
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 28/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የእኛነታችን ነጸብራቅ፣ የአልደፈር ባይነት አርማችን፣ እንደሻማ ቀልጦ ከጨለማ የታደገን፣ በእሱ ሞት እኛን ያኖረ ስልጡን፣ ሥርዓት ያለው፣ ጽኑ፣ ቅን፣ ታዛዥ፣ የፍቅር ቋት ነው ወታደር፡፡ አባላቱ ሕዝቡን ሊያመሰግኑ ከአሚኮ ቅጥር ግቢ ተገኝተዋል፡፡ ስለ ሀገሩ ደሙን አፍስሶ፣ ስለክብሯ ስጋውን ቆርሶ፣ አብዝቶ ለሚወደው ሕዝብ እሱነቱን አሳልፎ የሰጠ ወታደር በምን ቃል ይገለጻል? በዛሬ ጽሑፋችን የሀገሪቱን የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ በመዳፉ ይዞ ከሚፋለመው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ አንድ ክፍለ ጦር ላይ ትኩረታችንን አድርገናል፡፡
የ2014 ዓ.ም ፈጣን ምርት ይሏታል፡፡ እንደ ክፍለ ጦር ከተቋቋመች አጭር ጊዜዋ ነው፡፡ ታዲያ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሳ የሚደነቅ ጀብድ ፈጽማለች፡፡ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በብቃት ጠብቃለች፡፡ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ፣ በአበርገሌ እና በፍቼ ሰላሌ የተሰጣትን ተልዕኮ በስኬት አጠናቅቃለች፡፡ በምዕራብ ዕዝ ሥር የምትገኘው 34ኛ ክፍለ ጦር፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ደብረ ታቦር ከተማን ወርሮ ሊዘርፍና ሊያወድም ስምንት ኪሎ ሜትር ያሕል ርቀት ሲቀረው እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ተስፈንጥራ በመድረስ ወረራውን ቀልብሳዋለች፡፡ በጉና ተራራ ላይ አሸባሪውን ቡድን ዳግም እንዳይነሳ አድርጋ ድባቅ መትተዋለች፡፡ ጠላት ከሀገር የዘረፈውን ከባድ መሣሪያ ተጠቅሞ 15 ጊዜ ወደ ከተማዋ ሊገባ በተለያዩ አካባቢዎች የቆረጣ ውጊያ ቢሞክርም በበሳል ወታደራዊ መሪዎቿ እና የማሸነፍ ወኔ በተላበሱ ጀግና የሠራዊት አባላቷ ወደ መቃብር አውርደዋለች፡፡
እነዚያ ድንቅ የሠራዊት አባላት በጠላት አስከሬን ላይ በጀግንነት እየተረማመዱ ጋሳይ፣ ጎብጎብ፣ ነፋስ መውጫ፣ ጨጭሆ፣ የመሳሰሉ አካባቢዎችን ነጻ እያወጡ ገሰገሱ፡፡ የጥፋ መልዕክት ያነገበው ወንበዴ ቡድንም 716 ጫማ ከፍታ ወዳለው የደብረ ዘቢጥ ሰንሰለታማ ተራራ ፈረጠጠ፡፡ በዚያ አስቸጋሪ ቦታ ላይ ዳግም ምሽግ ቢሠራም በአስደናቂ ቅንጅታዊ ስምሪት ምሽጉ ተደርምሷል፡፡ ጠላትም በበቅሎ አግት ተራራ እና አካባቢው ላይ ወደ አፈርነት ተቀይሯል፡፡ አማራን አንገት ለማስደፋት እንደ ሾተል አሰፍስፎ ከገባበት ሳይወጣ እንደ ቅጠል ረግፏል፡፡ ከዚያ የተረፈውም ወደ ኋላ መፈርጠጡን ቀጠሏል፡፡
34ኛ ክፍለ ጦር ፋና ወጊ በሆነችበት ግንባር የጸጥታ ኀይሎች ጥምረት ደብረ ዘቢጥን፣ አግሪትን፣ ኮኪትን ነጻ አወጣ፡፡ አካባቢው በደን ስለተሸፈነ ፍላቂት ገረገራን ነጻ የማውጣት ሂደቱ አስቸጋሪ ቢሆንም ጠላት የሠራዊቱ ላንቃ የሚተፋውን እሳት የመመከት አቅም አልነበረውም፡፡ እናም 34ኛ ከ33ኛ ክፍለ ጦር ጋር በፈጠረችው ጥሩ ጥምረት ጠላትን ድባቅ እየመታች ጳጉሜን 5/2013 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡ 30 ስዓት ገደማ ፍላቂትን በእጇ አስገብታ ለከተማ ነዋሪው የአዲስ ዓመት ብሥራት አጎናጽፋለች፡፡
ጉዞዋ ሳይገታ ወደፊት ቀጠለች፡፡ ጠላት እየቀመሰ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ከፈረጠጠ በኋላ አርቢት ላይ ጠንካራ ያለውን ምሽግ ሠርቶ ጠበቀ፡፡ ይሕ ምሽግ ከአስፓልት ዳር 12 ኪሎ ሜትር ወደ ቀኝ እና 12 ኪሎ ሜትር ወደ ግራ የተሠራ ነበር፡፡ ተዓምረኛዋ 34ኛ መንግሥት በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ቆም ብላ በሰው ቁመት ልክ የተሠራውን ምሽግ ለመደርመስ ወታደራዊ ስልት ስትነድፍ ቆየች፡፡ ከዚያም ከ51ኛ ክፍለ ጦር ጋር በመሆን ሚሊሻውን ደጀን አድርጋ በግራና በቀኝ ጠላትን ቀለበት ውስጥ አስገባች፡፡
የወገን ጥምር ጦር በተሰጠው ግዳጅ እና ተልዕኮ ጠላት ተስፋ ያደረገው ምሽግ ከሞት ሊታደገው አልቻለም፡፡ በዚህ ውጊያ ለዘረፋ አማራ ክልልን የረገጠው ጠላት መቀሌን እየናፈቀ ወደ ትቢያነት ተቀየረ፡፡ ጀብደኛዋ 34ኛ ግን በደረሰችበት ሁሉ የሕዝቡን እንባ እያበሰች ገሰገሰች፡፡ ጀግኖቹ የሠራዊት አባላትም ለሕዝቡ ብስኩትና አስቃጥላ እየጋበዙ ጥበብ በተሞላበት አመራርና ወታደራዊ ዲስፕሊን ጋሸን ነጻ አወጡ፡፡
ጠላት በድጋሜ ሀሙሲት አካባቢ በባሕር ዛፍ ውስጥ ፈታኝ ምሽግ ሠርቶ ጠበቀ፡፡ ሆኖም ግን በተለመደው ወታደራዊ ጥበቧ አካባቢውን እያጸዳች እስከ ሙጃ ድረስ ዘለቀች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እስከ ኮን ድረስ በመዝለቅ ለወራት ተራርቀው የነበሩ እናትና ልጅን አገናኘች፣ የተነፋፈቁ ጎረቤታሞችን አገናኝታ በደስታ አላቀሰች፡፡ በዚያ ግንባር በድል የጀመረችውን ውጊያ በድል ቋጨች፡፡
ይህንን ጀብዱ የተመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለ34ኛ ክፍለ ጦር ‹ግድግዳው› የሚል ልዩ መጠሪያ ሰጥተዋታል፡፡ የዩኒቨርሲቲ መምሕሩ መንግሥቱ ካሳው ከነሐሴ 6/2013 ዓ.ም ጀምሮ ከሠራዊቱ ጋር በግንባር ይገኛሉ፡፡ የሠራዊት አባላቱ የተጠመዱ ፈንጂዎችን ለማምከን ሲሽቀዳደሙ ማዬት ሀሴትን ያጎናጽፋል ብለዋል፡፡ የሕዝቡ ድጋፍ ደግሞ ሠራዊቱ በወኔ እንዲጓዝ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል፡፡
በተለይ ለጦርነቱ ቅርበት የነበረው ሕዝብ የትግሉ ዋንኛ አካል እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ መላው ኢትዮጵያዊያን ያደረጉት ድጋፍ የሚስመሰግን ነው ብለዋል፡፡ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ የክፍለ ጦሩ አባላት እንዳሉት ውጊያ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የነበረው የሕዝብ ድጋፍ ለሠራዊት ማሸነፍ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ በክፍለ ጦሩ የሚዲያ ኀላፊ ሃምሳ አለቃ ታምሩ ጌታሁን እንዳለው የደቡብ ጎንደር እና የሰሜን ወሎ ሕዝብ በአንድ በኩል ምግብና አልባሳት እያቀረበ ከሠራዊቱ እኩል ተሰልፎ ተዋግቷል፡፡
ወታደራዊ ዘጋቢው አሥር አለቃ ትዛዙ አስፋው በበኩሉ የጀግኖቹን የአማራ ልዩ ኀይል፣ ፋኖ እና የሚሊሻ አባላት የጀግንነት ተጋድሎ ለመግለጽ ቃላት ያጥራል ብሏል፡፡ ይሕም የሠራዊቱ ግስጋሴ በድል እንዲቋጭ አድርጓል፡፡ የኢንዶክትሪኔሽን ኀላፊው መቶ አለቃ በልጠኖ ደገሎ ማሕበረሰቡ መከላከያን በማገዝ በኩል ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡ ወጣቱ አብሮ ተሰልፎ ሕይወቱን ጭምር እስከማጣት መድረሱ ለሠራዊቱ ያለውን ፍቅር ያሳየበት ነው ብለዋል፡፡ የሠራዊት አባላቱ በአሚኮ ቅጥር ግቢ ተገኝተው በትግል ወቅት ጦርነቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያለ የአማራ ሕዝብ ላደረገላቸው እገዛ “ምስጋናችን ለደጀኑ ሕዝባችን ይሁን!” ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/