
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የመከላከያ ሠራዊቱ ሲጠቀምበት በቆየው የማዕረግ ምልክት ላይ ማሻሻያዎችን አድርጓል። ማሻሻያው የተደረገበት ምክንያትም የሠራዊቱ ማዕረግ አገራዊም ይሁን ወታደራዊ ታሪካዊ ይዘት ያለውና የሠራዊቱንም ባህሪ ሊገልፅ የሚችል ሆኖ እንዲዘጋጅ በማስፈለጉ ነው።
በዚህም መሠረት በሠራዊታችን የማዕረግ ምልክቶች ውስጥ ጋሻና አንበሳ በዋናነት ጥቅም ላይ ውለዋል።
በአገራችን የቀደመ ታሪክም በተለይ ጋሻው በንጉሱም ይሁን በደርግ ዘመን በሠራዊቱ የማዕረግ ምልክቶች ላይ ጥቅም ላይ ውሏል። ንጉሱ ዘውድን በማዕረግ ምልክትነት ሲጠቀሙ፣ ደርግ ዘውዱን መቀየር ስለነበረበት ዘውዱን በአንበሳ ተክቶ ተጠቅሞበታል። እነዚህ ሁለቱም ታሪካዊና ወታደራዊ ምልክቶች ናቸው።
አሁን ስንጠቀምበት የቆየው የሠራዊቱ ማዕረግ እነዚህን ምልክቶች በመሰረታዊነት ነበር የቀየራቸው። በርግጥም ሲታይ ታሪካዊና አገራዊ ይዘቱ የጎላ አልነበረም። ሠራዊት ዘመን ተሻጋሪ መሆን ካለበት ዓርማውም፣ ማዕረጉም፣ ሌሎችም ነገሮች ስርዓት ሲለዋወጥ መቀየር የለባቸውም።
የደርግ ሠራዊት የማዕረግ ምልክቶች መሰረታዊ ይዘታቸው አገራዊ ነበር። ይህ የተሻሻለው የማዕረግ ምልክት እነዚህን አገራዊ፣ ታሪካዊና ወታደራዊ ይዘቶች በአንድ በኩል ታሪክን ከማስቀጠል አንፃር እንዲመለሱ ከማድረጉም በላይ ባላቸው አገራዊና ወታደራዊ ታሪካዊ ይዘት ምክንያት ከመጣውጋር የመቀየር እጣ አይኖራቸውም።
ወደ ምልክቶቹ ስንገባ፣ ጋሻ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስከብራ እንድትቆይ ያስቻሏት ቀደምት አባቶቻችን የተጠቀሙበት ወሳኝ የመከላከያ መሳሪያ ነው።
አርበኝነትም፣ ተጋድሎም አገርን የመከላከል ጉዳይም ሲነሳ ጋሻ ቀድሞ የሚመጣ መሳሪያ ነው። በርግጥ ጦርም ጎራዴም አሉ፣ እንደ ማጥቂያ መሳሪያነት። ሁሉንም ማመላከት ስለማይቻል ሠራዊታችንም የመከላከያ ሠራዊት መሆኑን ለማመላከት የመከላከያ መሳሪያ የሆነው ጋሻ በተሻሻለው አርማ እንዲካተት ተደርጓል።
ሌላው አንበሳው ነው። ስለአንበሳ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል። በዋናነት ግን እኛ ኢትዮጵያውያን፣ ጥቁር ህዝቦች፣ ነፃነታችንን ሳናስደፍር የአገራችንን ሉአላዊነት አስከብረን የቆየን አንበሶች ነን፣ ጥቁር አንበሶች።
አንበሳ ጉልበት አለው፣ ጉልበቱን ደሞ በጥበብ የሚጠቀም እንስሳ ነው። እንደ ወታደር ስትራተጂ ያውቃል፣ ስልትም ያውቃል፣ ኢላማውን ከመምረጥ ጀምሮ በምን መልኩ ይዞ መጣል እንዳለበት ያውቃል። በዚህ ላይ ደግሞ ጉልበት ስላለው ብቻ የፈለገውን እንደፈለገው አያደርግም።
አንበሳ ኤቲካል እንስሳም ነው (ወደ ሰው ስናመጣው ስነምግባር ልንለው እንችላለን)፤ እንደ ጅብ፣ ቀበሮና ሌሎችም እንስሳዎች ያደነውን እንስሳ ነፍሱ እያለ ሲበላ አይታይም፣ ህይወቱ ሳይወጣ አይበላም።
በሌላ በኩል ደግሞ በአቅም ከሱ ያነሱ፣ ሮጠው ሊያመልጡት የማይችሉ አነስተኛ እንስሳት ላይ ጉልበቱን ሲያሳይም አይታይም። ሊተናኮሉት ሲሞክሩም አቅሙን ስለሚያውቅ ብዙ አያሳስቡትም። ይሁን እንጂ ከሱጋ የሚገዳደር ጉልበት ሲመጣ ግን ተገቢውን ምላሽ ይሰጣል።
ይህ የአንበሳ ባህሪ በበርካታ ጉዳዮች ሠራዊታችንን በትክክል ይገልፃል።
ውጊያ የራሱ ህግጋት አሉት፣ አውዳሚና ገዳይ አቅም ስለተያዘ ብቻ ስርአት በሌለው መንገድ ጥቅም ላይ አይውልም። ሠራዊታችን ሊገድለው የመጣውን ጠላቱን እንኳን ከማረከ በኋላ ተንከባክቦ የመያዝ፣ ጭካኔያዊ ተግባር ያለመፈፀም፣ ባጠቃላይ ለሚያጋጥመው ስጋት ተመጣጣኝ ምላሽ የመስጠት ህግጋትን በፅናት የሚተገብር ምግባር የተላበሰ ነው።
በመሆኑም የሠራዊታችን የማዕረግ ምልክት በዋናነት አንበሳውን ሰራዊታችንን እና ህዝባችንን በሚገልፀው የአንበሳ ምልክትና የአገር ሉዓላዊነትና ክብር የማስጠበቃችን ምልክት የሆነውን ጋሻ እንዲያካትት ተደርጎ ተዘጋጅቷል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊት
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/