
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከተለያዩ ምሁራን፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችና ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር የክልሉ ገቢ አሰባሰብ በሚሻሻልበትና
በሚያድግበት ሁኔታ ላይ በባሕር ዳር መክሯል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶክተር) የልማት ፋላጎትን ለማሟላትና መንግሥታዊ አገልግሎትን ለማሳደግ የገቢ ተቋም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። በክልሉ የገቢ አሰባሰብ ሂደት ዝቅተኛ መኾኑን ያመላከቱት ርእሰ መሥተዳድሩ ችግሩን ለመቅረፍ ሪፎርም ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት። ዶክተር ይልቃል የክልሉን ሕዝብ የልማት ፍላጎት ለማሟላት የገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ሊጠና እንደሚገባ ገልጸዋል። ነጋዴው የሚከፍለው ግብር ለሀገር ልማትና ለሀገር ደኅንነት መኾኑን አውቆ ግብሩን በወቅቱ መክፈል ይጠበቅበታልም ብለዋል። የገቢ ተቋም ባለሙያዎች በተቀመጠው ጥናት መሰረት ገቢን ለማሰባሰብ ሌት ከቀን መሥራት እንዳለባቸውም ዶከተር ይልቃል አስገንዝበዋል።
ከአማራ ኢኮኖሚ ሽግግር ማእከል አቤሴሎም መለሰ በአማራ ክልል የተሻለ ግብር ሊከፍል የሚችል የሥራ ተቋራጭ መኖር አለበት ብለዋል። የተበታተኑ የልማት ድርጅቶ ወደ አንድ ተቋም መጠቃለል እንደሚኖርባቸውም አመላክተዋል። የክልሉ መንግሥት በርካታ ባለሀብቶችን ማፍራት እንዳለበትም ነው አቶ አቤሴሎም የጠቆሙት።
ባለሀብት በላይነህ ክንዴ ነጋዴው በሚገባ መሥራት አለበት በሠራው ልክ ደግሞ ግብሩን መክፈል አለበት ብለዋል። የገቢ ተቋማት ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጉ ማስገባት አለባቸውም ነው ያሉት። ክልሉ በኢኮኖሚ ብቻ ሳይኾን በፖለቲካውም እድገት ማሳየት እንዳለበት ጠቁመዋል። ሀገሪቱ ኹለንተናዊ እድገት እንዲኖራት በኹሉም አካባቢ በተደጋጋሚ ውይይት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የክልሉን ገቢዎች ቢሮ ስትራቴጂክ እቅድ መነሻ በማድረግ ተቋሙ ሊጓዝበት የሚገባውን ፍኖተ ካርታውን አስቀምጧል። ፍኖተ ካርታዉን ያቀረቡት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግና ፋይናንስ መምህር ለጤናህ እጅጉ (ዶክተር) የክልሉ የበጀት ሽፋን የሕዝቡን የልማት ፍላጎት መሰረተ ያደረገ መኾን አለበት ብለዋል። በጀቱ የክልሉን ሕዝብ ችግር የሚፈታ መኾን እንዳለበት ነው ምሁሩ ባቀረቡት ፍኖተ ካርታ የጠቆሙት። በመኾኑም ክልሉ የገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ እንዳለበት መክረዋል። የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አሁን ያለበትን ቁመና፣ ወደ የት መሄድ እንዳለበትና የክልሉን በጀት ማሳደግ በሚያስችልበት ሁኔታ ላይ የተዘጋጀ መኾኑ ዶክተር ለጤና ጠቁመዋል።
የገቢ ተቋማት የተጠናከረ የቅንጅት ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ምሁሩ አሳስበዋል። የገቢ ተቋማት የተሻለ ሥራ ለመሥራት አሠራራቸውን ማዘመን ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል። የገቢ ተቋማት የነጋዴዎችን የግብር አከፋፈል ባሕሪያት መለየት እንዳለባቸው የቀረበው ፍኖተ ካርታ ይጠቁማል። የገቢ ተቋማት ወደ ነጋዴዎች መቅረብ፣ ግንዛቤ መስጠት እንዳለባቸውና ከፍተኛ የግብር ከፋዮች የተለየ መስተንግዶ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ምሑሩ መክረዋል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ፀጋ ጥበቡ (ዶክተር) በተቻለ መጠን ኹሉም ዜጋ ክልሉን ለማሳደግ መሥራት አለበት ብለዋል። የተቋማቸውን ሥራ ለማዘመን በቴክኖሎጂው ብቁ የኾኑ ባለሙያዎች ጋር እየሠሩ መኾናቸውም ጠቁመዋል። ኹሉም ዜጋ ለሚሸምተው ቁሳቁስ ደረሰኝ መጠየቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ዋና ሥራ አስፈፃሚ መላኩ ፋንታ ኹሉም አመራር የድህነት መውጫን በማሰብ ለገቢ አሰባሰብ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል። ገቢን ለመሰብሰብ ከተለመደ አሠራር መውጣት እንደሚያስፈልግ አቶ መላኩ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/