
ባሕር ዳር፡ መስከረም 26/2012 ዓ/ም (አብመድ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በደዋ ጨፋ ወረዳ በወለዲ ከተማ ጥያቄ ሆኖ የኖረው የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ መፍትሔ በማግኘቱ መደሰታቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በከተማዋ ቦታ የተሰጣቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት እስከ ሁለት ዓመት ተደራጅተው ቆይተው የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ተቀብለዋል። ነዋሪዎቹ ቤት ለመሥራትም የክረምቱን መውጣት እየተጠባበቁ ነው። ጥያቄው እንደቆየና ቦታውን በማግኘታቸው እንደተደሰቱ የገለጹት ነዋሪዎቹ በቤት ኪራይና ከወላጅ ጋር ተጠግተው ሲኖሩ ለነበሩ ሰዎች ትልቅ መፍትሔ ነው።
የወለዲ ከተማ ንዑስ ማዘጋጃ ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፉአድ ሰይድ ደግሞ በከተማዋ 65 ያክል ማኅበራት ተደራጅተዋል። በ2011 ዓ.ም ለ10 ማኅበራት ቦታ ለመስጠት ዕቅድ ተይዞ በተያዘው በጀት ዓመት ለሁሉም ቦታ ተሰጥቷል። በዚህም 225 የሚሆኑ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ፈላጊዎች ተስተናግደዋል። ማዘጋጃ ቤቱ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ የከፋ ችግር እንደሌለበት የገለፁት አቶ ፉአድ ቀሪ ማኅበራትን የቦታ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ እንደሚሠሩም ገልፀዋል።
ለተጠቃሚዎች ቦታ ሲሰጥ የመሠረተ ልማት ከተሟላ በኋላ እንደሆነም ተገልጿል። ቦታ አሰጣጡ ግልጽ እንደሆነና በሕገ ወጥ መንገድ ቦታ የሚሰጥበት አግባብ እንደሌለም አረጋግጠዋል። የቦታ ፈላጊዎችን ጥያቄ ለመመለስ በየዓመቱ ዕቅድ እንደሚይዙ የገለፁት አቶ ፉአድ በ2012 ዓ.ም ለ11 ማኅበራት የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ እንደሚሰጥም ገልፀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ