
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አትጠገብ ዳብሳ ያሳደገችው፣ ተዋበች የሠራቸው፣ ሥሬቱን ያሳመረችው፣ ካሳ የተዋበበት፣ መይሳው ያጌጠበት፣ ተስፋውን እና ራዕዩን የቋጠረበት ውብ ሹርባ፤ እሜቴ አትጠገብ በካሳ ሹርባ ላይ አደራ አስቀምጣለች፤ ኢትዮጵያ ትፀና ዘንድ ለልጇ ከቁንዳላው ጋር ቃል ኪዳን አሥራለች፤ ተዋበች በመይሳው ቁንዳላ ላይ ራዕይ ዐይታለች፤ አንድነት ተመልክታለች፤ ታላቅ ሀገር ዓልማለች፤ መይሳው የሐር ነዶ በሚመስለው ቁንዳለው የአንድነት ምስጢር አስሮበታል፤ የጀግንነት ልክ ሸርቦበታል፤ ራዕይ ተሠርቶበታል። አሸናፊነት ጎንጉኖበታል።
በካሳ ቁንዳላ ዱር አይበቃንም ያሉት ሽፍቶች ደንግጠዋል፤ ጥቅጥቅ ባለው ጫካ የሚኖሩት ባለ ቁንዳላውን ሲያዩ ደንብረዋል፤ ጫካው ሜዳ ኾኖባቸዋል። መጠጊያ ጠፍቶባቸዋል። ካሳ የገባባቸው ጫካዎች ተጨንቀዋል። ባለ ቁንዳላው በዘመኑ ከነበሩት ጀግኖች ሁሉ የተለየ ነበርና ሁሉም ፈሩት። እረኞች ከከብቶቻቸው ኋላ ለኋላ እየተከተሉ፣ በዋሽንታቸው ቅኝት እየቃኙ፣ ስለሚነሳው ንጉሥ ትንቢት ይናገሩ ጀመረዋል፤ የእረኞችን ትንቢት የሚሰሙት መሳፍንቱና መኳንንቱ ስጋት ገብቷቸዋል። ዓለም አጫዋቾቹም በማሲንቆአቸው እያዋዙ ሁሉንም አስተካክሎ፣ ሀገር አንድ ስለሚያደርገው ንጉሥ ይተነብያሉ፤ መኳንንቱና መሳፍንቱን በቅኔ ይሸነቁጣሉ፤ የገባቸው መስፍኖች ትንቢቱን በትዕግስት ለመጠበቅ ሞከሩ፤ አንዳንዶችም በእረኞችና በዓለም አጫዎቾች ትንቢት ያፌዛሉ፤ ሌሎችም ትንቢቱ የማይፈፀምበትን መንገድ ይቀይሳሉ፤ ስልት ይነድፋሉ። አባቶችና እናቶችም በጀግንነት የእረኞች ትንቢት እንደሚደርስ ጠብቀዋል።
በቁንዳላው ውስጥ አንድነት፣ በቁንዳላው ውስጥ ጀግንነት፣ በቁንዳላው ውስጥ ኢትዮጵያዊነት፣ በቁንዳላው ውስጥ ዘመናትን አሻግሮ የሚያይ ብልሀት፣ በቁንዳላው ውስጥ የሀገር ፍቅር፣ በቁንዳላው ውስጥ የሀገር ክብር፣ በቁንዳለው ውስጥ የአሸናፊነት ምስጢር፣ በቁንዳው ውስጥ የፀናች ሀገር አለች።
መሣፍንቱና መኳንንቱ በርክተው፣ ወሰን ለክተው፣ ግብር እያስገበሩ፣ ጭሰኛውን እያስፈራሩ ይኖሩ ነበር። የነገሥታቱ አቅም ተዳክሟል፤ አንድነት ላልቷል፤ ጉልበታሙና ጦር አዝማቹ ሁሉ በርትቶ፣ አንደኛው ከሌላኛው ልቆ ለመገኘት ጦርነት በርትቶ ነበር። የመሳፍንቱና የመኳንንቱን አለመስማማት፣ የነገሥታቱንም መዳከም ያዩት የውጭ ጠላቶች ባሕር እየከፈሉ፣ የብስ እያቋረጡ ኢትዮጵያን ሊወሯት፣ ሊደፍሯት ገሰገሱ። የመሳፍንቱና የመኳንንቱ የሽኩቻው መብዛት ደግሞ ገበሬው አርሶና ቆፍሮ እንዳይበላ፣ ነጋዴው በበረሃ ተንገላቶ፣ በረሃብና በጥም ተቀጥቶ ነግዶ እንዳያተርፍ አድርጎታል። ቀዬውን የረገጠው መስፍን ሁሉ ገብር እያለ አሳሩን አብዝቶበታል። ከላይ ኾኖ አንተም ተው አንተም ተው የሚል ጠንካራ መሪ ጠፍቶ ሁሉም በየፊውና ክንዱን ያነሳ ነበር። ብቻ በዚያ ዘመን ብርቱ ሰው ተፈልጓል። መልካሙ ገበሬ ያለ ስጋት እንዲያርስ፣ በሰፊ አውድማ እንዲያፍስ፣ እንግዳ እንዲቀበል፣ ወተትና ማር በቤቱ እንዲበዛ ፈጣሪው መልካም ሰው ይጥልለት ዘንድ መማፀን ላይ ነው።
ዙፋን ካረጋ፣ መንግሥት ካልተረጋጋ እንዳሻ ማረስና ማፈስ አይቻልምና። ጌታው ዝናብ ከሰማይ እንደሚያወርድለት፣ ከወፍ አዕላፍ አትርፎ እንደሚያበላው አምኖ ከጎተራው የከረመችውን ዘር ከደረቀ መሬት ላይ የሚበትነው ገበሬ ከመልካም እናቶች ማሕፀን ውስጥ መከራውን የሚያቃልለት አንድ ደገኛ ንጉሥ እንደሚፈጥርለት ተማምኗል። ታቦቱ ከመንበሩ፣ ንጉሡ ከወንበሩ እንዲፀናለት የሚማፀነው ገበሬ ጀንበር በዘለቀች ቁጥር ወደ ሰማይ እያንጋጠጠ በአስፈሪው ዙፋን ላይ አንድ የሚያደርግ፣ የሰቆቃውን ጊዜ የሚቋጭ ንጉሥ እንዲሠጠው እየለመነ ነው። አንድነት እንጂ መለያየት የማያምርበት ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአንድ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ይመራ ዘንድ ልቡ ከጅሏል። መሣፍንቱና መኳንንቱ ግን የተመቻቸው ይመሥላል፤ በየአውራጃው መስፍን እየሆኑ እየተቀመጡ፣ ያሻቸውን እየቀጡ፣ ያሻቸውን እየሸለሙ ግብር እያስገበሩ መኖር ሳይደላቸው አልቀረም።
ጠጅ ማንቆርቆር፣ በሠጋር ፈረስ መብረር፣ ሳይገብሩ ማስገበር ተስማምቷቸዋል። ዘመኑ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የውጭ ጠላቶችም የኢትዮጵያን የውስጥ ሁኔታ እያዩ መቋመጥ ጀመሩ። መሳፍንቱ እና መኳንንቱ እየተከፋፈሉ ከቀጠሉ ሊደፍሯት እና ሊወሯት የሚከጅሉት ብዙዎች ናቸው። ቀን ጠብቆ ከተደበቀበት የሚነሳ ሞልቷልና። ደገኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአስፈሪው ዙፋን ግርማ ሞገስ ያለው ንጉሥ ይቀመጥበት፣ ሀገርንም ያረጋጋበት፣ አንድነት ያመጣበት፣ በዳር በድንበር የከበቡትን ጠላቶች ተስፋ መና ያስቀርበት ዘንድ የዘወትር ፀሎትና ምኞታቸው ነው። ቀን እየጨመረ ዓመት እየቆጠረ ሲሄድ የእረኞችና የዓለም አጫዋቾች ትንቢት ተቃረበ።
የአባቶች እና የእናቶች ፀሎት ተሰማ። ፈጣሪ የጠየቁትን ሰጣቸው። አንድነት የሚያመጣ፣ ሰላቶንና ወንበዴን የሚቀጣ፣ ከጨለማ ዘመን የሚያወጣ፣ ዘመናዊነትን የሚዘምር፣ የሚጀምር፣ ክብርና ፍቅር ያለው ሰው በጎንደር ቋራ ተወለደ። ሀገርና ሕዝብ ይካስ ዘንድ ብልኋ እናቱ ካሳ ስትል ስም አወጣችለች። የፀሎት ምላሽ ልጅ። አትጠገብ መሻገሪያውን ወለደችው፤ የጭንቅ ቀን ስጦታውን ታቀፈችው፤ የማይደፈረውን አዘለችው፤ በክብር እና በፍቅር፣ በራዕይና በተስፋ አሳደገችው። ብላቴናው ከእናቱ እቅፍ ሳይወጣ ገና የእረኞች ትንቢት በረታ፤ ከዘመኑ አስቀድሞ የተወለደውን ልጅ ደጋግመው ጠሩት፤ የመሳፍንቱ ስጋት ጨመረ፤ የትንቢተኛው ንጉሥ ስም በየቦታው ተነገረ። ዘመን ደረሰ፤ እሜቴ አትጠገብ አንድያ ልጇን ቀለም ይቆጥር፣ ምስጢር ይመረምር ዘንድ ለመምህር ሰጠችው። ብላቴናው ብልህ ነበርና በትጋት ቀለም ቆጠረ፤ ዳዊት ደገመ፤ ምስጢር መረመረ። በዘመኑ ላቅ ብሎ መገኘት ይሻላልና እንቅስቃሴዎቹ ሁሉ የተለዩ ነበሩ ይሉታል። በጥበብ አደገ፤ ጥሪው ሀገር ለማፅናት፣ አንድነት ለማምጣት ነበርና የቤተ ክህነቱንና የቤተመንግሥቱን ሥርዓት መረመረ። በሀገሩ ጉልበተኞች በርትተው ደካሞች ሲበደሉ ተመለከተ። ገና በተማሪ ቤት በነበረበት ጊዜ የመሳፍንቱን አካሄድ አስተዋለ።
ካሳም ስንዴ ዛላ መሳይ ሹርባ ተሠርቶ መልካም ስርዓት፣ የጠበቀ አንድነት ሊያመጣ ወደ በረሃ ወረደ። በበረሃው ደፋርና ኩሩ ገብቶበታልና በረሃው ተጨነቀ፤ ባለ ራዕዩ ካሳ ሹርባውን ተሰርቶ፣ ወገቡን አጥብቆ፣ ጃኖውን ለብሶ ከበረሃ በረሃ እየተመላለሰ ሕልሙን ለማሳካት ጥረት ጀመረ። ጀግንነቱን የተመለከቱ ብዙ ጀግኖች ተከተሉት። ማን ነክቶን ሲሉ የነበሩ መሳፍንቱና መኳንንቱ ፈሩት። እርሱ ሕልሙና ዓላማው የአንድ አካባቢ መስፍን ኾኖ መኖር አልነበርም። የእርሱ ሕልም ኢትዮጵያን በአንድነት መግዛት፣ ሀገር ማፅናት፡፡ ወኔ ታጠቀ፤ ለሀገር የማይጠቅሙትን ቀጣቸው። የቋራ በረሃዎች ማደሪያና መክረሚያው ኾኑ። ተከታዮቹ በረከቱ። ከድል ላይ ድል እያገኘ መጣ።
ካሳ ሕልሙን ይኖር ዘንድ የምትረዳው ተዋበችን ከቤተ መንግሥት አስወጥቶ አገባ። እርሷም አስቀድማ ትወደው ሕልሙንም ትደግፈው ነበርና ታጠቅ ግፋበት አለችው። ታጥቆ ተነሳ። ገፋበት። ሀገር ከፋፍለው ግብር እያስገበሩ፣ በሰጋር ፈረስ እየበረሩ ሀገሬውን ይበድሉ የነበሩት መሳፍንቱንና መኳንንቱን ሥርዓት አሲያዛቸው። የካሳ ግዛት እየሰፋ መሳፍንቱም እየተዳከሙ ሄዱ። አያሌ ጦርነቶችን አድርጎ፣ እነ ገብርዬ፣ አለሜና ገልሞ እየተከተሉት የመሳፍንቱን ዘመን ፈፀመው። አስቀድሞ ትንቢት የተነገረለት፣ እረኞች የዘመሩለት፣ ጀግናው ካሳ በደረስጌ ማርያም ንጉሠ ነገሥት ኾኖ ዘውድ ጫነ። ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስም ተባለ። ባለ ግርማ ሞገሱ ንጉሥ።
ጠንካራ ንጉሥ በኢትዮጵያ ላይ ነግሧልና ባሕር ሰንጥቀው፣ የብስ አቋርጠው የመጡት፣ ኢትዮጵያን ለመውረር የቋመጡት ጠላቶች ሁሉ ተደናገጡ። አይቀጡ ቅጣት እንደሚቀጣ ዝናው ናኝቷልና። ብልኋ ባለቤቱ ተዋበችም ከአጠገቡ ኾና ዘውድ ደፋች። ዘመነ መሳፍንት አከተመ። ካሳ ደሀ እንዳይበደል፣ ፍርድ እንዳይጓደል፣ ኢትዮጵያም በስልጣኔ እንድትደላደል ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ኳተነ። የጎንደርን አብያተ መንግሥታት የመሰለ ቅንጡ ቤተመንግሥት እያለ እርሱ ግን በእግሩ እየተመላለሰ፣ በድንኳን ውሎ በድንኳን እያደረ ሀገሩን ያቀና ዘንድ ደከመ። የመከራውን ዘመን ታገለው። ቁጭ ብሎ ግብር ማስገበር የለመዱ የመሳፍንቱና የመኳንንቱ ወገኖች በየሥፍራው ጦር እያስነሱ ሥራውን አበዙበት። ጦርነት በሚበዛበት፣ ጠላት በመላበት ዓለም ውስጥ የጠነከረ ወታደርና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እንደሚያስፈልግ አስቀድሞ ስለተረዳ በጋፋት ኢንዱስትሪ አቋቁሞ የጦር መሳሪያ አሠራ።
ዜጎች በመንገድ ሲተሳሰሩ ሕይወት ቀላል ይሆናልና መንገድም ያስጠርግ ጀመር። በሀገሩ አያሌ ለውጦችን ለማድረግ ሳይሰለች ታተረ። ከዘመኑ አስቀድሞ የሚያልመው ቴዎድሮስ ኋላ ቀሩ ዘመን እተበተበ አላስሄድ አለው። ጠላቶቹ በረከቱበት፤ ወገኔ ያላቸው ከዱት። ጠላት እየጎተቱ አመጡበት። ይባስ ብሎ አብዝቶ የሚወዳት፣ የራዕዩ ደጋፉና ተካፋይ ተዋበች ጥላው ላትመለስ ሞተች። በምታስፈልገው ፈታኝ ወቅት በሞት ተለየችው። ጀግናው ካሳ እንባ አውጥቶ አለቀሰ። ውስጡ ተነካበት። የሐር ነዶ በመሰለው ቁንዳላው ያሰረውን ተስፋ እና ራዕይ ያሳካ ዘንድ ሳይሰለች ታተረ። እርሱ ቀድሞ ሌሎች ዘግይተዋልና እየጎተቱ አላስሄድ አሉት። ዘመን የቀደመው ቴዎድሮስ መከራው ፀናበት። የመጨረሻው ዘመን ቀረበ። ታማኝ የጦር መሪዎችን ይዞ ወደ መቅደላ አምባ ወጣ።
የሀገር ባንዳዎች የውጭ ጠላት እየጎተቱ አመጡበት። የጦርነቱ ዘመን ደረሰ። ተጋጠሙ። እስከሞት የታመነው ቆራጡ የጦር መሪ ገብርዬ ወደቀበት። ያን ጊዜ የቴዎድሮስ ጀንበር አዘቀዘቀች፤ ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ባለ ራዕዩን መሪ ልታጣ ቀረበች። በመቅደላ ብርሃኗን የሰጠችው ጀንበር ጠቋቆረች፤ ጦርነቱ ቀጠለ። እጁ የሚያቃጥለው ጀግናው ቴዎድሮስ በመቅደላ አፋፍ ላይ ተንጎማለለ። ያችን ቀን እንደማያልፋት ተረዳ። እጅ መስጠት የማያውቀው ጀግና ከወገቡ የማትለየውን ሽጉጥ አወጣት። ተመለከታት። ለክብር፣ ለፍቅር፣ ለቃል ኪዳን ሲል ጮማ በጎረሰበት፣ ወተትና ማር በጠጣበት ጉሮሮው ባሩድ ለቀቀበትና ጋደም አለ። የሚወዳቸው ተዋበችና ገበርዬ ወደሄዱት ዓለም አመራ።
ታዲያ በሞቱ ጀግንነት፣ በሞቱ ውስጥ አሸናፊነት፣ በሞቱ ውስጥ አንድነት፣ በሞቱ ውስጥ እምነት፣ በሞቱ ውስጥ ተስፋ፣ በሞቱ ውስጥ ራዕይ፣ በሞቱ ውስጥ ቃል ኪዳን ጥሎ ነበር ያለፈው። እርሱ አለፈ እንጂ ራዕዩ ግን አያልፍም። ሞቶ የማይቀበር፣ ወድቆ የማይሰበር ስም በኢትዮጵያ ላይ ተክሏልና። ሕልሙን የሐር ነዶ በሚመስለው የቁንዳላው ዛላ እንደገመደ፣ የመጨረሻውን ራዕይ ሳያይ ቴዎድሮስ ተሰናበተ።
“አትንኩኝ ብሎ እንጂ ባሩዱን ተጠምቶ፣
መቅደላ ላይ ጠጣው ጎንደር አስቀድቶ” እንደተባለ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ባሩዱን ጠጣው። በዚያ ዘመን ወደ መቅደላ የወጣው የጠላት ጦር በመቅደላ አምባ የነበረውን ሃብትና ንብረት ዘረፈ፤ የተቀደሰውን ሥፍራ አረከሰ። ተስፋ፣ ራዕይ፣ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ አሸናፊነት የተገመደበትን የቴዎድሮስን ቁንዳላ ይዞ ሄደ። ራዕይ ያሠረበት፣ በዘመኑ ሁሉ ያማረበት፣ የተዋበበት፣ ተዋበች የሠራችው፣ አትጠገብ ዳብሳ ያሳደገችው የካሳ ቁንዳላ በጠላት ሀገር ተቀመጠ።
ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የኢትዮጵያ ልጆች የአባታችንን ቁንዳላ መልሱ ብለው ጠየቁ። በመቅደላ አምባ የተዘረፉት መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ይመለሱ፣ በክብራቸውም ይቀመጡ ዘንድ ጠየቁ። የቴዎድሮስ ቁንዳላም ተመለሰ። ይህ አንድነት የተሰራበት፣ ኢትዮጵያዊነት የተጎነጎነበት የቴዎድሮስ ቁንዳላ ሕዝብ ሁሉ ያየው ዘንድ ቴዎድሮስ ወደ ተገኘበት ሀገር መጥቷል። ቁንዳላውን ያዩ ሁሉ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ አርቆ አሳቢነትን፣ ታሪክን፣ የመንፈስ ፅናትን ያዩ ዘንድ ይፈለጋሉና።
ቁንዳላው ያስተሳስራል፣ ቁንዳላው አንድ ያደርጋል፣ ቁንዳላው ያበረታል፣ ቁንዳላው ተስፋ ይሰጣል።
“የመይሳው ሥሬት የካሳ ቁንዳላ፣
የአንድነት ገመድ ነው ውሉ የማይላላ” የእርሱ ስንዴ ዛላ መሳይ ቁንዳላ ውሉ የማይላላ የአንድነት ገመድ ነው። የተስፋና የራዕይ ምልክት ነው። ከቁንዳላው ላይ አንድነት እና ጀግንነት ሠፍሮበታል። አርቆ አሳቢነት አርፎበታል።
የነገሥታቱ ሀገር ጎንደርም የልጇን የንጉሡን ቁንዳላ በክብር ተቀብላ አንድነት ልታሳይበት ነው። ፍቅርና ክብር ልታስተምርበት ነው። ንጉሥ ሆይ ከዘመን ቀድመህ፣ በጥበብ ተቃኝተህ፣ በጀግንነት ተፋልመህ የአንድነት መሠረት እንዲጸና አድርገሃልና ለዘላለም ትከበራለህ።
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/