❝ሰማያዊት እና ምድራዊት ኢየሩሳሌምን በዓለት ላይ አነፃቸው❞

281

ላልይበላ፡ ታኅሣሥ 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቢብ ልጅ በጥበብ ያድጋል፣ የጥበብን መንገድ ይከተላል፣ በጥበብ ይመላለሳል፣ በጥበብ ይኖራል። ዓለትን በጥበብ እንደ ሰበዝ ሰነጠቀው፣ እንደ አሽከር አዘዘው፣ በጠቢብ እጆቹ አሳመረው፣ እንደ እርሱ ዓለትን ያዘዘ ማን አለ? የዓለም ጠቢባን በሕንጻ ጥበባቸው መሠረቱን ተክለው ወደ ጣሪያው እየሠሩ ወጡ። ከመሠረቱም ጀምረው አስጌጡ።
ኢትዮጵያዊ ጠቢብ ንጉሥ ወቅዱስ ግን የዓለምን ጥበብ ንቆ ሥራውን ከጣሪያው ጀመረ፣ ወደ መሰረቱም ድንጋይን መረመረ፣ በጥበብ አሳመረ፣ ውቅር ወቀረ፣ አብያተ መቅደስን አነፀ፣ ድንቅ የሆነውን ሥራ ቀረፀ። ዓለማት ተደነቁ፣ በእጆቹ ሥራም ተራቀቁ። ጥበቡን ግን አጀብ ከማለት ውጭ ምን ይባላል አሉ። ረቂቅ ነውና።
ኢትዮጵያውያን የታደሉ ናቸው ምድራዊት ኢየሩሳሌም እና ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በምድራቸው አሉና። በጥበብ ተቀርፀዋልና። በኢትዮጵያ ድንቅ ጥበቦች ሞልተዋልና። ኢትዮጵያውያን ዘለዓለም ይኮራሉ፣ በአባታቸው ጥበብ ይመካሉ፣ እርሱ መልካምን ነገር አድርጓልና። በመጻሕፍት የተፃፉት፣ በሰማይ ያሉት የተቀደሱ፣ በፈጣሪ እጅ ብቻ የተዳሰሱ፣ በቅዱስ መንፈስ የተሞሉትን በምድር አስመስሎ ሠራቸው፣ አሳምሮ አስጌጣቸው። ሌሎች የሌላቸው ኢትዮጵያውያን አላቸው። ኢትዮጵያውያን ያላቸው ግን ሌሎች የላቸውም።

ቀደም ባለው ዘመን ማሕፀናቸው መልካም ልጅ ይፀንስ ዘንድ የተባረኩ ሴት ነበሩ። እኒህ ሴት ፈጣሪን በመፍራት፣ ስሙን በሰርክ በመጥራት የሚኖሩ ደገኛ ነበሩ። በቤታቸው ሲኖሩም የእግዚአብሔር መላእክ ወደ እሳቸው ሄደ። አንቺ ሴት ሆይ ደስ ይበልሽ ከአንቺ የሚወለደው ልጅ የተመረጠ ነው አላቸው። ስሙ የገነነ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ የክርስቶስን ፈለግ የሚከተል፣ በሥውር ከኤልያስ እና ከዕዝራ ጋር በገነት የሚኖር ነውም አላቸው። እኒያ ማሕፀናቸው አስቀድሞ የተባረከ እናት ቃሉን ጠበቁት። ፈፅመው አከበሩት። የመፀነሻው ቀን ደረሰ። በንፁሕ አልጋ፣ በንፁሕ ልብ፣ በንፅሕና ተዋውቀው ንፁሕ ልጅ ፀንሰው አደሩ። የመወለጃው ዘመን ደረሰ፣ ተወለደም። በመፀነስና በመወለድ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተባበረ ነበር። በመጋቢት 29 ተፀንሶ በታኅሣሥ 29 ተወልዷልና።
ይህ ልጅ በተወለደ ጊዜ በነጫጭ ንቦች ተከበበ። ያየው ሁሉ ተደነቀ፣ ምን ይሆን እያለ አሰበ። ሕፃኑ ግን አስቀድሞ ተመርጧልና በንቦች ተከበበ። ንቦችም አጀቡት እንጂ አልነደፉትም፣ አከበሩት፣ ጠበቁት፣ በዙሪያው ተመላለሱ እንጂ መርዛቸውን አልተከሉበትም። ነጫጭ ንቦቹ ከቤት የገቡትን ሰዎች እንዳይወጡ፣ ከውጭ የነበሩትንም እንዳይገቡ ከለከሉ፣ አስቀድሞ ቃል የተነገራቸው እናቱ በልጃቸው እየሆነ ያለውን ተመለከቱ። ከፅንሰቱ በፊት የተባሉትንም አስታወሱ። ንብ እንኳን ገዢውን አወቀ፣ ተረዳ አሉ። ስሙንም ላል ይበላ አሉት። ይህም ማር ይበላል እንደማለት ነው ይላሉ አበው። ፀጋ ያልተለየው ልጅ በፀጋ አደገ። በሞገስ ተጠበቀ፣ በመልካም መንገድ ተመላለሰ። ለቅድስና ተዘጋጀ።
ይህ ቅዱስ ልጅ የተወለደባት ሥፍራ ደብረ ሮሐ ትባላለች ። የእናቱ ሥም ኼርዎርና (ኬርዎርና) የአባቱም ስም ዣን (ዛን) ስዩም ይባላሉ። ደገኛ ልጅ የተሰጣቸው ደገኛ ሰዎች። አበው ላል ይበላ በተወለደ ጊዜ ታላቅ ምስጢር ተገልጧል ይላሉ። ይኸውም በተወለደ ጊዜ በንብ መከበቡ ንብ የንጉሥ ሠራዊትን ይመሰላል። ስለዚህም ንቦች በንጉሥ ሠራዊት አምሳል ከበቡት። ሳይሾሙት ንጉሥ ሆኖ መሾሙ ታወቀ። ላል ይበላ የእውቀት መንፈስና የጥበብ መንፈስ መልቶበት ተወለደ። የማስተዋል መንፈስ፣ የቅድስና መንፈስም ከእርሱ ጋር ነበሩ። አባቱና እናቱ በተሰጣቸው ልጅ ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ። በተወለደ በአርባኛ ቀኑም በአባቱ በዣን (ዛን) ስዩም፣ በእናቱ በኼርዎርና በበዛ ሠራዊት ታጅቦ አፄ ካሌብ ባሠሯት ማይ ማርያም በተባለች ቤተ ክርስቲያን ክርስትና ተነሣ።

ላልይበላ በተወለደ በስድስት አመቱ ፊደል ይቆጥር ዘንድ ለመምህር ተሰጠ። በአባቱ ቤተ መንግሥትም አባ ዳንኤል የሚባሉ መምህር ፊደል አስቆጠሩት። ዳዊት አስደገሙት። ላል ይበላ የፈጣሪውን ሕግጋት እየተማረ፣ ጥበብን እየመረመረ በጥበብ አደገ። በቤተ መንግሥት እየኖረ ሳለም አባቱና እናቱ ሞቱበት። ደገኛው ልጅ ልቡ አዘነች። ዓይኖቹም እንባን አፈሰሱ፣ አንጀቱ በሐዘን ተላወሰ። ከወንድሙ ከንጉሥ ከሐርቤ (ገብረ ማርያም ) ጋር ሆኖ ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን በተጨማሪ ሥርዓተ ቤተመንግሥትን ተማረ። በዚህ ወቅት ግን ፈተና ገጠመው። ከወንድሙ ከንጉሥ ገብረ ማርያም ቀጥሎ የሚነግሠው ላል ይበላ ነው እየተባለ ይነገር ነበርና በቤተ መንግሥቱ ቅናት መጣ። ላል ይበላም ይሞት ዘንድ ተፈረደበት። በገብረ ማርያም እህት በርብቃም መርዝ ይጠጣ ዘንድ ተሴረበት። ላል ይበላም አገልጋይ ዲያቆን እና አዳኝ ውሻ ነበረው። ከርብቃ የመጣውን ሕብስት መሳይ መርዝም ላል ይበላ ከመቅመሱ በፊት ዲያቆኑ መቅመስ ነበረበትና ቀመሰው። ዲያቆኑም ሞተ። ከዲያቆኑ የፈሰሰውን የቀመሰው አዳኝ ውሻም ሞተ።
ላልይበላም በአገልጋዩና በአዳኝ ውሻው ሞት አምርሮ አዘነ። ስለ ዲያቆኑና ስለ ውሻው ፍቅር ስል መሞት አለብኝ ሲል በፅዋው የሞላውን መርዝ አንስቶ ጠጣው። መርዙም ጣለው። ነገር ግን ለንግሥና እና ለቅድሥና አስቀድሞ የተዘጋጀ ነበርና አልሞተም። ለቀናት ግን ራሱን ስቶ ሰነበተ። በዚህም ጊዜ ጌታ በመላእክቱ አማካኝነት አስጠራው። ምስጢራትንም አሳየው። ጌታም ላል ይበላን ስሙ የሚጠራበት፣ ክብሩ የሚነገርበት፣ ስጋና ደሙ የሚፈተትበት ቤተመቅደስ ያንፅ ዘንድ አዘዘው። ጌታም የምወድህ ሆይ እነዚህን አብያተ መቅደስ ለማነፅ የምትደክመው በከንቱ አይደለም የብዙ ሰዎች መድኃኒት የሚሆኑ በረከት የሚያሰጡ በመሆናቸው ነው እንጂ አለው። ላል ይበላ ኀይልና ክብር ለበሰ፣ እንደ አድማስ ድንጋይ ጸና።

ከወደቀበትም ተነሳ፣ ከሰዎች ክፋት ይርቅ ዘንድ ወደ ጫካ ገባ። በዚያም ሆኖ ለፈጣሪው ምስጋና ማቅረብ ጀመረ። ሚስት ያገባ ዘንድም የእግዚአብሔር መላእክ ነገረው። ላል ይበላ ግን ሚስት ማግባት እንዴት ይገባኛል? ሲል ጠየቀ። ብቻውን በባዕት ውስጥ መኖር ይሻ ነበርና። የፈጣሪው ፈቃድ እስኪመጣ ጠበቀ። የጌታ ፈቃድ ኾነ። መስቀል ክብራ የተባለች ሴት አገባ። የንግሥና ዘመኑም እየተቃረበ መጣ። መንገዱ ኹሉ በጥበብ ነበር።
“መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘለዓለምን ሕይወት ያዝ።” እንዳለ መጽሐፍ የታመነለትን የዘለዓለም ሕይወት ይዞ ጸና። በትጋት መልካሙን ዘመን ጠበቀ። በቅድስና ተራመደ። ንግሥናውንም ከወንድሙ ከአፄ ገብረ ማርያም ተቀበለ። ለክብሩ ዘውድ ደፋ፣ የሚያበራ በትረ መንግሥት በእጁ ጨበጠ። ኢትዮጵያን ያስተዳድር በምድሯም ድንቅ ድንቅ ነገሮችን ይፈፅም ዘንድ በአስፈሪው ዙፋን ላይ ተቀመጠ። ስመ መንግሥቱም ገብረ መስቀል ተሰኘ።ይህም አሸናፊ ለጠላት የማይበገር ማለት ነው።

ቅዱስ ወ ንጉሥ ላል ይበላ በጥበብ ሥራውን ይፈፅም ጀመር። ደሃ እንዳይበደል፣ ፍርድ እንዳይጓደል በብልሃት አገለገለ፣ መልካሙን ነገር ኹሉ ፈፀመ። ለምድር ውበት የሚሰጡ ከእርሱ በፊት ያልተሠሩ ድንቅ አብያተ መቅደስ የሚሠራበት ዘመንም ደረሰ። እኒያ አብያተክርስቲያናት ከምድር ልብ ወጥተው የተሠሩ ናቸው ይሏቸዋል። እንጨት ያልገባባቸው፣ ጭቃ ያልተለጠፈባቸው፣ ምሦሦአቸው ድንጋይ፣ ግድግዳቸው ድንጋይ፣ ጣሪያቸው ድንጋይ፣ መሠረታቸውም ድንጋይ ነው። ይህስ ከልብ የረቀቀ ከሕሊና የተሠወረ ድንቅ ጥበብ ነው። በምድር ከላል ይበላ ውጭ እንደዚያ አድርጎ የሠራ የለም። ከኢትዮጵያ ውጭም እንደዚያ አይነት ሃብት ያለው የለም።
በሚያስደንቅ ጥበብ፣ በተሠወረ ምስጢር ፣ ከምድር ልብ ገልጦ ለሰው ልጆች ሊያሳያቸው ወደደ። በዓለት ላይ የሚገለጠው የቅዱስ ላል ይበላ ጥበብ ደረሰ። የአብያተ መቅደሱን ሥራ ያፋጥን ዘንድ ወደደ። በንጹሕ ልብ ተነሳ። የብረት መሳሪያዎችን አዘጋጀ። ምድራዊ ሐሳብን አራቀ። በዓለቱ ላይ ተራቀቀ። የሰው ልጆች ባልቻሉት ድንቅ ጥበብ ከላይ ወደታች ዓለትን አነፀ። ዓለትን አዘዘው፣ ንጉሥ ኾኖ ሳለ በእጁ የዓለት መጥረቢያ ይዞ ለጌታው መመስገኛ ይሆን ዘንድ ቤተ መቅደስ ይሠራ ዘንድ ታተረ። መኳንንቱ እና መሳፍንቱ፣ የጦር አዛዦቹ፣ የእልፍኝ አስከልካዮቹ፣ የቤተ መንግሥት ባለሟሎቹ የሚደሰቱበት፣ ተድላና ደስታ የሚያደርጉበት፣ እርሱም በዙፋን ላይ ተቀምጦ የሚደሰትበት፣ ፍርድ የሚሰጥበት ቤተ መንግሥት መሥራት አልፈለገም። እርሱ የደከመው ከዘመን ዘመን ምስጋና እየተቀረበባቸው፣ የሰው ልጆች እየተደነቁባቸው፣ መላእክት እየረበቡባቸው የሚኖሩ ድንቅ መቅደሶችን ለመሥራት ፈለገ እንጂ።

ላል ይበላ አንዲት ቤተ መቅደስ ብቻ አልሠራም። በአንድ ምሳሌ ብቻም አልቆመም። ሃይማኖቱን በዓለት ላይ ገለፀው፣ በድንጋይ ላይ አነፀው፣ ምድራዊት ኢየሩሳሌምን፣ ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን፣ አያሌ ምስጢራትን በዓለት ላይ በሠራቸው አብያተ መቅደሶቹ ላይ አነፃቸው። በምልክት አስቀመጣቸው። ቅዱሳት መጻሕፍትን በምሳሌ ዓለት ላይ ፃፋቸው። እርሱ የሠራቸውን የሚመስል የሠራ ጠቢብ አልተኘም። እርሱም ድንቅ ሥራዎቹም ድንቅ ናቸው እንጂ። አበው የላል ይበላን የእጁ ሥራዎች ማን ችሎ ይገልፃቸዋል፣ የትኛው አንደበትስ መናገር ይችላል? ይላሉ። ኹሉም በአብያተ መቅደሶቹ እየተመላለሰ በአድናቆት እያየ ከመገረም በስተቀር ምንስ ይላል።
በቅዱስ ላል ይበላ የተሠሩትን አብያተ መቅደስ ማዬትና ማድነቅ የሚወድ ቢኖር ይሂድና ይመልከታቸው። ከምድር ጠቢባን ሁሉ ላቅ ያለ የጥበብ ሥራ ያያል። አበው ቤተመቅደሶቹ እንደ ሙሴ ድንኳን የሚያረጁ አይደሉም። ዐላውያን እንዳፈረሱት እንደ ሰሎሞን ምኩራብም አይደለም ይላሉ። ይህ ረቂቅ ነውና። ኢትዮጵያውያን በላል ይበላ ድንቅ ጥበብ ይኮራሉ፣ በሥራዎቹ ጌጥ ይደምቃሉ፣ በበረከታቸው ይከብራሉ፣ በኢትዮጵያ ምድር ብቻ ስለ ተሠራው ድንቅ ሥራ በኩራት ይመሰክራሉ፣ ይናገራሉ። ከዓለማት ኹሉ የላቀ ጥበብ በምድራቸው አለና።
ቅዱስ ወ ንጉሥ ላል ይበላ ሥራዎችን አጠናቆ ጀመረ፣ እንዴት ካሉ የጀመረው ከጣሪያው ነውና። ዓለትን ከላይ ወደ ታች መረመረ። በፀጋም ከበረ። እንደ እርሱስ ጥበብን የተቸረ፣ ምስጢራትን የመረመረ ማን አለ?
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ ‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የፌደራል ተቋማት የ100 ቀናት አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በህዳሴው ግድብ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
Next articleዜና መጽሔት ባሕር ዳር ፡ ታኅሣሥ 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ)