❝የማይዝሉ ክንዶች፣ የማይደክሙ ጀግኖች❞

296

ታኅሣሥ 25/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሚዘናጠፈው ቁመናቸው፣ ልብ የሚያስደነግጠው ጎፈሬያቸው፣ በእውቅ የተሠራው ጥርቅ ጫማቸው፣ በገላቸው ላይ በውበት የሚወርደው ጎሚሷቸው፣ በትክሻቸው ላይ ስትሞናሞን የምትውለው መውዜራቸው እና ክላሻቸው፣ ተሰምቶ የማይጠገበው ለዛቸው፣ አሳስሮ የሚያስቀረው ፍቅራቸው፣ ወገን የሚያኮራው ጀግንነታቸው ፣ አልሞ ተኳሽነታቸው፣ ለጠላት አትንኩኝ ባይነታቸው ሁሉም ነገር ይናፍቃል። ውል ይላል።

ከአፈሩ ይሁን ከውኃው ንግግር አዋቂ፣ ሀገርና ወገን ጠባቂ ይወለድበታል። ጀግኖች ይፈልቁበታል። ወይዛዝርት ይገኙበታል፣ ጀግና እየወለዱ ጀግና ያሳድጉበታል፤ መልከ መልካም፣ መልከ ቀና፣ ኩሩ ደፋር ቆራጥ ጀግና በሀገሩ ሞልቷል። ቢሻቸው ለፍቅር፣ ካሻቸው ለጦር ተክነውበታል። ለወደዱት ማርና ወተት፣ ጠጅና ጠላ፣ ነጭ ጤፍ እንጀራ በእርጎ ያቀርባሉ፤ ጮማ ይቆርጣሉ፤ በሞቴ እያሉ ያጎርሳሉ፤ ያለብሳሉ፤ ያጠጣሉ። ሰው በልቶ የጠገበ አይመስላቸውም፤ እንግዳ አቀባበል ፣ ሰው አከባበር ያውቁበታል። ፍቅራቸው በዘመን አይሻርም፤ በምንም አይቀየርም፤ ከወደዱ ወደዱ ነው።

ደግነት፣ ጀግንነት፣ አርቆ አሳቢነት መገለጫቸው ነው። ሲወዱት ለሚጠላቸው፣ ሲያከብሩት ለሚገፋቸው፣ ሲደግፉት ለሚነቅፋቸው፣ በክብራቸው፣ በሀገራቸው፣ በርስታቸው ለሚመጣ ደግሞ ቆራጥ አሞት አላቸው፤ በጮማ ፋንታ ጥይት ይሰጡታል፤ በወተት ፋንታ ባሩድ ያጠጡታል፤ ዓልመው ይመቱታል፤ ልኩን ያሳዩታል። በሀገር ድርድር የለም፤ ድርድር አያውቁም፤ ጠላት ሀገርን ከደፈረ፣ ወንዙን ከተሻገረ፣ በአንድነት ተነስተው ወደ ጠላት ሠፈር ይደርሳሉ። በአንድነት ይተኩሳሉ፤ በአንድነት ይመታሉ፤ በአንድነት ይጥላሉ፤ በአንድነት ድል ያደርጋሉ። በጦር ሜዳ ጀብዱ ኮርተው ሀገር ያኮራሉ፤ ታሪክ ይሠራሉ።

ራያዎች ሀገርን፣ ቀዬን ለሚያረክስ፣ ክብር ለሚጥስ ሰላቶ ትዕግሥት የላቸውም። ራያ ወርቄ ያያ ውስጥ ነኝ። ወርቄዎች ጠላት በአራቱም ንፍቅ ከቧቸው፣ በአራቱም ንፍቅ ተዋግተው፣ በአራቱም ንፍቅ ተታኩሰው፣ በአራቱም ንፍቅ ጠላትን ደምስሰው፣ በምሽግ ውለው በምሽግ አድረው ቀያቸውን ሳያስደፈሩ በእንቢተኝነት ፀንተዋል። በማይዝሉ ክንዶች፣ በማይደክሙ ጀግኖች፣ በማይስቱ አፈሙዞች፣ በማይስቱ ተኳሾች የወርቄ ተራራዎች ተከብረው፣ ለጠላት እሳት ኾነው ጠላትን አቃጥለዋል።

የወርቄ ተራራዎችን አልፎ በሰላም የሚገባ እንግዳ እንጂ ባንዳ አይደለም። ከባድ መሳሪያ የታጠቀ፣ በመንጋ ተዋጊ የላከ ጠላት የወርቄዎችን ምሽግ መሥበር አልቻለም። ከወርቄዎች አፈሙዝ አላመለጠም። በወርቄዎች አፈሙዝ እየተለቀመ አለቀ፤ በክንዳቸው ደቀቀ እንጂ። ወርቄ በቅርብ የሚያያት፣ በጉዞ የማይደርስባት፣ በሰፊው የከጀላት፣ ነገር ግን ያልነካት፣ ተመኝቷት የቀረች የጀግኖች ሥፍራ ናት። ወርቄዎች ለወራት በዘለቀ ውጊያ በአራቱም ንፍቅ ብርቱ ትግል አድርገዋል። በብርቱው ተዋግተዋል። በብርቱው ጠላትን ድባቅ መትተዋል። ቀያቸውን አስከብረዋል።

“የጩቤያቸው እንኳን አለው ሚዶ ሚዶ፣ አስለምደውታል የታፋ ብርንዶ፤” እንዳለ ዘፋኙ የጩቤያቸው ሚዶ አለው፤ የጠመንጃቸው ውበት፣ ጌጥ፣ የደስደስ አለው። በአሻገር ሲያዩት ያበራል። በአሻገር ሲያዩት ያስደስታል። በአሻገር ሲያዩት ያስጎመዣል። ትጥቅ አሳማሪዎች፣ በኩራት ኗሪዎች ናቸው።

ወርቄ ሲነሳ ጀግንነት አብሮ ይነሳል። አሸናፊነት ይታወሳል። ባለሽርጦቹ ወርቄዎች ጀግንነታቸው ግሩም ነው። በዚህ ምድር የሚኖሩ፣ ጀግና ሕዝብ የሚመሩ ፣ በጀግንነታቸው የተከበሩ፣ ልበ ሙሉ ጀግና ሰው አሉ። ይማም መሐመድ ይባላሉ። የወርቄ ያያ ቀበሌ አስተዳዳሪ ናቸው። ከሚመሩት ሕዝብ ጋር ወዳጅነት አላቸው ይሏቸዋል። በተለይም ጦረኞች እና ጀግኖች አብዝተው ይወዷቸዋል። እኒህ ጀግና ከሌላኛው የወርቄ ቀበሌ አስተዳዳሪ በካሪስ ጎቤ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት አላቸው። ጠላት ወረራ በፈፀመ ጊዜ ታዲያ ሁሉ ጀግኖች በጋራ ይመክራሉ፤ ሀገራችን አናስደፍርም፣ ቀያችንን አናስረግጥም በጀግንነት መዋጋት አለብን። ለዚህ ደግሞ ጀግናው ሕዝባችንን ማነሳሳት አለብን በማለት ይመካከራሉ። በምክራቸው ፀንተው ለሕዝባቸው አሳወቁ። ድሮም ጥቃት የማይወደው የወርቄ ሕዝብ እሺ ብሎ በአንድነት ተነሳ።

ይማም የወርቄ ያያ ጀግኖችን ይዘው፣ በጀግንነት አዋጉ ተዋጉ፤ ድልም አደረጉ። ይማም ያን ጊዜ ሲያስታውሱት “ጠላት ወረራ ፈፅሞ ሚስት ይደፍራል፣ ልጆችን ያሰቃያል፣ በሬ ያርዳል፤ ይህን አስቀድመን ሰማን፤ ወጣቱን ሰበሰብን፤ አደረጃጀት ሠራን፤ በጋራ አደረግነው አካባቢውን ማስጠበቅ ጀመርን። ጠላት ማጥቃት ጀመረ፤ በአንድነት ተዋጋነው፤ ለጠላት አልቀመስ አልን” የወርቄ ያያ ጀግኖች በእልህ መዋጋታቸውን ቀጠሉ። ጠላትም በየጊዜው እየተመታ ተመለሰ። “ቀበሌያችን ዙሪያዋን ምሽግ አላት። አካባቢያችን አልተደፈረም። ጠላት እየሸሸ ሲሄድ ሮቢት ላይ የጠላትን ኃይል በመደምሰስ ከጠላት መሳሪያና መኪና ማርኳል” ነው ያሉት ይማም።

ጀግኖቹ ቀያችንን አናስደፍርም፤ መሳሪያችንን ለጠላት አንሰጥም ብለው መዋጋታቸውንም ነግረውናል። ለረጅም ሰዓታት በእግር እየተጓዙ ጥይት እያመጡ በጀግንነት መዋጋታቸውንም ያስታውሳሉ። በወርቄዎች ዘንድ ያለ ምክንያት ጥይት አይተኮስም። ጥይት የሚተኮሰው ወደ ጠላት ብቻ ነበር። መግባቢያቸውም ጥይት ብቻ እንደነበር ነው የሚናገሩት። የወጣቶች ጀግንነት እልህና ወኔ መቼም ቢሆን እንደማይረሳቸው ይማም ነግረውናል። ሁለቱ ቀበሌዎች ተመካክረው ግንባር ፈጥረው በመዋጋት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማስፋታቸውንም ይማም ያስታውሳሉ። ቀስ በቀስ ራያን በማነቃነቅ በሁሉም የራያ አካባቢዎች የሽምቅ ውጊያ እንዲደረግ የገባው ጠላት እንዳይወጣ የማድረግ ሥራ መሥራታቸውንም እንዲሁ። የወርቄ ወጣት ለሀገር ተምሳሌት ኾኗልም ነው ያሉን። አቋማችን የትግል አድማሳችንን እያሰፋንና ጠላትን መደምሰስ ነበርም ብለዋል። ለወራት በዘለቀው ጦርነት ሀገር የሚታደግ ጀግና ተዋጊ መፍጠራቸውንም ነግረውናል።

አማራ ሩህሩህ የኾነ ሕዝብ ነው፤ በጀግንነትም አይደፈርም ነው ያሉት። አማራ በኢትዮጵያዊነት የታመነ ኩሩ ሕዝብ መሆኑንም ይማም ያሥረዳሉ። ወጣቱ የምንለውን ይሰማል፤ ያከብረናል፤ ኅልውናውን ለመጠበቅ የተዘጋጀ ኃይል ነውም ይላሉ ይማም። በመስማማታችን እና በአንድነታችን ድል አምጥተናል ብለዋል። ወደኋላ የማይመለስ ኃይል አፍርተናል፤ ጦራቸው ተነስ ሲሉት የሚነሳ ጀግና እንደሆነም ነው የገለጹት። ከጠላት ጋር መተናነቅ እንጂ አካባቢን ጥሎ መሸሽ ነውር መሆኑንም ይማም ነግረውናል። ወርቄን ጠላት በፍጹም አይረግጣትም፤ ከመሳሪያችን የሚወጣውን እሳት ጠላት እንዴት ሊቋቋም ይችላል? ሲሉም ጀግናው ይማም ይጠይቃሉ። የወርቄዎች መሣሪያ ጠላትን የሚያቃጥል እንጂ ለጠላት የሚሰጥ አይደለምና። ሽፍታና ወንበዴ ንብረታችንን አይነካትም፤ ቀያችንን አያረክሳትም፤ እኛ የምንናገረው ለሀቂቃ (ለእውነት) ነው ይላሉ ይማም።

ለወራት ሲዋጉ በመልዕክተኛ፣ በጥይት ተኩስ፣ እና በሌሎች መገናኛዎች እየተገናኙ ግፋ በለው እያሉ እየተዋጉ ጠላትን አሳፈሩ። “የምልክቱ ጥይት ከተተኮሰ እየበላንም ቢሆን ማዕድ አቋርጠን እንነሳለን፤ አንዴ ቆርሰን ሁለተኛ አንደግምም፤ አካባቢያችን ከጥንት ከጠዋት ጀምሮ ስመጥር ነው፤ ራያን ረግጦ መሄድ የለም። ራያን የረገጠ እንጂ ከራያ የወጣ ጠላት የለም፤ ጠላት ረግፏል፤ በየጥጋጥጉ ቀርቷል፤ የእኛ ዓላማችን ለወርቄ ብቻ ሳይሆን ለአማራ ክልል የሚሆን ጀግና ወጣት መፍጠር ነው፤ ይህን ያየ ወጣት ወደኋላ አይልም፤” ነው ያሉት ይማም።

ጀግናው ይማም የወርቄ ልጅ የጎፈሬውን ማሳመሪያ ሚዶ ወይንም ማበጠሪያ ተክሎ በዒላማ የሚመታ፤ ቀለህ የማይስት ነውም ይላሉ። በወርቄ ጀግኖች የተደመሰሰው የአሸባሪው ትግራይ ወራሪ ቡድን ሁሉም የተመታው ከአንገቱ በላይ ነውም ሲሉ የወርቄን ጀግንነት ይማም ይናገራሉ። በወኔ የተነሱት ጀግኖች በሁሉም አቅጣጫ ተዋግተው፣ ረሃብና ጥሙን ታግሰው ያልተደፈረች ቀዬ እንድትኖራቸው አድርገዋል። ጀግንነት፣ ቁርጠኝነት፣ አንድነት የእነሱ መመሪያዎች ነበሩ። ጠላት ያፈረባት፣ በየጎራው ወድቆ የቀረባት፣ ጀግኖች የሚፈልቁባት ወርቄ ያያ።

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous article❝ሀገራችን የገጠማትን የኅልውና አደጋ በተሟላ ድል የምታጠናቅቀው በጦርነቱ የነበሩ ጥንካሬዎችን በማጎልበት የሚስተዋሉ መዛነፎችን በማረም ነው❞ አቶ አብርሃም አለኸኝ
Next article“ይሕ የወለድሽው ልጅ አድጎ ነገ እኛን ነው የሚያጠፋው ብለው ገደሉት” ልጇን በአሸባሪው ቡድን ያጣችው እናት