ʺየጠላቶችህ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ የክተት ዘመቻ እንደተጠራህ አስብ”

408

ባሕር ዳር፡ ጥር 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ስለ አንድነት አብር፣ በክንድህ ሀገርህን አስከብር፣ ጠላት በበዛበት ምድር መከበሪያው አንድነት፣ አትንኩኝ ባይነት፣ ብልሃት፣ ጀግንነት ነው፡፡ በለቅሶህ ድግስ የሚደግሱ፣ በእንባህ ዘለላ አንጀታቸውን የሚያርሱ፣ ከሰርጋቸው ይልቅ የአንተ ተዝካር የሚያስደስታቸው፣ የአንተ መሞት የሚያኖራቸው፣ በደምህ ጎርፍ ቤታቸውን የሚያሞቁ፣ በአንተ ለቅሶ የሚስቁ፣ በአንተ ሀዘን የሚሳለቁ፣ የአንተ አንገት መድፋት ቀና የሚያደርጋቸው፣ የሚያኮራቸው እልፍ ጠላቶች በዙሪያ ቆመዋል፡፡ በዘመምክበት ንፍቅ ሁሉ በጦር ሊወጉህ፣ በሳንጃ ሊያደሙህ የሚሹ፡፡

የአራት ዓይና ጠቢብ ልጅ አይደለህ? ጠላት ክንዴን አይነካውም የሚለው ጀግና አባት አይደል የወለደህ? ሀገሯን ሲነኩባት አራስ ነብር ከምትሆን እናት ማሕጸን አይደል የተገኘህ? በአራቱም ንፍቅ መክት፣ በአራቱም ንፍቅ ሳትዳከም ተመልከት፣ በአራቱም ንፍቅ እያለምክ ተኩስ፣ በአራቱም ንፍቅ ክብርህ ሳይነካ ጠላትህን አዋርደህ መልስ፣ ለአንተ ሀገር ያስረከቡት በየዘመናቱ የተነሱትን ጠላቶች ቀጥተዋል፣ እሳት ሆነው አቃጥለዋል፣ ውቅያኖስ ሆነው አስጥመዋል፣ አንበሳ ሆነው አድቅቀዋል፡፡ ራሳቸው ተክብረው ሀገርና ሕዝብ አክብረዋል፡፡ ስማቸውን በታሪክ ድርሳን ላይ ደመቅ አድርገው አጽፈዋል፡፡ የክብር ጥሪ ይቀስቅስህ፣ የጠላቶችህ ግፍና ክፋት እንቅልፍ ይንሳህ፡፡

ያልተደፈረ ክብር፣ ያልተደፈረች ሀገር እንዳለህ አትዘንጋ፣ በአንተ ዘመን ሀገር እንዳይደፈር ተጠንቀቅ፣ አንድ ሆነህ ተነስ፣ አንድ ሆነህ ተኩስ፣ አንድ ሆነህ ጠላትህን መልስ፣ በአራቱም ንፍቅ እሳት ይዘው የሚዞሩ ሞልተዋልና፡፡ ከተዘናጋህ፣ ከተዳከምክ ቤትህን አቃጥለው በነዲዱ ለመሞቅ፣ በለቅሶህ ለመሳቅ የሚጠባበቁ አሉና፡፡ አንተም አይሆንም በላቸው፡፡
ʺ ዓባይ ሞልቶ እሳት ይዞረዋል
ሊጠፋ ነው እንጂ ማን ይሻገረዋል ” እንዳለ ጃሎ ባዩ ዓባይን እሳት ይዞ መዞር ለመጥፋት፣ ለማንቀላፋት እንጂ ለመሻገር አይሆንም በላቸው፡፡ እሳት የሞላውን ወንዝ አይሻገረውም፣ የሞለውን ወንዝ አያቃጥለውም፣ አንድ የሆነውን እና የጠነከረውን ሕዝብም ጠላት አይደፈርረውም፣ ክብሩን አይነካውም፡፡ አንበሳ ያለበትን ጫካ ጅብ አይደፍረውም፣ አንበሳ ያለበትን ዱር ቀበሮ አይረማመደውም፣ አንበሳው ከአንቀላፋ፣ ጫካውን ጥሎ ከጠፋ ግን የአንበሶች መኖሪያ የጅቦች፣ የቀበሮዎችና የተኩላዎች መናኸሪያ ይሆናል፡፡

አንተ ደግሞ አንበሳ ነህና በመኖሪያህ ጅብና ተኩላ እንዲዘምትበት አትፍቀድ፡፡ ወላጆችህ በስሜን ዘምተው አሸንፈዋል፣ በምዕራብ ዘምተው ድል አድርገዋል፣ በምሥራቅ ዘምተው ጠላትን ሰብረዋል፣ ምሽግ አፍርሰዋል፣ በደቡብ ዘምተው ግዛት አጽንተዋል፣ ሉዓላዊነትን አስከብረዋል፡፡ ለዘመናት በአራቱም አቅጣጫ ጠብቀዋል፡፡ ለዘመናት ጠላትን አሳፍረዋል፣ የነጻነት፣ የአሸናፊነት፣ የአንድነት ምሳሌና ምልክት ሆነው ኖረዋል፡፡

በክንዱ በሠራው ታሪክ የኮራ፣ በጨለመ ዘመን ሁሉን የሚያዳርስ ብርሃን ያበራ፣ ከዘመናት በፊት ዘመንን የቀደሙ ኪነ ህንጻዎችን የሠራ፣ ለጠገበ ጥይት፣ ለተጠማ ወተት የሚሰጥ፣ ፈትፍቶ ማጉረስ፣ አልሞ መተኮስ፣ የሚገባውን ማንገሥ፣ የማይባውን መውቀስ የሚችል፤ የጠላት ወጀብ የማያናውጠው፣ የጠላት የውሸት ወሬ የማይንጠው፣ በሠንደቁ የሚምል፣ ከጀግኖች ጋራ በጀግንነት ሥፍራ የሚውል፣ ቃሉን የማያብል፣ ሕዝብ የማይበድል፣ ከጀግንነቱ፣ ከአንድነቱ፣ ከብልሃቱ፣ ከኢትዮጵያዊነቱ የማይጎድል ሕዝብ ልጅ ነህ፡፡

በምድርም በሠማይም በአሸናፊነት የምትውለበለበው ሠንደቅ ከተደፈረች፣ ቅድስቷ ምድር ኢትዮጵያ ከተነካች ቁጣው ገንፍሎ፣ በሠንደቋ ግርጌ በኢትዮጵያ አምላክ ምሎ የሚነሳ ሕዝብ ነው የወለደህ፡፡ ምሎ ከተነሳ፣ እንደ አንበሳ ካገሳ የሚያቆመው ጠላት በዘመኑ አልተገኘም፣ ዛሬም አልተገኝም፣ ነገም አይገኝም፡፡ አሸናፊ የወለደህ፣ በአሸናፊነት ያሳደገህ፣ በአሸናፊነት ያኖረህ፣ የአሸናፊዎችን ሀገር ያወረሰህ ነህና ከአሸናፊነት ውጭ ሌላ አትመልከት፣ ከአሸናፊነት ውጭ የሚመጥንህ፣ የሚስማማህ አንዳች ነገር የለም እና ለማሸነፍ ብቻ ተነስ፣ ለድል ብቻ ገስግስ፡፡

ጠላትህ ፈርቶህና አክብሮህ እስኪኖር ድረስ ክንድህን አበርታ፣ የምትከበረው በክንድህ፣ በአንድነትህ ብቻ ነው፡፡ ክንድህ ከዛለ፣ አንድነትህ ከላላ የዛን ጊዜ በአራቱም ንፍቅ ቆመው መድከምህን የሚከታተሉ ጠላቶች ክንዳቸውን ይዘረጋሉ፣ ነፍጣቸውን ያነሳሉ፣ አንተን ሊያጠፉህ ይነሳሉ፤ የአባቶችህን ታሪክ ያላወቁ፣ ጀግንነትክን ያልጠየቁ ሁሉ እየመጡ እየተመቱ አልቀዋል፣ በሜዳና በጋራው ሁሉ ቀርተዋል፣ የትግራይ ወራሪና አሸባሪ ቡድን ቀዬን ሊያረክስ መጥቶ አብዛኛው ተመትቶ፣ በገባበት ቀርቶ እድል የቀናው ወደ ዋሻው ተመልሷል፡፡ ሳይነኩት የነካው፣ ለዘረፋና ለውንብድና የመጣው አብዛኛው ተደምስሷል፣ የጀግኖችን ክንድ ቀምሷል፡፡ ዳሩ ዛሬም ሌላ እድል ሊሞክር፣ አሁንም ቀዬ ሊያረክስ፣ ክብር ሊጥስ እያሰፈሰፈ ነው፡፡ የሚጠብቀው ጀግኖች እንዲዳከሙለት፣ አንድ የሆኑት እንዲለያዩለት፣ አልሞ ተኳሾቹ ነፍጣቸውን እንዲያስቀምጡለት ነው፡፡ የጀግኖች አንድነት ከላላ፣ አልሞ ተኳሾቹ ነፍጣቸውን ካስቀመጡ ጠላትም ያን ጊዜ ወረራውን ያስፋፋል፣ ሀብትና ንበረት ይዘርፋል፣ ያጠፋል፡፡

የጠላቶችህ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ የክተት ዘመቻ እንደተጠራህ አስብ፣ የጠላቶችህ ዘመን አልተፈጸመም፣ የጠላቶችህ ዘመን የሚፈጸመው በአንተ አንድነት እና ጀግንነት ብቻ ነው፡፡ ሀገር ለማዳን የተጠራው የክተት ጥሪ ዛሬም እንዳለ፣ ትግሉ ገና እንዳላለቀ፣ ድሉም እንዳልተቋጨ አትዘንጋ፡፡ የጠላቶችህን ዘመን ፈጽመህ፣ ዓለማቸውን መና አስቀርተህ፣ አቅመ ቢስ አድርገህ የዛን ጊዜ የክተት ጥሪ እንዳልተጠራ ትቆጥራለህ፡፡

የአማራ መገለጫው በክብርና በሀገር አልደራደርም ማለቱ ነው፡፡ አማራ ከምንም በላይ ሠንደቁን፣ ከማንም በላይ ኢትዮጵያ ሀገሩን ያስቀድማል፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ለሠንደቁ ክብርና ፍቅር ሲል በየዘመናቱ ደም አፍስሷል፣ አጥንት ከስክሷል፤ በደሙ ጠብታ ሀገር አጽንቷል፣ በአጥንቱ ስባሪ ሀገር ገንብቷል፣ ወገን አኩርቷል፡፡ አሸባሪውና ወራሪው ቡድን ዛሬም በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች ወረራ ለመፈጸም፣ ጥቃት ለማድረስ ዝግጅት ላይ ነው፡፡

ታዲያ ጠላት የጦርነት ድግስ እየደገሰ፣ ዛሬም ለሌላ ጥፋት እየተረባረበ አንተ የምትተኛበት፣ አርፈህ የምትቀመጥበት ምንም አይነት ምክንያት የለም፡፡ ዛሬም በጀግንነት ተነስ፣ ዛሬም በአንድነት ተነስ፣ ዛሬም በአሸናፊነት ለአሸናፊነት ገስግስ፣ ያልተቋጨውን ድል ቋጨው፣ የጠላትን የመጨረሻ እስትንፋስ ዝጋው፣ ቆልፈው፡፡ ሰላምህ፣ ክብርህ፣ መከበሪያህ ያለው እራስህ ጋር ነው፡፡ የሚያለያዩህን ናቃቸው፣ የሚያቀራርቡህን አክብራቸው፣ በአንድነትህ አብር፣ ለዳግም ወረራ የሚሰናዳውን ጠላት ቀድመህ እነቀው፣ ያን ጊዜ ከእነ ሙሉ ክብርህ በደስታና በሰላም ትኖራለህ፡፡

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን እና ተላላኪው ሸኔ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመተካት እና በብሔረሰብ አስተዳደሩ ለማልማት እንደሚሠሩ ባለሃብቶች አስታወቁ፡፡
Next articleበአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ በችግር ውስጥ የሚኖሩ ሕፃናት እና ሴቶችን በዘላቂነት ለማቋቋም እና ለተግባራዊነቱም ለመሥራት ዝግጁ እንደሆኑ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ተናገሩ።