
ባሕር ዳር፡ ጥር 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ቤት ንብረታቸው የተዘረፈባቸው እና የወደመባቸው ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው በመመለሱ ሂደት ዲያስፖራው የሚኖረው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል።
ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ባደረሰው ጉዳት እና ባለፉት 3 እና 4 ዓመታት ባጋጠሙ የተፈጥሮ አደጋዎች በአማራ ክልል ከ11 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለከፋ ጉዳት መዳረጋቸውን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስት ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የዲያስፖራ አቀባበል የሃብት አሰባሰብና ሎጀስቲክስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዘላለም ልጃለም ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነር ዘላለም የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ዜጎችን በመደገፍ ረገድ ሕዝቡ ያደረገው እና እያደረገ ያለው ድጋፍ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በገንዘብ በቁሳቁስ እና በሃሳብ በማገዝ የማይናቅ ሚና ተጫውተዋል፤ ለዚህም ምሥጋና ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን እያደረሰ ያለውን መጠነ ሠፊ ጉዳት ለመቀልበስ በተደረገው የህልውና ዘመቻ ዲያስፖራው በአማራ ክልል ብሎም በኢትዮጵያ የገጠመውን ፈተና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማሳወቅ ረገድ የተወጣዉን የዜግነት ኀላፊነትም አንስተዋል፡፡ ለዚህም ላቅ ያለ ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት ኮሚሽነር ዘላለም፡፡
ለተጎጂዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ በቅድሚያ የደረሰውን ጉዳት መረዳት ተገቢ በመሆኑ በርካታ ዲያስፖራዎች ወደ ሀገራቸው በመምጣት ችግሩን ከምንጩ እየተረዱት መሆናቸውን ኮሚሽነር ዘላለም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የፖለቲካ ልዩነት ሳይበግራቸው ለወገኖቻቸው እያደረጉት ያለውን ሰብዓዊ እርዳታ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ክልሉ ከደረሰበት ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እንዲያገግም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። የደረሱ ጉዳቶችን ለዲያስፖራው ለማስረዳትም በክልል ደረጃ ከመንግሥት፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከዲያስፖራ ወኪሎች የተውጣጣ በክልሉ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡
እስካሁንም ዲያስፖራው በመልሶ ግንባታው ላይ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጉብኝቶች ተካሂደዋል፤ አውደ ርዕዮች ተዘጋጅተዋል፤ ሲምፖዚየሞች እና የችግሩን ጥልቀት ሊያሳዩ የሚችሉ ጥናታዊ ጽሑፎች በቀጣይ ቅዳሜ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
ኮሚሽነር ዘላለም እንደገለጹት ዲያስፖራዎች ችግሩን ተረድተው በዘላቂነት እንዲያግዙ እና የሀገራቸውን ችግር የእኛም ችግር ነው ብለው እንዲረዱ ፕሮጀክቶች ተነድፈዋል፤ ለተግባራዊነታቸውም ሁሉም ርብርብ ያደርጋል፡፡
ኮሚሽነሩ በክልሉ ከ11 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ለከፋ ጉዳት ተዳርጓል፤ የዕለት ደራሽ ምግብም ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪ የማኅበራዊ አገልግሎት ሠጭ ተቋማት መውደም ችግሩን ቢያገዝፈውም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች በሚያደርጉት ድጋፍ ችግሩን ተሻግረን በሰላም የምንኖርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/