
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ የክልሉን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ለጎብኚዎች በሚያስተዋውቅበት እና ከዘርፉም ተጠቃሚ መሆን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የቢሮው ምክትል ኀላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮንን ቢሮው ክልሉ ያለውን የቱሪዝም ሀብት ለዲያስፖራው እና ለሌሎች ጎብኚዎች ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታዎችን ሲፈጥር ቆይቷል ብለዋል። የአማራ ክልል በተፈጥሮ ሀብት፣ በታሪካዊ ቅርሶች፣ በሃይማኖታዊ ትውፊቶች፣ በባሕላዊና መንፈሳዊ ትውፊቶች የበለጸገ መሆኑን አቶ ኤርምያስ አስረድተዋል።
የአማራ ክልል በመልክዓ ምድር አቀማመጡ በራሱ የቱሪዝም መስህብ መሆኑን ነው የገለፁት። በመሆኑም ጎብኚዎች በክልሉ መስህብ እንዲዝናኑ፣ እንዲጎበኙ እና መውሰድ የሚገባቸውን እውቀት እንዲወስዱ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል። ቢሮው የክልሉን መስህብ በማስተዋወቅ ተጠቃሚ ለመሆን ታኅሣሥ፣ ጥር እና የካቲት ወራትን መርጦ በነዚህ ወራት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ምክትል ኀላፊው መጪውን የክርስቶስ የልደት በዓል በላል ይበላ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት መደረጉንም ነው ያስረዱት። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በላልይበላ ከተማ ላይ ውድመት ቢፈጽምም መንግሥት ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር የአውሮፕላን በረራን የማመቻቸት፣ የመብራት፣ የውኃ፣ የመንገድ እና የሆቴሎች አገልግሎት የተሟላ እንዲሆን ማድረጉን ገልጸዋል።
ማንኛውም ተጓዥ በመሰረተ ልማት ምክንያት እንግልት እንደማይደርስበትም አቶ ኤርምያስ አረጋግጠዋል። መንፈሳዊ ተጓዦችም እንደተለመደው ጉዧቸውን ወደ ላልይበላ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በጥር 7/2014 ዓ.ም በደብረ ብርሃን ከተማ የቅድስት ሥላሤ ክብረ በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊት በደመቀ መልኩ እንደሚከበር አቶ ኤርምያስ አስረድተዋል። ሃይማኖታዊ በዓሉ ታላቅ የቱሪዝም ጠቀሜታ እንዳለውም አስገንዝበዋል። በተጨማሪም የጥምቀትን በዓል በጎንደር ከተማ በድምቀት ለማክበር ቅድመ ሁኔታዎች ተመቻችቷል ያሉት ምክትል ኀላፊው የጎንደር ከተማ አስተዳደር እንደተለመደው ሁሉ ቅድመ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር ያልተመቻቸው ሰዎች በሰሜን ሸዋ ምንጃር ሸንኮራም በዓሉ በደመቀ መልኩ ስለሚከበር ጎብኚዎች በቦታው መገኘት እንደሚችሉ አስረድተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን የጥምቀት በዓል ከአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ነፃ በሆኑ እንደ ደሴ፣ ወልድያ፣ ሰቆጣ፣ ከሚሴና በሌሎች አካባቢዎችም በዓሉ በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር ቅድመ ሁኔታዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ጎብኚዎች በስፍራው በመገኘት ከወገኖቻቸው ጋር በዓሉን እንዲያሳልፉ ምክትል ኀላፊው ጠይቀዋል።
በመጪው ጥር 13 በዓባይ ወንዝ መነሻ በሰከላ ወረዳ የግዮን በዓል በመገኘት እንዲኹም ጥር 21 በሚከበረው በግሸን ደብረ ከርቤ በዓል ላይ በመገኘት ጎብኚዎች መንፈሳዊ ትውፊቶችን እንዲታደሙ አስገንዝበዋል።
ጎብኚዎች ከጥር 21 እስከ 23 በሚከበረው የአገው ፈረሰኞች በዓል እና በደብረ ታቦር በሚከበረው የመርቆሬዎስ በዓል ላይም እንዲሳተፉ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ መጋበዙን ምክትል ኀላፊው ጠቁመዋል። ቢሮው የጉዞ ማኅበራትን፣ አስጎብኚ ድርጅቶችን እንዲሁም የተለያዩ አጋር አካላትን በማስተባበር እየሠራ መሆኑን አቶ ኤርምያስ አስረድተዋል።
ተጓዦች በሚጓዙበት እና በሚጎበኙበት አካባቢ ሁሉ አስተማማኝ ደኅንነትን ሊያስከብሩ የሚችሉ የጸጥታ አካላት በትኩረት እየሠሩ መሆኑንም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/