
ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2012 ዓ/ም (አብመድ) በአማራ ክልል መንግሥት አስተባባሪነት የተዘጋጄና በቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጉዳይ የሚመክር ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይርሳው በውይይ መክፈቻ ላይ ባሰሙት ንግግር ‹‹በቅማንት ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን አለመረጋጋት ከኮሚቴው ጋር በመሆን ሌላ ዓይነት መልክ እንዲይዝ በተቀናጀ መልኩ እየሠሩ ያሉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት እየሠራ ነው›› ብለዋል፡፡
ጉዳዩን የመገናኛ ብዙኃን ባልተገባ መልኩ የአንድ ወገንን ሐሳብ ብቻ በመያዝ ማቀጣጠላቸው ተገቢ እንዳልሆነና ሊታረሙ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ጥያቄውን ለመመለስ የክልሉ መንግሥት ኃላፊነቱን ተወጥቷል፤ ቀሪ ጥያቁዎችም ካሉ በሠላማዊ መንግድ ለማስናገድ እየሠራ ነው›› ብለዋል አቶ ጌትነት በንግግራቸው፡፡
ለውይይቱ መነሻ ሁለት ጽሑፎች እየቀረቡ ነው፡፡ ‹‹የቅማንት ጥያቄ ከየት ወደዬት፡- እስከ ፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ›› በሚል ርዕስ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ በሆኑት አቶ ቹቹ አለባቸው እና ‹‹የቅማንት ጥያቄና የክልሉ መንግሥት ምላሽ›› የሚል ርዕስ የያዘ ጭብጥ ደግሞ በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሕግ አማካሪ አቶ መርሐጽድቅ መኮንን አማካኝነት እንደሚቀርቡም ታውቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን -ከአዲስ አበባ
ፎቶ፡- በጌትነት ገደፋው