
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የአማራ እና አፋር ክልሎችን በመውረር ኢትዮጵያን ለመበተን የቻለውን ጥረት አድርጓል። የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን የማፍረስ እና ኢትዮጵያዊያንን የመበተን ዓላማው ባይሳካም በወረራ በደረሱባቸው አካባቢዎች ዘርፈ ብዙ ውድመቶችን አድርሷል።
በወረራው የደረሰውን ዘርፈ ብዙ ክፍተት ለመሙላት እና የተፈጠሩትን ስብራቶች በፍጥነት ለማከም ያለመ የከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የምክክር መድረክ ለሦስት ቀናት በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። የምክክር መድረኩ ትናንት ሲጠናቀቅ የምክክር መድረኩን ዓላማ እና የጋራ ድምዳሜ አስመልክቶ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የሽብር ቡድኑ ወረራ ሲጀምር ዓላማው ከተቻለ ኢትዮጵያን መበተን ካልቻለ ደግሞ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥ የአማራን ሕዝብ በማዋረድ አንገት ማስደፋት ነበር ያሉት አቶ ግርማ ዓላማው በአማራ ሕዝብ እና በኢትዮጵያዊያን የላቀ ተሳትፎ ተኮላሽቷል ብለዋል። በጦርነቱ ኢትዮጵያ አሸንፋለች ሲባል ጦርነቱ ተጠናቋል ማለት አይደለም ያሉት የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኅላፊው የምክክር መድረኩም ዓላማ አመራሩን እና ሕዝቡን ለቀጣይ ድል ማብቃት ነው ብለዋል።
“በጦርነቱ የተገኘውን ድል ለላቀ እና ዘላቂ ውጤት መሸጋገሪያ ለማድረግ ድሉን በአግባቡ መጠበቅ ያስፈልጋል” ያሉት አቶ ግርማ ለዚህም የተስተዋሉ መዛነፎችን ማረም ለነገ የማይባል ተግባር ነው ብለዋል። ክፉ እና አፍራሽ ሃሳቦች ለማደግ ጊዜ ስለማይፈጅባቸው እየተከታተሉ ማረም የአስፈፃሚው አካል ሚና መሆኑንም አቶ ግርማ ጠቁመዋል።
ዳግም የማይደፈር ጠንካራ ሀገር የመገንባት ሂደት የላቀ ርብርብ ይጠይቃል፤ ሕዝቡን መሠረት ያደረገ የጋራ ርብርብ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኘው አመራር ከሕዝቡ ጋር መወያየት እና የጋራ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል። ለዚህም የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያዊያን በጦርነቱ ያሳዩትን የጋራ ተሳትፎ በመልሶ ግንባታው እንዲደግሙት ማድረግ፣ የተጎዱ የመሠረተ ልማት አውታሮችን መልሶ መገንባት፣ መስዋእትነት የከፈሉ ጀግኖች ቤተሰቦች መደገፍ፣ እውቅና መስጠት እና ጠንካራ የመከላከያ ኃይል መገንባት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸውንም አቶ ግርማ ገልጸዋል።
በምክክር መድረኩ በርካታ ሀገራዊ እና ክልላዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት እንደተደረገባቸው አቶ ግርማ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/