የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ በ79 ተፋሰሶች 1ሺህ 500 ሄክታር መሬት ለማልማት መዘጋጀቱን አስታወቀ።

137

ገንዳ ውኃ፡ ጥር 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የ2014 ዓ.ም የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ሥራ ለማስጀመር በገንዳ ውኃ ከተማ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የግብርና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር በርሃማነት እንዳይስፋፋ በደን ጥበቃ ላይ በትኩረት መሠራት እንዳለበት ተገልጿል።

በዞኑ የሚገኙ 79 ተፋሰሶችን መሰረት በማድረግ 1 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱንና ለ514 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወደ ሥራ መገባቱን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ኤፍሬም ወርቁ ተናግረዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በግብርናው ዘርፍ አመርቂ ውጤት ለማምጣት ደኖችን መከለል፣ መጠበቅና ኅብረተሰቡ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው ግንዛቤ መስጠት ተቀዳሚ ተግባር ይሆናልም ብለዋል።

ሕገወጥ የደን ጭፍጨፋ፣ ሰደድ እሳትን ማስቆምና የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመረባረብ በትኩረት እንደሚሠራም አቶ ኤፍሬም አስረድተዋል።

የዞኑ የቆዳ ስፋት 1 ነጥብ 7 ሚሊዬን ሄክታር ሲሆን የአልጣሽን ብሔራዊ ፓርክ ጨምሮ 623 ሺህ 400 ሄክታር መሬት በደን የተሸፈነ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፈንታሁን ሳሀሉ ነግረውናል።

ዞኑ ከፍተኛ የደን ሽፋን ያለበት ቢሆንም አሁን ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ከፍተኛ ውድመትና መመናመን እየታየበት ነው ብለዋል።

በዞኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ከሚሠራባቸው ቦታዎች አንዱ “አረንጓዴ ዘብ” በመባል የሚታወቀው የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ነው። ፓርኩ 266 ሺህ 570 ሄክታር መሬት የቆዳ ስፋት ሲኖረው ሁሉም በደን የተሸፈነ ነው።

በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦችን ከመጠበቅ ባሻገር ለ300 ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩን የፓርኩ የሕግ ማስከበር ቡድን መሪና ተወካይ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ስመኛው ውበቱ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡-ቴዎድሮስ ደሴ-ከገንዳ ውኃ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበሳምንቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የስልክ ውይይት የፖለቲካ ሁነቱ እንደተቀየረ ማሳያ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
Next articleበአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሃይንከን ቢራ አክሲዎን ማኅበር ድጋፍ አደረገ፡፡