ባሕር ዳር እንግዶቿን መቀበል ጀምራለች፡፡

137

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች የሀገራቸውን ጥሪ ተቀብለው መግባት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ አንድ ሚሊየን የሚደርሱ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት ወደ ሀገራቸው ይገባሉ ተብሎ በሚጠበቅበት በዚህ መርኃ ግብር መንግሥት እና ሕዝብ ቤት ያፈራውን አዘጋጅተዋል፡፡ የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ውቢቷ ባሕር ዳርም ቅድመ ዝግጅቶቿን አጠናቃ እንግዶቿን እየጠበቀች ነው ተብሏል፡፡

መርኃ ግብሩ ባለፉት ሦስት ዓመታት የኮሮናቫይረስ ሥርጭት እና አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የፈጸመው ወረራ በተለይም የከተማዋ ምጣኔ ሃብታዊ አንቀሳቃሽ የነበረውን ቱሪዝም በእጅጉ አቀዛቅዞት ከርሟል፡፡ አንድ ሚሊየን ኢትዮጵያዊ ወደ ሀገር ቤት መርኃ ግብር የተጎዳውን የቱሪዝም ዘርፍ ያነቃቃዋል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ የሚመጡ እንግዶቿ በቆይታቸው መልካም ጊዜን እንዲያሳልፉ እና ስለሀገራቸው እና ክልላቸው እንዲመክሩ የተለያዩ ዝግጅቶችን አዘጋጅታለች፡፡ ከዝግጅቶቹ መካከል አንዱ በቤዛዊት ቤተ መንግሥት ለእንግዶቹ የሚኖረው የንጉሥ እራት መርኃ ግብር አንዱ ነው፡፡

ወደ ንጉሥ እራቱ መርኃ ግብር ከማምራታችን በፊት ግን ስለቤዛዊት ቤተ መንግሥት እና ባሕር ዳር አጭር መግቢያ እናንሳ፡፡

ወደ ክልሉ ርዕሰ መዲና ባሕር ዳር ጎራ ያለ ሁሉ የከተማውን ከፊል ገፅታ ከምድር ላይ ሆኖ ማየት ቢያሻው ቤዛዊት ግንባር ቀደም እና ተመራጭ ቦታ ነው፡፡ የከተማዋ የውበቷ ድምቀት፣ የጌጧ ፈርጥ የሆኑት ዓባይ እና ጣና አብሮነታቸውን አዋህደው ዓባይ በጣና ላይ ሲነጉድ ለማስተዋልም ቤዛዊት ልዩ ስፍራ ነው፡፡

ቤዛዊት የከተማዋ ከፍታ ብቻ አይደለም፡፡ ቤዛዊት ባሕር ዳርን “ቤት ለእንቦሳ” ላሏት እንግዶች “እምቦሳ እሰሩ” ያለችበት አድባር፤ ነገሥታት እና መኳንንት ግብር ያበሉበት ደብር፤ ስዩመ መንግሥት እና የጎጃም ታሪካዊ ስፍራ- ቤዛዊት ቤተ መንግሥት፡፡

ኢትዮጵያን ከአራት አስርት ዓመታት በላይ የመሯት ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ጃንሆይ) በጎጃም ቤተ መሥግስት ይኖራቸው ዘንድ ይፈልጉ ነበር፡፡ ጃንሆይ በወቅቱ የባሕር ዳር አውራጃ አስተዳዳሪ ለነበሩት ፊታውራሪ ኃብተማሪያም ወልደ ኪዳን ለቤተ መንግሥት የሚሆን ቦታ እንዲመርጡ ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡ ዋና አስተዳዳሪው ፊታውራሪም አስፈልገውና አፈላልገው የቤዛዊት ኮረብታማ ቦታን የቤተ መንግሥት መቀመጫ ይሆን ዘንድ ለንጉሡ መረጡላቸው፡፡ ቤዛዊት በንጉሠ ነገሥቱ በጎ ፈቃድ ለቤተ መንግሥት መቀመጫነት ታጨች፡፡

ወቅቱ የካቲት 10/1958 ዓ.ም. የያኔው የፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርቲያን ያሁኑ የፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል እና የቤዛዊት ቤተ መንግሥት ግንባታ በንጉሠ ነገሥቱ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠላቸው፡፡ የቤዛዊት ቤተ መንግሥት ግንባታ ወዲያውኑ ተጀምሮ ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ በ1960 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተመርቆ ሥራ ጀመረ፡፡

ከንጉሡ መውረድ በኋላ የተተኩት ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ወደ ቤዛዊት ቤተ መንግሥት በርካታ ጊዜ ያቀኑ እንደነበር ይነገራል፡፡ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ተዘግቶ የኖረው ታሪካዊው ቤተ መንግሥት እንግዶቹን ተቀብሎ የንጉሥ እራት ይበላበታል ተብሏል፡፡ ከሕዝብ የራቀውን እና ተዘግቶ ዘመናት ያለፈውን ቤተ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ለማገናኘት መልካም አጋጣሚ መሆኑ ነው፡፡

ከታኅሣሥ 25/2014 ዓ.ም እስከ ጥር 13/2014 ዓ.ም በሚኖረው ይፋዊ መርኃ ግብር ወደ አማራ ክልል ከግማሽ ሚሊየን በላይ እንግዶች ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ያሉት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ በትግሉ ተስፋሁን ናቸው፡፡ አቶ በትግሉ ተስፋሁን 400 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ባሕር ዳርን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ ይህን ታሳቢ ያደረገ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ነው የተናገሩት፡፡

ለእንግዶች “የእንኳን ደህና መጣችሁ” መርኃ ግብርን ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነውም ብለዋል፡፡ እንግዶቹ በተለይም ከጥር 1/2014 ዓ.ም ጀምሮ በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ መርኃ ግብሮች ቆይታ እንደሚያደርጉ የገለጹት አቶ በትግሉ ከተማ አስተዳደሩ ጥር 3/2014 ዓ.ም በቤዛዊት ቤተ መንግሥት የንጉሥ እራት ግብዣ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡ ይህም ለዘመናት ተዘግቶ የቆየውን የቤዛዊት ቤተ መንግሥት ለሕዝብ እና ለጎብኝዎች ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

እንግዶች በቆይታቸው የኢትዮጵያን እውነት ለቀሪው ዓለም የሚገልጡበት የዲፕሎማሲ እውነት ከማግኘታቸውም በላይ ላለፉት ሦስት ዓመታት የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አጋራው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article“ይሕ የወለድሽው ልጅ አድጎ ነገ እኛን ነው የሚያጠፋው ብለው ገደሉት” ልጇን በአሸባሪው ቡድን ያጣችው እናት
Next article“የተፈናቀሉትን የመመለስና የመቋቋም ሥራ በከፍተኛ ርብርብ እየተሠራ ነው” አቶ ስዩም መኮንን