
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ላልይበላ ቅን ልቦች፣ ጠቢብ እጆች እና ትሁት እሳቤዎች ተዋህደው የገነቡት የጥበብ አልፋ እና ኦሜጋ ነው፡፡ እርሱን የመሰለ ከቀደመም አልነበረም እስካሁንም አልተፈጠረም፡፡ ቅድስና ከመሪነት፣ ጥበብ ከትግስት እና ሩቅ አሳቢነት ከብልህነት ጋር ተዋህደውበታል፡፡ አልባሬዝ “እኔ ያየሁትን ብናገር ማን ያምነኛል” እንዳለ፤ ኢትዮጵያዊ እናቶች “ዐይኔ ዓለም አየ እግሬ ደርሶ እንደሚሉ” ላልይበላ ትናንትም ሆነ ዛሬ ለተመልካቹ አዲስ ነው፡፡
የዓለም ሚስጥር የሆነችው ሀገር ብዙ የጥበብ ሚስጥር የሆኑ አሻራዎችን አደባባይ ላይ ዘርግታ አሳይታለች፡፡ ኢትዮጵያ ሁሉም የሚያያት ሀገር ብትሆንም የሚረዷት ግን የተመረጡት ናቸው፡፡ የፈተናዋ መብዛት፣ የመከራዋ መበርታት እና በጽናት የመሻገሯ ምስጢርም ፈታኞቿ የሚመለከቷት እንጂ የሚረዷት ካለመሆናቸው የመነጨ ነው፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ ያለችው ኢትዮጵያ ጥረቷ ሁሉ ከራሷ ጋር እንጂ ከሌሎች ጋር አልነበረምና ዘመንን የተሻገሩ አሻራዎቿ ሁሉ ትናንቷን እና ገናናነቷን ከፍ አድርገው የሚናገሩ ናቸው፡፡
ቅድስናን ከምንፍስና፤ ክህነትን ከንግስና ያዋሃደው ጠቢብ ከ900 ዓመታት በፊት በደብረ ሮሃ ከአንድ አለት 11 አብያተ ክርስቲያናትን አንፆ እንኳን በጆሮ የሚሰሙት በዐይናቸው የሚያዩትን እንኳ ለማመን እስኪከብዳቸው የኢትዮጵያን ታላቅነት በጽኑ አለት ላይ መሰረተው፡፡ በቅዱስ ላልይበላ የታነጹት ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ዘመን ተሻጋሪ ብቻ ሳሆኑ ኢትዮጵያ የነበራትን ከፍታ ማሳያ ምስክሮችም ሆነው ይታያሉ፡፡
ትናንት ኢትዮጵያ የሰራቻቸው የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዛሬ የዓለም ሕዝብ የጋራ ሃብት ናቸው፡፡ ልዩነቱ ኢትዮጵያ ከላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ ጀርባ ከፍ ያለ ምንፍስናን እና ታላቅነትን ታስተናግዳለች፡፡ ቀሪው ዓለም ደግሞ ከአንድ አለት ከተፈለፈሉት እና ከቆሙት አብያተ ክርስቲያናት በኋላ ኢትዮጵያ ገናና ታሪክ ያላት እስከማይመስለው ድረስ ከዚያ ላይ ቆሟል፡፡
ዘመንን እያለፈች አዝማናትን እየተሻገረች ከዚህ የደረሰችው ኢትዮጵያ ግን በመከራ ዘመን ውድ ሕይዎታቸውን ገብረው ቅርሶቻቸውን የሚያሻግሩ ልጆች ባለቤት እና በፍስሃ ዘመን ከአራቱም አቅጣጫ ተሰባስበው በፍቅር ትናንታቸውን የሚያከብሩ ልጆች ባለቤት ነች፡፡
በዚህ ሁሉ መካከል ግን ከውስጥም ከውጭም ኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያ የሆነውን ሁሉ የሚመኙ የውስጥ መሰሪዎች እና የውጭ ወራሪዎች ደጋግመው ታይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለዚህ ትውልድ እቅፍ ስትደርስም ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነው ሳይሆን ድሮም እንደትናንቱ ራሳቸውን አሳልፈው ሀገራቸውን የሚያጸኑ ልጆች ስለነበሯት ነበር፡፡ ዘንድሮም ልደትን በላልይበላ ለመመልከት እና በቤዛ ኩሉ ለመደሰት የተከፈለው መስዋእትነት አያሌ ነው፡፡
ከስድስት ወራት የመከራ እና የጨለማ ዘመን ወረራ ስቃይ ከተገላገለች አንድ ወር እንኳን ያልሞላት የጥንቷ ደብረ ሮሃ የዛሬዋ ላልይበላ በልደት ዋዜማ እና በቤዛ ኩሉ ንጋት ደምቃ ላያት የመንፈሷን ምንፍስና እና የልጆቿን ጥንካሬ ያስተውላል፡፡ የደፈሯቸውን መክረው እና የናቋቸውን አስተምረው የሚሸኙት ኢትዮጵያዊያን እነ አልባሬዝን ብቻ ሳይሆን የዚህን ዘመን የባህር ማዶ ሰዎች ያስደምማሉ፡፡ የኢትዮጵያን የጥበብ ልክ ለማወቅ ግን ጉልበት ሳይሆን እውቀት፤ ስሜት ሳይሆን ስሌት ያስፈልጋል!
መልካም ልደት!
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/