
ባሕር ዳር፡ ጥር 06 / 2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከዛሬ 203 ዓመት በፊት ጥር 6/1811ዓ.ም ጎንደር-ቋራ ተወለዱ፡፡
. አባታቸው ደጃዝማች ኃይለጊዮርስ በሱዳኖች በ 1813 ዓ.ም ስለተገደሉ፣ እናታቸው አትጠገብ ወደ ጎንደር ከተማ በሁለት ዓመታቸው ይዘዋቸው መጡ፡፡ ወይዘሮ አትጠገብ የጎንደር ከተማ መስራች የአፄ ፋሲለደስ ዘመድ ናቸው፡፡ ወይዘሮ አትጠገብ የጎንደር ባላባት ዘር ናቸው-ጳውሎስ ኞኞ፡፡
. አፄ ቴዎድሮስ በእናታቸው በኩል ምንም ወንድም እህት አልነበራቸውም፡፡ እናታቸው ባለቤታቸው እንደሞተ ወዲያው ቆርበው ስለነበር ከቴዲ ውጭ ልጅ አልወለዱም፡፡ ለዚህም ቴዎድሮስ አንድ ለናቱ ይባላል፡፡
. አፄ ቴወድሮስ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፣በትውልድ ስማቸው ካሳ ኃይሉ፣በውትድርና ስማቸው ደግሞ መይሳው ካሳ ሲባሉ የዙፋን ስማቸው ዳግማዊ ቴዎድሮስ ነው፡፡ ቀዳማዊ ቴዎድሮስ በፍካሬ ኢየሱስ፣ በ15 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ተወዳጅ ንጉሥ ነው፡፡ ይህ ንጉሥ በ 19 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዳግም እንደሚነሳ ትንቢት ተነግሯል፡፡ ይህን ትንቢት በመያዝ ካሳ ኃይሉ ራሱን ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ብሎ የካቲት 11/1847 ሾመ፡፡
…….
ቴዎድሮስ ጣዎስ ድሮስ ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን የአምላክ ስጦታ ማለት ነው፡፡
❖
. አፄ ቴዎድሮስ ሩሲያ እና እንግሊዝ ግብጾች እና ቱርኮችን ከሀገር ለማስወጣት እንዲረዷቸው ደብዳቤ ቢፅፉም ምላሽ አጡ፡፡ እንግሊዝ ከቱርክ ጋር ሩሲያን በክሬሚያ ጦርነት ወጋቻት፡፡አፄ ቴዎድሮስም እልህ ተጋብተው እንግሊዛዊያንን አስረው ሴባስቶፖል መድፍን አሠሩና ስያሜውን ለሩሲያ የጦር ሜዳ ሰጡ – ባህሩ ዘውዴ፡፡
………
አፄ ቴዎድሮስ በ 13 ዓመት የንግሥና ጊዜያቸው የባሪያ ንግድን፣ ጎጠኝነትን ወዘተ አስቀርተዋል፡፡ ዘመናዊ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሙከራ አድርገዋል፡፡ ዘመናዊ ጦር፣ዘመናዊ ምሽግ፣ዘመናዊ ሙዚየም አቋቁመዋል፡፡መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ በብዛት እንዲተረጎም ከማድረግ ባለፈ ሥነ ጽሑፍ፣ፍልስፍና እንዲያድግ ጥረዋል፡፡
የመንገድ ዝርጋታ አስጀምረዋል፡፡ ብሔራዊነትን ሰብከዋል፡፡ የዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ የአንድነት መነሻ ናቸው- ፓውል ሄንዝ፡፡
.ሚያዝያ ወር መግቢያ በዕለተ ዓርብ ፣ ትንሣኤን ሳይገድፉ በስቅለቱ በ 1860 ዓ.ም ራሳቸውን መቅደላ አፋፍ ላይ ለሀገራቸው ተሰው፡፡
….”መቅደላ ከአፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ፣
..የሴቱን አናውቅም፣ወንድ አንድ ሰው ሞተ”
በወቅቱ እንግሊዛዊያን ወደ መቅደላ ሲመጡ 6 ሚሊየን ፓውንድ መድበው፣32 ሺህ ዘመናዊ ወታደር ይዘው እንደመጡ ታሪክ ይዘግባል፡፡
❖በምናብ ተወልዶ በምናብ የሞተ!!!በትንሽ ዘመን ትልቅ የሆነ፣ ከመለያየት አንድነትን የሰበከ የአንድነት ሐዋርያ (ተጓዥ) ንጉሥ
ዳግማዊ ቴዎድሮስ በዚህች ምድር የኖሩ ለ 49 ዓመታት ብቻ ነበር፡፡ዳሩ ቁምነገር በዕድሜ አይሰፈርም፡፡በገነነ ሥራቸው ከዘመናቸው በላይ አስበው፣ ከዕድሜያቸው በላይ ኖሩ!!!
ዛሬም ነገም ክብር ለመቅደላው ሞት ደፋሪ!! ምሥጋና ለጋፋቱ የቴክኖሎጂ ጥመኛ!!!
(በድጋሚ የቀረበ)
ዘጋቢ፡- የሺሐሳብ አበራ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/