
ባሕር ዳር: ጥር 03/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት ፎረም ከተመሰረተ ጀምሮ ለሕዝብ ጥቅም የሚሰጡ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታትም በግብርና፣ በጤና፣ በትምሕርት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በሌሎች ዘርፎች ላይ በትኩረት ሠርቷል፡፡
የፎረሙ ዋና ጸሐፊ ዶክተር አስማረ ደጀን እንዳሉት አሸባሪው ቡድን የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ ፎረሙ ከክልሉ መንግሥት ጎን ኾኖ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው፣ ሃብትና ንብረታቸው ለወደመባቸው እና ለተፈናቀሉ ወገኖች ደራሽ ድጋፍ ማድረጉን ጸሐፊው ተናግረዋል፡፡ ፎረሙ በቻለው አቅም የክልሉን ክፍተት ለመሙላት ጥረት አድርጓል ነው ያሉት፡፡
ዶክተር አስማረ በዚህ ጦርነት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የሕዝባዊ ማዕበል ሊፈጥር እንደሚችል ትንበያ በመሥራት የአማራ ሕዝብ መመከት የሚችልበትን ስልት ለክልሉ መንግሥት አሳውቋል ብለዋል፡፡ ከአማራ ምሁራን መማክርት ጋር በመሆን ጠላት በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወደ ቀበሮ ጉድጓድ የገባው ለማዘናጋት እንደሆነ እና የሀገሪቱ ስጋት እንደሚሆን ትንበያ ሠርቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ወጣቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ተቀላቅለው ጠንካራ ሠራዊት እንዲገነባ የማስዝገንዘብም ሥራ ማከናወኑንም አብራርተዋል፡፡
ዶክተር አስማረ እንዳሉት የዩኒቨርሲቲዎች ፎረሙ በወሰን እና ማንነት ጥያቄዎች ዙሪያ በርካታ ጥናታዊ ሥራዎችን በማከናወን ምክረ ሐሳቦችን አዘጋጅቷል፡፡
አሸባሪው ቡድን በፀጥታ ኀይሎች ጥምረት ተቀጥቅጦ ከተሸነፈ በኋላም በክልሉ የደረሰውን ስርቆት እና ሁለንተናዊ ውድመት የሚያጠና ቡድን መሠማራቱን ዶክተር አስማረ ተናግረዋል፡፡
ፎረሙ በመልሶ ማቋቋም ክልላዊ ዐቢይ ኮሚቴ አባል በመሆን እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ በግብርናው ዘርፍ ጉዳት ከደረሰባቸው ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ውጪ እያንዳንዳቸው ከ200 እስከ 1 ሺህ ሄክታር የበጋ ስንዴ በመስኖ እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አፈጻጸማቸውም በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ ከአማራ ምርጥ ዘር ድርጅት ጋር በመሆን በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን የዘር እጥረት ለመፍታት እየሠራም ይገኛል፡፡ ይህም ለክልሉ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
‹‹የባሰ ጦርነት ከፊታችን ይጠብቀናል›› ያሉት ዋና ጸሐፊው ይህንን መመከት የሚያስችል የተተነተነ ምክረ ሐሳብ ለውሳኔ ሰጪ አካላት ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በቀጣይም ተከታታይ ሕዝባዊ ጉባዔዎች በማዘጋጀት ጠንካራ አንድነት ያለው ሕዝባዊ አደረጃጀት እንዲኖር ይሠራል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/