‹‹የቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አንዱ የታላቅነታችን ማሳያ ነው›› አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ

162

ላይበላ፡ ታኅሣሥ 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በልደት በዓል አከባበር ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ፍጹም ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው፣ የተጣሉ የታረቁበት፣ ፍቅር የተሰበከበት፣ አንድነት የታወጀበት የፍቅር እና የነጻነት በዓል ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለብዙ ሺህ ዓመታት በነጻነት የኖረ፣ ነጻነቱን የሚወድ ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡ ነጻነትን የሚወድ ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም የሚያከብር እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

ሚኒስትሯ የልደት በዓል ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በልዩ ድምቀት መከበሩ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡ ዘር፣ ባሕል፣ ቋንቋ ሳይገድባቸው ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት በአንድ መንፈስ ተሰብስበው በበዓሉ መታደማቸው ልዩ ኩራት እንደሚሰጥም ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በአንድ ልብ ለጋራ ዓላማ የሚቆሙ፣ ለጋራ ልማት የሚተባበሩ፣ በአንድ መንፈስ ሀገራቸውን የሚወዱና ደምቀው በሕብረት እንደ ችቦ የሚያበሩ እውነተኛ ኢትዮጵያውያን ናቸው ብለዋል፡፡ ዛሬ የታየው ሕብረትና አንድነትም የዚህ ነጸብራቅ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አኩሪና በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ገበያ ግንባር ቀደም ተወዳዳሪ የሚደርጓት የባሕል፣ የታሪክና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆኗን ገልጸዋል፡፡ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ ሰፊ ታሪካዊ፣ ባሕላዊና መልክዓ ምድራዊ ሀብት ያላት መሆኗንም ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ‹‹የቅዱስ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አንዱ የታላቅነታችን ማሳያ ነው›› ብለዋል፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት የኮሮና ቫይረስ በፈጠረው ተጽዕኖ እና አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በፈጸመው የግፍ ወረራ ምክንያት የቱሪዝም ሀብቱን እንደቀደመው ጊዜ ሳንጠቀም ቀርተናል ነው ያሉት፡፡ አሁን ግን መንግሥት በወሰደው ቁርጠኛ ርምጃ እና በኢትዮጵያውያን ርብርብ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ነጻ ማድረግ እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የደረሰውን ሁለንተናዊ ጉዳት ለማከም የሁሉንም ርብርብ ይፈልጋል ብለዋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም በዚህ ረገድ በርካታ ተግባራትን ለማከናወን እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የልደት በዓል የሀገሪቱን ሰፊ የቱሪዝም ሀብት የምናስተዋውቅበት ብቻ ሳይሆን በባሕል፣ በታሪክና በመልክዓ ምድር በስፋት መልማት የሚችሉ አዳዲስ የመስሕብ ሀብቶች እዳላት ጭምር የምናሳይበት ነው ብለዋል፡፡ ዘርፉ እምቅ የኢኮኖሚ ሀብት ያለው በመሆኑ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የቱሪዝም ዘርፉ ማመንጨት የሚችለውን የኢኮኖሚ አቅም እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዓሉ ሲከበር በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን፣ የዘማቾችን ቤተሰቦች እና ሀገርን ለማስከበር በዱር በገደሉ እየተዋደቁ የሚገኙ ጀግኖችን በማሰብ ሊሆን እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በቅዱስ ላልይበላ በቤዛ ኩሉ ሥነ-ስርዓት ላይ ባስተላለፉት መልእክት ያነሱአቸው ሀሳቦች
Next article“ልደትን በላልይበላ እንዲህ በደመቀ መልኩ እንድናከብር ውድ ሕይዎታቸውን ለከፈሉ ሁሉ ምሥጋናችን ይድረስ” የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ