ ግስጋሴውን ጨመረ። የመሳፍንቱ ዘመን በክንደ ብርቱው ሰው ሊፈፀም ተቃረበ። መሳፍንቱን ቀጣቸው፣ መኳንንቱን አደብ አስያዛቸው። ሰብሳቢ ጠንካራ ንጉሥ አጥቶ የነበረው የሀገሬው ሰው ፈጣሪ ልመናችን ሰምቷል እያለ ተደሰተ። ግርማ ያጣው ዙፋን ግርማ ያለው ንጉሥ ሊያገኝ ተቃረበ። ሁሉንም አሸንፎ በደረሰጌ ማርያም ንጉሠ ነገሥት ተብሎ በአስፈሪ ግርማ በአስፈሪው ዙፋን ላይ ተቀመጠ። በጳጳሱ እጅም ተቀባ። ስሙም ቴዎድሮስ ተሰኘ። ትንቢተኛው ቴዎድሮስ እየተባለ ተጠራ። ተዋበችም ከአጠገቡ ሆና ዘውድ ደፋች።
ለሀገሩ እንቅልፍ የማያውቀው ቴዎድሮስ ምቾት ሳይፈልግ ሌት ከቀን ለፋ። ደከመ። አቤ ጉበኛ ታላቁን ንጉሥ “ለሀገራቸው ተፈጥረው፣ ለሀገራቸው ኖረው፣ ለሀገራቸው ምቾታቸውንም፣ ሕይወታቸውንም የሠውት ገናናው ኢትዮጵያዊ” ይሉታል። በካሳ ጀግንነት ያልተስማማ የለም። ሁሉም ጀግንነቱን መሥክሮለታል። “ለአፄ ቴዎድሮስ ጀግንነት የማንም ብዕር የማንም አፍ ምስክርነት ከሚሰጠው በላይ እረፍት የሚባል ሳያውቁ በየአቅጣጫው ተንከራተው አንድ ያደረጉት የኢትዮጵያ አፈር ይመሰክራል” ይላሉ አቤ ጉበኛ። የቴዎድሮስን ጀግንነት ጋራውና ሸንተረሩ ሁሉ እንደሚያውቀው ይናገራሉ። አቤ ጉበኛ ዶክተር ሔነሪ እስተርን ዋቢ አድርገው “ካሳ በእነዚያ ጊዜዎች ያሳያቸው ፍርሃት ጨርሶ የሌለበት ጀግንነትና የጦርነት ስልት ወዳጆቹም ጠላቶቹም እንዲያደንቁትና እንዲያጨበጭቡለት አድርገውታል” ብለዋል።
“ቃሉ ቢደጋገም ብትባል አንበሳ
ይህ ያንስሃል ለአንተ ቢከፈልህ ካሳ ” እንዳለች ዘፋኟ ካሳ ከዘመኑ የቀደመ አንበሳ ነበር። አንበሳ እየተባለ ቢጠራ ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም። በፈጣሪው አብዝቶ የሚመካው ካሳ ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ገዝቶ፣ ዘመናዊነትን አስፋፍቶ በዚያ ዘመን በስቃይ ውስጥ የነበረችውን ኢየሩሳሌምንም ነፃ ለማውጣት ራዕይ ነበረው። ራዕዩ እውን እንዲሆን አብዝቶ ደከመ። ቤተ መንግሥት ንቆ በድንኳን ውሎ እያደረ ሀገሩ በረከት ታገኝ ዘንድ ታገለ። የካሳን መንግሥ የሠሙት የውጭ ጠላቶች ስጋት ገባቸው። ሊወሯት የፈለጓት ኢትዮጵያ ኀያል ንጉሥ ነግሶባታልና ደነገጡ። ተንቀጠቀጡ። ቴዎድሮስም በጀግንነት፣ በብርታት ሳይሰለች ለሀገሩ ደከመ። ጠላት የበዛባት ሀገሩ ኢትዮጵያ እልፍ ጀግኖች እንዳሏት የተረዳው ቴዎድሮስ ጀግኖቹን ዘመናዊ መሣሪያ ለማስታጠቅና ዘመኑ ከደረሰበት ስልጣኔ እንዲደርሱ ኢንዱስትሪ አቋቋመ። የታሰበው ይሳካ ዘንድ ቴዎድሮስ ደከመ።
ጠላቶች ግን በዙበት። የመኳንንቱና የመሳፍንቱ ወገን ነን የሚሉ መንገዱ ላይ እየቆሙ አስቸገሩት፣ በየጊዜው ጦርነት እየከፈቱ ጊዜ አሳጡት። አርፎ ለሀገሩ የሚሠራበት ራዕዩን ፈፅሞ እውን የሚያደርግበት ጊዜ አጣ። በየጊዜው ጠላቶቹ ተበራከቱ። የውስጥ ባንዳዎች የውጭ ጠላቶችን እየመሩ አስገቡበት። በተሳሳተው ዘመን የተወለደው ትክክለኛው ሰው አብዝቶ ለፋ። ይባስ ብሎ ደረቱን እያሻሸች፣ ራዕይ የተሸረበበትን ቁንዳላ እየዳበሰች ካሳ ታጠቅ ብላ ያስታጠቀችው፣ ከአጠገቡ ሆና ያበረታችው፣ ብርቱ ክንድ የሆነችው ተዋበች ተለየችው። ሞት ከእርሱ ነጠቀበት። የቴዎድሮስ አንጀት ተላወሰች። አብዝታ አዘነች። መካሪው፣ የራዕዩ ተጋሪ ብልሗ ተዋበችን አጥቷልና አምርሮ አለቀሰ። ጠላቶቹም ተበራከቱ። ካሳ እነ ገብርዬን ይዞ ወደ መቅደላ አምባ አመራ። በዚያም ቆየ። በውስጥ ባንዳ የተመራው ጠላት መጣ። የካሳ ዘመን ፍፃሜ ቀረበ። ጦርነት ተጀመረ።
ካሳ አብዝቶ የሚወደው፣ አብዝቶ የሚያምነው ገብርዬ በጀግንነት አለፈ። የገብርዬን መሞት የሰማው ካሳ የመጨረሻውን እንባ አፈሰሰ። ካሳ ልቡ በሀዘን ተመታ በመቅደላ አምባ ላይ ተመላለሰ። ራዕዩን ሳይፈፅም ሩቅ እንዳሰበ ምድርን ሊሰናበታት እንደሆነ አሰበ። ሺህዎችን እንደ ቆሎ ያሸው የቴዎድሮስ እጅ ለጠላት አትሰጥም አለ። ተዋበች ታጠቅ እንዳለችው የታጠቃት፣ ከወገቡ የማይለያት ሽጉጥ ከወገቡ ነበረችና ዝቅ ብሎ ተመለከታት። ከወገቡ ላይ ሳባት። በአምባው አናት ላይ ወዲያና ወዲህ ተመላለሰ። ካሳ አፈሙዙን አዞረ። ማርና ጮማ በተንቆረቆረበት ጉሮሮ ባሩድ ጨመረበት። የካሳ ዘመን ተፈፀመ። ራዕዩና ዘመን የቀደመው ቃሉ ግን ዛሬም አለ።
ዛሬም ትውልዱን ይቀሰቅሳል። “ጋፋትን ሳስታውስ መድፉ ትዝ ይለኛል መቅደላን ሳስበው ሽጉጥ ይታየኛል እንዲያም እንዲያም ብዬ ቀልቤን ስመልሰው እንደ ቴዲ ያለ አጣሁኝ አንድ ሰው”እንዳለች ዘፈኟ በጭንቅ ቀን የሚደርስ፣ ክብር የሚያላብስ በራዕይ የሚገሰግስ እንደቴዎድሮስ አይነት ሰው እንሻለን። ይህ ታላቅ ሰው የተወለደው ልክ በዛሬዋ ቀን ጥር 6 ነበር። ጀግናው ኀያል ነህና፣ በጭንቅ ቀን ደርሰሃልና እንኳን ተወለድክ። ሥራህ ደንቅ ነውና ስምህ ከፍ ብሎ ይኖራል። በየቦታው ይጠራል። ለዚያም ነው ዘፋኙ
“እንኳንስ በጎንደር በተወለደበት
በድፍን ሀገሩ የእርሱ ስም አለበት” ሲል የተቀኘው። ንጉሥ ሆይ እንኳንም ተወለድክ።
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/