“ትሁት ሕዝብ እግር አጥቦ ይቀበላል”

208

ላልይበላ፡ ታኅሣሥ 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) መልካም ሕዝብ ስለ መልካም ነገር ብቻ ይተጋል፣ መልካም ነገርን ያደርጋል፣ መልካም ሰዎች ምድርን በመልካም ነገር ይሞሏታል፣ ከሰማይ በረከት ያሰጧታል፣ ከፈጣሪ ጋር ያወዳጇታል። መልካም ሰዎች ስንፍናን ይተዋሉ፣ በደልን ከአጠገባቸው ያርቃሉ፣ ክፋትን ይንቃሉ፣ ጥበብን እና መልካም ነገርን ብቻ ይከተላሉ። ስለ መልካም ተግባር እንቅልፍ ያጣሉ። በትሕትና ዝቅ ብለው፣ በፀጋ ከፍ ይላሉ። በክብር ይደምቃሉ። ትሕትናቸው ስለ እውነት እንጂ በግብዝነት አይደለም። ትሁቶች ትሕትናን ወደውት ያደርጉታል፣ ሳይሰለቹ፣ ሳይታክቱ ይፈፅሙታል። በፀጋው ይከብሩበታል።

በተቀደሰችው ምድር፣ የተቀደሰውን በዓል ሊያከብሩ የሚጓዙት ብዙዎች ናቸው። በተቀደሰችው ምድር የሚኖሩት ደግሞ የሚመጡትን እንግዶች ለመቀበል በትጋት ይቆማሉ፣ በአክብሮት ይቀበላሉ። በመልካም ስብዕና እንኳን ደህና መጣችሁ ይላሉ። ትሁት ሰው በትህትና ይኖራል፣ ስለ ትህትና መልካሙን ነገር ያደርጋል። እነርሱም ትሑቶች ናቸውና ስለ ትሕትና ሁሉንም ነገር ያደርጋሉ።

የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል የሚያከብሩ አማኞች ወደ ተቀደሰችው ከተማ ላልይበላ ይጓዛሉ። በጌታ የልደት ቀን ንጉሥና ቅዱስ ላልይበላ ተወልዷልና የእርሱም በዓል ይከበራል። በዓሉ ከሌሎቹ አካባቢዎች ሁሉ ለየት ይላል። ላልይበላ ከተማም ብዙ እንግዶችን የምትቀበለው በዚህ ታላቅ በዓል ነው።

በዓሉን ለማክበር የሚመጡ አማኞችን የከተማዋ ነዋሪዎች ዝቅ ብለው እግራቸውን እያጠቡ፣ የደከመውን እያሳረፉ፣ የራበውን እያጎረሱ ይቀበሏቸዋል። ዓመት አልፎ ዓመት በመጣ ቁጥር የሚደረግ መልካም ሥራቸውም ነው። አይለዋወጥም። በዓሉን ለማክበር የሚመጡ አማኞችን ባዘጋጁት ቦታ አሳርፈው ያለ ልዩነት ሳይለዩ ሁሉንም ዝቅ ብለው እግራቸውን ያጥባሉ።

ከእንግዶቹ ምርቃት እና በረከት ይቀበላሉ፣ በዓሉም መልካም ይሆንላቸው ዘንድ ይመኛሉ። እንግዶችም ለትሁቶቹ ምርቃት እና ምስጋና ያቀርባሉ። ይህ ነው የመልካም ሰው ገበያው።

“ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢጠፋ፥ ደስ ብሎኛል፤ ከሁላችሁም ጋር አብሬ ደስ ብሎኛል፤ እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ ከእኔም ጋር አብራችሁ ደስ ይበላችሁ።” እንዳለ መጽሐፍ በጠማማ ዘመን ውስጥ የቀደመውን የአባቶችን መልካምነት፣ ደግነት፣ ዝቅ ብሎ እንግዳ ተቀባይነት ያረሱ፣ እንደ ምሳሌ የሚታዩ፣ እንደ ዓርዓያ የሚቆጠሩ ድንቆች ናቸው የላልይበላ ከተማ ነዋሪዎች። የቀደመውን የኢትዮጵያዊነት ለዛ አክብረውና ጠብቀው ይዘውታልና።

በላልይበላ ከተማ ደግነት በዝቷል፣ መልካምነት ሞልቷል። በረከት ሊቀበሉ ከሚሄዱት በረከቱን እየተካፈሉ፣ በረከት በመላበት ከተማ ውስጥ እየኖሩ በጌታ የልደት ሰሞንና ቀን በደስታና በፍቅር ያሳልፋሉ። የጌታ ልደት ለእነርሱ ደስታቸው መመኪያቸው ነውና። ወደ ላልይበላ አቅንቶ በትሕትና የሚኖሩትን ሰዎች የተመለከተ ሁሉ ላል ይበላን ይናፍቃታል፣ ይወዳታል። በመልካም ቦታ መልካም ሰዎች አሉና።

ትሁት ሕዝብ እግር አጥቦ ይቀበላል፣ እንግዶችንም ያስተናግዳል። የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በላልይበላ የሚያከብሩ ተጓዦችን ወጣቶች እግራቸውን እያጠቡ፣ መንገድ እያሳዩ፣ የደከማቸውን እያሳረፉ እንኳን ደህና መጣችሁ እያሏቸው ነው። የልደት በዓል ሰሞን በላልይበላ ጎዳናዎች እየተዘዋወረ ላየ ሁሉ የከተማዋ ወጣቶች ድንኳን ጥለው፣ ቄጤማ ጎዝጉዘው፣ የረሃብ ማስታገሻ ምግብ ይዘው እንግዶችን ለመቀበል ሲፋጠኑ ይመለከታል። እግራችሁን ካላጠብናችሁ፣ ከድካማችሁ ካላረፋችሁ እያሉ በትህትና የሚጠይቁት ብዙዎች ናቸው። እኔም የወጣቶቹ እንቅስቃሴ አስደንቆኛል። ዝቅ ብለው እግር ያጥባሉ፣ ጉልበት ይስማሉ፣ የበረከት ሥራ ለመሥራት ይፋጠናሉ።

የእንግዶችን እግር ሲያጥቡ ካገኘናቸው የከተማዋ መልካም ወጣቶች መካከል ሰጠኝ ደስታው ከሩቅ ሀገር የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ እግራቸውን በማጠብ፣ በዓሉን በሰላም አክብረው እንዲመለሱ እንሠራለን ነው ያለን። የደከሙ እንግዶችን እግራቸውን አጥበን አርፈው እንዲሄዱ እንደሚያደርጉም ነግሮናል።

ሌላኛው በጎ አድራጊ ወጣት አዳነ ተገኘ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶችን በማስተናገድ፣ ዝቅ ብለን እግራቸውን በማጠብ የነብስ ዋጋ እንገበያለን፣ ከፃዲቁ ክብር እንካፈላለን ብሏል። የፃዲቁን ሥራ ሠርተን የፃዲቁን ዋጋ ለማግኘት ነው የምንሠራውም ነው ያለው። እግር አጥበው የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ባሕልን፣ ኢትዮጵያዊነት መልካምነት የሚለውን የምናሳይበት ድንቅ ነገር ነውም ብሏል።

ያ ቀን አልፎ እንኳን እንግዶች በሰላም መጡልን እንጂ እኛ መልካም ሥራችንን እንሠራለን ብሎናል። እንግዶችን አጥበን፣ እግራቸውን ስንስም የምናገኘው የህሊና እርካታ ከፍ ያለ ነውም ብሎናል። ላልይበላ ስሞት አፈር ስሆን ተብሎ የሚበላበት፣ መልካምነት የሞላበት መሆኑንም ተናግሯል።

በጎ አድራጊዋ ወሰኔ ያለውም ‟ተግባራችን ከአባቶቻችን የወረስነው መልካምነት ነው፤ መገለጫ ባሕላችን ነው፤ በዓመት ያለንን እያቀረብን እግራቸውን እያጠብን እንግዶችን እንቀበላለን፤ ከእግር አጠባው በረከት እናገኝበታለን፤ በአባቶች እና እናቶች እንመረቃለን፤ ደስተኞችም እንሆናለን፤ በቀጣይ ዓመትም በዚሁ ተግባራችን እንቀጥላለን“ ብላለች።

ሌላዋ በጎ አድራጊ የሺህወርቅ ሲሳይም እንግዳ ተቀባይነት ከወላጆቻቸው የወረሱት መልካም ተግባር መሆኑን ነግራናለች። በሚያደርጉት ሁሉ ደስተኛ እንደሆኑም ነው የነገረችን።

በተቀደሰችው ከተማ የተቀደሰውን በዓል የሚያከብሩ እንግዶች ወደ ከተማዋ እያቀኑ ነው። ደገኛው ሕዝብም በደግነት እየተቀበላቸው ነው። በትህትና ዝቅ ብሎ በፀጋ ከፍ ማለት እንደዚህ ነው።

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleለወገንዎ ድጋፍ ያድርጉ‼
Next articleጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ አዲስ አበባ ገባች።