ʺበመሶብ እንጀራ ፍየል በጉ ታርዶ፣ ደስ ይለኛል ጎንደር ያውቃል መስተንግዶ”

167

ባሕርዳር፡ ጥር 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ነገሥታቱ በሚያምረው ቤተ መንግሥት ውስጥ ኖረውበታል፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ በቤተ መንግሥቱ አጸድ ሥር ሰፍረውበታል፣ ጋሻ ጃግሬዎች፣ የእልፍኝ አስከልካዮች፣ የጦር አበጋዞች በዙሪያ ገባው በኩራት ተመላልሰውበታል፣ ዓለም አጫዋቾች በቤተ መንግሥት በሚያምረው ድምጻቻው አዚመውበታል፣ ሊቃውንቱ በአብያተ ክርስቲያናቱ ሰማያዊ ዝማሬን አቅርበውበታል፣ ነገሥታቱና መኳንንቱ፣ መሳፍንቱና ሊቃውንቱ፣ ጦረኛው፣ አርሶ የሚበላው፣ ታናሽ ታላቅ ሳይባል ግብር በጋራ ተበልቶበታል፣ ደስታና ፍስሃ ተደርጎበታል፣ አያሌ ታሪክ ተሠርቶበታል፣ ጥበብ እንደ ዥረት ፈስሶበታል፡፡

በአብያተ ክርስቲያናቷ የእጣን ጭስ፣ በተራራዎቿ ግርማ ሞገስ እየታጀበች፣ በታሪክ እየደመቀች፣ ከታሪክ ላይ ታሪክ እየሠራች የምትኖር፤ ቀሳውስቱ የተቀኙላት፣ ጀግኖች የሚፈልቁባት፣ ነገሥታቱ በኩራት የኖሩባት፣ ዓይኖች ለማየት የሚመኟት፣ ጀሮዎች ለመስማት የሚጓጉላት፣ ባለ ቅኔዎች የተቀኙላት፣ የዜማ ደራሲዎች ያዜሙላት፣ የታሪክ ሰዎች ታሪኳን የጻፉላት ድንቅ ምድር ናት፡፡ የአፍሪካ መናገሻ፣ የጀግንነት፣ የአንድነት፣ የኢትዮጵያዊነት መነሻ ይሏታል፡፡ በተንዘራፈፈው የጃን ተከል ዋርካ የደመቀች፣ በአብያተ ክርስቲያናቱ የተከበበች፣ በአብያተ መንግሥታቱ የተዋበች፣ ምስጢራትን ያቀፈች፣ የታሪክ፣ የጥበብ፣ የጀግንነት፣ የአንድነት ማሕደር የሆነች ድንቅ ሥፍራ፡፡

ጀግኖች ይወለዱባታል፣ በጀግንነት ያድጉባታል፣ በጀግንነት ይጠብቋታል፣ ሊቃውንቱ ሳያቋርጡ ምስጋና ያቀርቡባታል፣ በሥፍራዋ የደረሱት ሁሉ የሀገር ምሰሶ፣ የሀገር አድባር፣ ዋልታና ማገር ይሏታል፣ የነገሥታቱን ምድር፣ የጀግኖችን ሀገር ጎንደርን፡፡ ጎንደር ሲትነሳ ታቦታቱ፣ ጀግንነቱ፣ አንድነቱ፣ ኢትዮጵያዊነቱ፣ እንግዳ ተቀባይነቱ፣ ኩራቱ፣ ደግነቱ፣ ብልህነቱ ሁሉ አብሮ ይነሳል፤ ጎንደር ለጀግንነት፣ ለአንድነት፣ ለደግነት፣ ለእንግዳ ተቀባይነት የተመቸ ነውና፡፡

ቃላቸውን አያብሉም፣ ቃላቸውን ከሚያብሉ ሞትን ይመርጣሉ፣ ለእውነት ሲሉ አንገታቸውን ይሰጣሉ፡፡ አበው እንኳን የጦር አበጋዞች የነገሥታቱ ፈረሶች ታማኞች ናቸው፣ ጌታቸውን ያከብራሉ ይሏቸዋል፡፡ ሕግ ያከብራሉ፣ ትዕዛዛትን ይጠብቃሉ፣ ስለ እውነት ሲሉ ይኖራሉ፣ ለሀገራቸው ክብር፣ ለሠንደቃቸው ፍቅር ነብሳቸውን ይሰጣሉ፣ ደንበር ያጸናሉ፣ ጠላት ይቀጣሉ፣ ወንበዴን አደብ ያስይዛሉ፣ ጎንደር ለጠገበና ሀገርን ለሚከዳ ጥይት፣ ለተጠማ ወተት መስጠት ያውቁበታል፣ ስሞት አፈር ስሆን እያሉ ማጉረስ ፣ የታረዘን ማልበስ ይችሉበታል፡፡

እድል ቀንቶት በቀያቸው የዘለቀ ሁሉ በፍቅራቸው ባሕር ውስጥ ይሰምጣል፣ በጃንተከል ጥላ ሥር ይጠለላል፣ በጀግንነታቸው ይደመማል፣ በመስተንግዷቸው አጀብ ይሰኛል፣ በአብያተ መንግሥታቱ ውበት፣ በጦረኞቹ ጀግንነት፣ በቀሳውስቱ ትህትና ባየው ሁሉ ይደነቃል፣ አካባቢውን ለቆ፣ ከፍቅራቸው ርቆ መሄድን ሲያስብ መንፈሱ ትጨነቃለች፤ ዓይኑ እንባን ታመነጫለች፣ ፍቅራቸው ያስራል፣ ደግነታቸው መመለስን ያስረሳል እና፡፡

የአፍሪካ መናገሻ፣ የአንድነት መነሻ፣ የነገሥታቱ፣ የአብያተ ክርስቲያናቱ፣ የሊቃውንቱ ሀገር ጎንደር ቀን በቀን ትደምቃለች፣ ከፍ ባለ ዝና ትታወቃለች፣ ጀንበር በዘለቀች ቁጥር ትጠራለች፣ ትታወሳለች፣ ፍቅሯ በአሻገር የጠራቸው፣ ዝናዋ የቀሰቀሳቸው፣ ታሪኳ የሳባቸው ሁሉ ሊደመሙባት፣ ታሪክ ሊቀስሙባት፣ በውበቷ ሊያጌጡባት፣ በጥበቧ ሊደምቁባት ወደ ጎንደር ይገሰግሳሉ፣ በዚያውም ይከትማሉ፣ በአዩት ሁሉ ይደመማሉ፣ ይደነቃሉ፡፡

የጎንደር ጎዳናዎች ነጫጭ በለበሱ ምዕመናን ይዋባሉ፣ የካህናቱ ዜማ ከእየአድባራቱ ይሰማል፣ የጽናፅኑ፣ የጽሕናው፣ የከበሮው ድምጽ ያስተጋባል፣ ሁሉም ቀልብን ይሰባል፡፡ ይህች በሁሉም የደመቀች ሥፍራ በወረሃ ጥር፣ የኢየሱስ ክርስቶስን የጥምቀት ቀን ተከትሎ ደግሞ የበለጠ ትደምቃለች፣ ታብባለች፣ እንግዶቿን ትቀበላለች፣ እንግዳ መቀበል፣ እቅፍ ድግፍ አድርጎ ማቀማጠል ታውቅበታለችና እልል እያለች እንግዶቿን ትቀበላለች፣ አቀማጥላ ታሳርፋለች፤ በሰፊው እልፍኝ ጠጅ እየተጣለ፣ ጠላ እየተጠመቀ፣ ጮማ እየተቆረጠ፣ ወይዛዝርቱ እልል እያሉ፣ ጎበዛዝቱ ደግሞ እየሸለሉ እና እያዜሙ በአማረው ቤተመንግሥት እንግዶቻቸውን ይቀበላሉ፣ እልፍኙ የተመቸ ነው፣ ሥፍራው የተደላደለ ነው፡፡ የሄደው ሁሉ በሠፊው እልፍኝ ያርፋል፣ በፍቅራቸው ባሕር ውስጥ ይንሳፈፋል፡፡

ʺአይዝልበት ክንዱ አይነጥፍበት ማዱ፣
እንብላ እንጠጣ ነው ጎንደሬ ልማዱ” እንዳለ ከያኒ ክንዱ የማይዝልበት፣ ማዱ የማይነጥፍበት፣ ደግነት የበዛለት የጎንደር ሰው ለወደደው እንብላ እንጠጣ እያለ ያበላል ያጠጣል፡፡ በልተው የጠገቡ አይመስለውም፣ ድግሱ አያልቅበትም፡፡ እነሆ የጥምቀት በዓል እየደረሰ ነው፣ ጎንደርም እንግዶቿን ለመቀበል ሸብ ረብ እያለች ነው፣ ቄጠማ ጎዝጉዛ እንግዶቿን አሳምራ ለመቀበል በሥራ ተጠምዳለች፡፡ እንግዳ ክቡር ነውና እርሷም ማክበሩን፣ ድግስ ማሳመሩን ታውቅበታለችና፡፡

ʺበማተቡ አዳሪ ሰው አምኖ እማይከዳ፣
ያውቅበታል ጎንደር ሲቀበል እንግዳ” እንደተባለ ሰው አምኖ የማይከዳው፣ እስከ ሕይወት ፍጻሜ የሚታመነው የጎንደር ሰው እንግዳ መቀበሉን ያውቅበታል፡፡ ማጉረስ፣ ማልበሱን ይችሉበታል፣ ወዳጅን በፍቅር፣ ጠላትን በጦር መማረኩን ተክኖበታል፣ ድግስ መደገስ በክብር ማንገስ ከእነርሱ ነው፡፡ በድግሱ መታደም የፈለጉ ሁሉ ወደ ሥፍራው ያቀናሉ፣ በውቧ ሥፍራም የማይረሳ ጊዜ ያሳልፋሉ፡፡

ʺበመሶብ እንጀራ ፍየል በጉ ታርዶ
ደስ ይለኛል ጎንደር ያውቃል መስተንግዶ” መስተንግዶ ያውቃሉ፤ ጎንደር በመሶብ እንጀራ ሞልታ፣ ሁሉንም አዘጋጅታ፣ በቤተ መንግሥቱ ልታስጠልል፣ በጃንተከል ዋርካ ሥር ልታሳርፍ፣ በክብር ልትቀበል፣ በውስጧ የበዙትን ታሪካዊና መንፈሳዊ ሥፍራዎች ልታሳይ ቀኑን እየጠበቀች ነው፤ የጥምቀተ ባሕሩ ትዕይንት፣ የቀሳውስቱ ሕብረ ዝማሬ፣ የወይዛዝርቱ የጥምቀት ጨዋታ፣ የጎበዛዝቱ ደስታና ጭፈራ ውል ይላል፡፡ ጥምቀትን ጎንደር ሳይገኝ ማንስ ይቀራል? ታቦታቱ በክብር ከየአድባራቱ ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕሩ ይወርዳሉ፣ ካሕናቱ ልብን የሚያስደነግጥ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው በጋራ ያዜማሉ፣ ምስጋና ያቀርባሉ፣ ነጫጭ የለበሱ ዲያቆናት ወረብ ይወርባሉ፣ ታቦታቱን ይከበክባሉ፣ ምድርን ያስጨንቃሉ፣ በዝማሬ ክንፍ ይላሉ፣ በጥምቀት ቀን ጎንደር ነጫጭ በለበሱ አማኞች ትሞላለች፣ እልልታ ታበዛለች፣ ታቦታቱ ከየአድባራቱ ሲወጡ ሴቶች እልል ይላሉ፣ ወንዶች በደስታ ይዘላሉ፣ ምስጋና ያቀርባሉ፣ በሀገርኛ ባሕል ይዘፍናሉ፤ ያን ጊዜ ጎንደር ምድራዊ የማይመስል ውበት ይከባታል፣ ከዳር ዳር የሚሰማ ድምጽ ያናውጻታል፣ ነብስን የሚያስደስት የእጣን ጭስ ያውዳታል፡፡ ሁሉም ልዩ ይሆናል፡፡

ባሕረ ጥምቀቱ ተባርኮ ሲከፈት የመጠመቂያ ጊዜው ሲደርስ ደግሞ ሌላ እልልታ፣ ሌላ ምስጋና ይመጣል፣ ሌላ ዝማሬ እጹብ ድንቅ ያሰኛል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ጎንደር የተለየ ድግስ ደግሳለች፣ አንድነት ያረፈበትን፣ ጀግንነት ያለበትን፣ ራዕይ የተጎነጎነበትን፣ ተስፋ የተሸረበበትን፣ ቃል ኪዳን የታሰረበትን የንጉሥ ቴዎድሮስን ቁንዳላ ልታሳይ ተሰናድታለች፡፡ የቁንዳላው ፍቅር የጠራቸው፣ ቃል ኪዳን ለመቀበል ያማራቸው ሁሉ ወደ ሥፍራው ያቀናሉ፡፡

ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ጀግንነት፣ አንድነት፣ ደግነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ውበት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ መልካም እሴትና ሌሎች እልፍ ጥበቦችን እና ምስጢራትን በአንድ ማሕደር ውስጥ ማየት የፈለገ ካለ ዓይኖቹን ወደ ጎንደር ያዙር፣ ጀሮዎቹን ወደ ጎንደር ያዘንብል፣ ወደ ጎንደርም ይራመድ፣ የማይረሳ ትዝታ፣ ወደር የሌለው እርካታ ማግኘት የሚሻ ሁሉ ጉዞውን ሁሉ ወደ ነገሥታቱ ምድር ያድርግ፡፡ በጎንደርም ጥምቀትን ያክብር፡፡

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com

Previous article❝መነሻና መዳረሻችን የሕዝባችን ክብርና ጥቅም ማስከበር ነው!❞ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
Next articleʺጠላት ካንዣበበ ክፉ ቀን ከመጣ ቀስቅሱት በላይን አስተካክሎት ይምጣ”