
ባሕር ዳር፡ መስከረም 27/2012 ዓ/ም (አብመድ) ኬንያዊው የረዥም ርቀት አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ ማራቶንን ከ2፡00 ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን ቢቢሲ አስነበበ፡፡
የኦሎምፒክ ማራቶን ሻምፕዮኑ ኪፕቾጌ ከሁለት ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከ42 ኪሎ ሜትር በላይ ለመሮጥ ልዩ ልምምድ ለማድረግ ወደ ኦስትሪያ ቬይና ማቅናቱ ተሰምቷል፡፡
ኪፕቾጌ ልምምድ ከሚሠራበት የስምጥ ሸለቆ ቀዬው ኢልዶሬት ከተማ ወደ ቬይና ትናንት ከእንግሊዛዊው ቢሊዮነርና የዚህ ልዩ ልምምድና ግብ ደጋፊ ሰር ጂም ራክሊፍ በተሰጠው የግል ጄት ማቅናቱ ነው የተገለጸው፡፡
ኪፕቾጌ ባለፈው ዓመት በበርሊን ማራቶን ያስመዘገበውን 2፡01፡39 የሆነ ፈጣን ሰዓት ለማሻሻል ነው ጥረት የጀመረው፡፡
ኪፕቾጌ ከ2፡00 በታች ለመግባት በቬይና ጎዳናዎች እንደሚሮጥ የታወቀ ሲሆን ጊዜውና አዘጋጆች ግን ወደፊት እንደሚገለጹ ተነግሯል፡፡