
ላልይበላ፡ ታኅሣሥ 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ የልደት በዓልን ለመታደም በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላልይበላ ተገኝተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቷ ለሃይማኖቱ ተከታዮች ባስተላለፉት መልዕክታቸው “ከስድስት ወራት የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ በኋላ ልደትን በላልይበላ እንዲህ በደመቀ መልኩ እንድናከብር ውድ ሕይዎታቸውን ለከፈሉ ሁሉ ምሥጋናችን ይድረስ” ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ላልይበላ የምትታወቀው ለ900 ዓመታት በዘለቀው የመንፈሳዊነት፣ የቅድስና እና የጥበብ አሻራዎቿ መሆኑን አውስተው ይህ ጥንታዊ እና ታሪካዊ አሻራ ለትውልድ እንዲቀጥል በየጊዜው ውድ ዋጋ ተከፍሏል ነው ያሉት፡፡ በቅርቡ የታየውም የዚሁ ጥንታዊ የተጋድሎ አሻራ ውጤት እንደሆነም አንስተዋል፡፡
ላልይበላ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የዓለም ሕዝቦች ቅርስ ናት ያሉት ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ነዋሪዎቿ በተደጋጋሚ ከደረሰባቸው ዘረፋ እና መንገላታት አገግመው ዛሬም እንደትናንቱ ሁሉ የዓለምን ሕዝብ በፍቅር፣ በትህትና እና በኢትዮጵያዊ ዕሴት እንዲቀበሉ ማገዝ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ኢትዮጵያውያን የሚያምርባቸው ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት በአንድ ላይ ተሰባስበው ፍቅርን፣ መተሳሰብን እና መረዳዳትን ሲሰብኩ ነው ብለዋል፡፡ ዳግም ወደር አልባ ጭካኔን፣ ወደር አልባ ጥላቻን እና ወደር አልባ መጠላለፍን አይሆንም ልትሉ ይገባል ሲሉም መክረዋል፡፡ ተመክሮ እና ተዘክሮ እምቢ ላለ ደግሞ ወታደሩ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ ማዕበል እንደሚሆን እናንተ ሕያው ምስክሮቼ ናችሁ ነው ያሉት፡፡
ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ በወረራው ለማናጋት የተሞከረው የኢትዮጵያውያንን ማኅበራዊ መስተጋብር እንደነበር አውስተው በሃሳብ ልዕልና የሚያምን ትውልድ እንዲፈጠር የሃይማኖት ተቋማት እና የሚመለከታቸው አካላት እንዲሠሩም ጠይቀዋል፡፡
ለ900 ዓመታት መንፈሳዊነትን፣ ምሕንድስናን እና ጥበብን አቅፋ እና ደግፋ የዘለቀችው የላልይበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት እድሳት በመንግሥት ትኩረት እንደተሰጠውም በመልዕክታቸው አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/