❝እነሆ ጌታ ተወልዷል፣ ዓለምም በብርሃን ተመልቷል❞

223

❝እነሆ ጌታ ተወልዷል፣ ዓለምም በብርሃን ተመልቷል❞

ታኅሣሥ 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ምንም ሳይኖር፣ ምንም ሳይፈጠር አስቀድሞ ይኖር ነበር። አኗኗሩ ረቂቅ ነው። ፍጥረታትንም ፈጠረ፣ ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር አሸጋገረ፣ ከዓለም በፊት የነበረ፣ አሁንም ያለ፣ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር፣ መነሻውና መዳረሻው የማይመረመር ኃያል። አልፋና ዖሜጋ እየተባለ የሚመሰገን ኹሉንም ማድረግ የሚችል፣ በኹሉም መገኘት የሚችል፣ ኹሉንም የሚያውቅ ፈጣሪ። ፍጥረታትን አሳምሮ ፈጠራቸው፣ አስውቦ አስቀመጣቸው።

ሕግንም ሠራ። ከፍጥረታት መካከል ተውቦና አምሮ የተፈጠረው የሰው ልጅ ሕግን ተላለፈ፣ ጌታውን በደለ፣ ፈጣሪውን አሳዘነ። ረሃብና ጥም፣ ስቃይና እንግልት ከማይታወቅበት፣ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ከመላበት፣ ፈጣሪ በሚመሰገንበት በገነት ይኖር ነበር። የሰው ልጅ ግን ሕግን ተላልፏልና ከተወደደችው ሥፍራ ወጣ። በጥፋቱም ተቀጣ፣ በተቀጣም ጊዜ አዘነ፣ አለቀሰ፣ በድያለሁና ይቅርታህን አድርግልኝ ሲል ተማፀነ። ጨለማ ወርሶታል፣ መከራው መጥቶበታል፣ ክብርና ልዕልና ርቆበታልና አምርሮ አለቀሰ። ደግ አምላክ፣ ኹሉን ቻይ፣ ለአዘኑት ይቅር ባይ ነውና የሰውን ልጅ ለቅሶ ተመለከተ። ተበድሎ ሳለ ሊክስ፣ የሰው ልጅ ረክሶ ሳለ ሊቀድስ፣ ከገነት ወጥቶ ሳለ ወደ ሥፍራው ሊመልስ ወደደና የሰውን ልጅ ሐዘን ተመለከተ። ሩህሩህ ጌታ ያድነው ዘንድ የማይሻር ቃል ኪዳን ሰጠው። ቃሉን የማያሳልፈውና የማያጥፈው ጌታ ያድነው ዘንድ ቃል ኪዳን ገባለት።

ከሰማየ ሰማያት እንደሚወርድ፣ ከንጽሒት፣ ቅድስት፣ ብጽሒት፣ ድንግል ከኾነች፣ መንፈስ ቅዱስ ካደረባት ከድንግል ዘንድ እንደሚወለድ፣ አድጎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞቶ፣ በኃይሉ ከሙታን ተለይቶ ተነስቶ እንደሚያድነው ቃል ገባለት። ከተወደደችው ገነት የወጣው የሰው ልጅ ቃሉ ይፈፀም ዘንድ ጠበቀ። የመዳኛውን ዘመን አሰበ። ዘመናት ነጎዱ። የአዳምን እዳ እና በደል ሊሽር፣ ከፍዳው ዘመን ሊያወጣው እግዚአብሔር የምህረት ዓይኖቹን ወደ ምድር ላከ። አዳምና ልጆቹ የተስፋውን ዘመን ጠበቁ።

በእስራኤል ፈጣሪውን የሚፈራ፣ ደግነት የበዛለት፣ ቅድስና ያለው ስምዖን የሚባል ሰው ይኖር ነበር። በስምዖን ላይ ቅዱስ መንፈስ አድሮበታል፣ በረከት ተሰጥቶታል። በዘመኑ ነግሦ እስራኤልን ሲገዛ የነበረው ንጉሥ መጻሕፍት እንዲተረጎሙ ለካህናት ትዕዛዝ ሰጠ። ስምዖንም ከተርጓሚዎች መካከል አንደኛው ነበር። የኢሳያስን ትንቢት ይተረጉም ዘንድም ለስምዖን ደረሰው። ይተረጉም ዘንድ ሥራውን ጀመረ። በመካከልም “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች” የሚል አገኘ። ስምዖን ግራ ተጋባ፣ አብዝቶ አሰበ፣ ተጨነቀ፣ በድንግልና መፀነስ እንዴት ይሆናል? ሲልም አሰበ። ስምዖን አብዝቶ ተጨነቀ። እንዴት አድርጌ ልተርጉመው ሲል አሰበ። እነሆ አንዲት ሴት ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች ብዬ ልተርጉመው ሲል ከራሱ ጋር ተስማማ። ሴት ብሎ ተረጎመው። አንቀላፋም፣ ከእንቅልፉ ሲነቃ ድንግል ተብሎ አገኘው፣ መልሶ ሴት አለው አሁንም ድንግል ተብሎ አገኘው፣ በነገሩ የተገረመው ስምዖን ዳግም ሴት ሊለው ሲል ትዕዛዝ ከሰማይ መጣ።

ትንቢቱ ሊፈፀም ግድ ነውና ከፈጣሪው ቃል መጣለት። ያነበበውን እንዳለ እንዲተረጉመው ታዘዘ። ትንቢቱ እስኪፈፀም ድረስ እንደሚቆይም ተነገረው። ዘመናት ቀረቡ። የመዳን ቀን እየደረሰ መጣ። የነቢያት ትንቢት እውን ሊሆን ፣ የአዳም እንባ ሊታበስ፣ ወደ እርስቱም ሊመለስ፣ በድሎ ሳለ ሊካስ፣ በጨለማ ካባ ውስጥ ተጠቅልሎ ሳለ ብርሃን ሊለብስ፣ በገነት ሊመላለስ፣ ዘመኑ ቀረበ። በሲዖል መከራው በርክቷል፣ ለቅሶ በዝቷል። የመዳን ቀን እስኪመጣ ድረስ እንባቸው ይፈስሳል፣ ጩኸቱም ይቀጥላል። እንባ አባሹ፣ ፀጋ አልባሹ፣ ተበድሎ ካሹ አምላክ ዘመኑ ደርሶ እስኪመጣ ድረስ እየተጠበቀ ነውና።

የትንቢቱ መፈፀሚያ ዘመን ደረሰ፣ የመዳን ቀን ቀረበ። ቅድስተ ሐና ተወለደች፣ አደገችም። ለአካለ መጠን ስትደርስ ከአይሁድ ወገን ለኾነ ኢያቄም ለተባለ ደግ ሰው አጋቧት። ቤታቸው የተቀደሰ ነበር። ልጅ ግን ያገኙ ዘንድ አልቻሉም። እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ እያለቀሱ ይማፀኑ ነበር። ሐና ማህፀኗ ዘር አልፈጠረችምና አብዝታ አዘነች። በሰርክ ለፈጣሪዋ ምልጃ አቀረበች። ከጸሎታቸው ግን አላቋረጡም ነበር። ጌታ የአብራክ ክፋይ ያጡትን ጥንዶች ተመለከታቸው። ፀሎታቸውን ሰማ። በደል ያልተገኘባት፣ በረከት የመላባት፣ የተመረጠች፣ የተቀደሰች፣ የሰላም፣ የብርሃን በር የኾነች፣ የማይቻለውን የቻለች፣ የማይዳሰሰውን የዳሰሰች ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ የሐናን ማህፀን ባረከ። ሐና ፀነሰች፣ መልካሟን ልጅ በማህፀኗ ተሸከመች።

የእግዚአብሔር መላክ ወደ ኢያቄም መጣ። ሐና እንደፀነሰችም አበሰረው። የምትወለደው ልጅ ስሟም ማርያም እንደሆነ ነገረው። ከእርሷም የዓለም መድኃኒት ይወለዳል አለው። ኢያቄምና ሐና ፈጣሪያቸውን ፈፅመው አመሰገኑ። ፀሎታቸው ፍሬ አፍርቷልና። ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ፣ ከኹሉም ያማረች፣ አብዝታ የተዋበች፣ አስቀድማ የተቀደሰች ልጅ ተወለደች። ስሟንም ማርያም አሏት። በእግዚአብሔር የተመረጠች የእርሱ ስጦታ ናትና። ማርያም ሦስት ዓመት ሞላት። ኢያቄም እና ሐና በስለትና በፀሎት ያገኟትን ልጃቸውን መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣ መጋረጃ ፈትላ ትኖር ዘንድ ለቤተ መቅደስ ሰጧት። ማርያም በቤተ መቅደስ በቅድስና ተቀመጠች።

መላዕክት የዕለት ምግቧን እያመጡ እየመገቧት በቤተ መቅደስ በክብር አደገች። ከሰማይ የመላእክቱን በምድርም የካህናቱን ዝማሬ እየሰማች አደገች። በቤተ መቅደስም 12 ዓመታትን ቆዬች። ዓለማት ለማይበቁት፣ ሳያቋርጡ የሚፈሱት አፍላጋት በእፍኙ ለማይሞሉት፣ ፍጥረታት ገፅታውን ለማየት ለማይችሉት አምላክ በምድር ማደሪያ ትኾን ዘንድ የተመረጠች ቅድስት በምድር ተገኘች። ማርያምም በቤተ መቅደስ ሳለች ጠላቶች ቤተመቅደሳችንን ታሳድፍብናለች ሲሉ ከሰሱ። እመቤቷ ከቤተ መቅደስ ትውጣም አሉ። ዘካሪያስም የማርያምን ጉዳይ ለእግዚአብሔር አቀረበ። ማርያምንም ጠብቃት አለ። ጌታም ዘካሪያስን አለው። ከነገደ ይሁዳ ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን አዛውንት በትራቸውን ሰብስበህ ከቤተ መቅደስ አስገብተህ ፀልይበት አለው። ዘካሪያስም የተባለውን አደረገ። የተባለውን ያደረገው ዘካሪያስም ፈጣሪው ኃይሉንና ፍቅሩን ያሳየው ዘንድ ተማፀነ። ለማን አደራ እንደምሰጣትም ግለጥልኝ ሲል ለመነ።

በቤተ መቅደስ ከገቡት በትሮች መካከል አንደኛዋ በትር ለምልማ፣ አፍርታ ዮሴፍ ኾይ ድንግል ማርያምን ጠብቃት የሚል ጽሑፍ ተጽፎባት ተገኘች። አረጋዊ ዮሴፍም የድንግል ማርያም ጠባቂ እንዲኾን ተመረጠ። የመዳን ቀን ደረሰ። መላኩ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ታዝዞ ሄደ።

❝መላኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥ ከዳዊት ወገን ለኾነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፣ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ። ደስ ይበልሽ፣ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። እርሷም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ የተነሳ በጣም ደነገጠች። ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት። ማርያም ኾይ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ፣ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ እርሱ ታላቅ ይሆናል፣ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል። ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለዓለም ይነግሣል። ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ማርያምም መልአኩን ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል። የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል❞ አላት።

ስምዖን ሊተረጉመው የፈራው ትንቢት ሊገለጥ ዘመኑ ደረሰ። አስቀድሞ በነብያት ትንቢት የተነገረለት፣ ኹሉም በእርሱ የኾነ ጌታ በጨለማ ውስጥ የተቀመጠውን፣ ከገነት የወጣውን የሰው ልጅ ሊያድን በማህፀን አደረ። ድንግል በድንግልና ፀነሰች።

ዓለማት የማይበቁት ጌታ አስቀድሞ ለአዳም በሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት በተቀደሰችው ማርያም ተፀነሰ። እርሱን ዘር አልቀደመውም። ማርያምም ከመፀነሷ በፊት፣ በፀነሰች ጊዜም፣ ከወለደች በኋላም በሐሳብም በሥጋም ድንግል ናት። ድንግልናዋን አልሻረውም። ❝ይህች እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጎበኝ፥ እንደ ጨረቃ የተዋበች እንደ ፀሐይም የጠራች፥ ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ማን ናት?❞ እንዳለ መጽሐፍ የተዋበችዋ ቅድስት የዓለም መዳኛ የኾነውን ፈጣሪ በማህፀኗ ተሸከመችው፣ የማይቻለውን ቻለችው፣ ግርማው የሚያስፈራውን በማህፀኗ ያዘችው።

❝አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው❞ እንደተባለች እርሷ ከሴቶች ኹሉ የተለዬች፣ የተባረከች፣ የተመረጠች፣ የተከበረች፣ የተቀደሰች ናት። የማህፀኗ ፍሬም የተቀደሰና የተባረከ ነው። የመወለጃው ጊዜ ደረሰ። ማርያም ፈጣሪዋን ወለደችው። የጨለማው ዘመን ተፈፀመ። ብርሃን በዓለም ላይ በራ። ምድር ተደሰተች፣ እልልም አለች።

በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት ሀገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው። ❝ሕጻን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም❞ እንዳለ።

ኹሉ ያለው አንዳች ያልጎደለበት፣ የማይጎድልበት፣ የማይዳሰስ፣ ረቂቅ ሥፍራ ያለው ጌታ ምንም እንደሌለው፣ መጠለያ እንዳጣ በቤተልሔም በከብቶች በረት ተወለደ። ባማረ ቦታ ይወለዳል ሲባል እርሱ ግን በበረት ተወለደ። ከብት ጠባቂዎች አዩት። መላእክት አመሰገኑት፣ ሰበዓ ሰገል ሰገዱለት። ላሞችና አህዮች እስትንፋሳቸውን ገበሩለት። ሰበዓ ሰገል በኮኮብ እየተመሩ ወደ ቤተልሔም አመሩ። በቤተልሔም የዓለም ጌታ ተወልዷልና። በቤተልሔም የዓለም ብርሃን ተገኝቷልና። በቤተልሔም የአዳም ተስፋ ተወልዷልና። በቤተልሔም የነብያት ትንቢት ተፈፅሟልና። የጨለማው ዘመን በብርሃን ተተክቷልና። በምሥራቅ የማይጠልቅ ፀሐይ ወጥቷልና። ሰበዓ ሰገልም ወርቅ፣ እጣንና ከርቤ አቀረቡለት። በክርስቶስ መወለድ የጥሉ ግድግዳ ፈረሰ፣ ሰውና መላእክት በጋራ ዘመሩ። ዓመተ ፍዳ አልቆ አመተ ምሕረት መጣ።

ስምዖን የእግዚአብሔርን የማዳን ቀን እየተጠባበቀ አምስት መቶ ዓመታትን ኖረ። የጌታን ቀን የሚጠብቀው ስምዖን በኢየሩሳሌም ተዳክሞ ነበር። ዬሴፍና ድንግል ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። ወደ ቤተ መቅደስም አገቡት። ስምዖንም ተበራቶ ወደ ቤተ መቅደስ አቅንቶ ነበር። አረጋዊው ስምዖን ተቀብሎ አቀፈው፣ ፈጣሪውን አቅፏልና ኃይልና ብርታት ኾነው። አመሰገነውም። ስምዖንም ትንቢቱ ሲፈፀም አይቷልና ጌታ ሆይ አኹን እንደ ቃልህ ባርያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፣ ዓይኖቼ በሰው ኹሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና አለ።

እነሆ ጌታ ተወልዷል፣ ዓለምም በብርሃን ተመልቷል። በጨለማ ሰንሰለት የታሰረው የሰው ልጅም ተፈትቷል፣ ክርስቲያኖችም የተወለደውን አምላክ ያመሰገኑታል፣ በልደቱም ቀን እልል እያሉ በዓሉን ያከብሩታል። ያም ቀን ደርሷልና እንኳን ደስ ያላችሁ፣ እንኳን አደረሳችሁ።

በታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleሕዝበ ክርሰቲያኑ የልደት በዓልን ሲያከብር የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።
Next articleፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ የልደት በዓልን ለማክበር ላልይበላ ገቡ።