
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በእናቱ ፍቅር የተለወሰው ኮሶ አሞቱን ብቻ ሳይሆን ፀጉሩንም ዘመን ተሻጋሪ ኮስታራ አድርጎታል። የተዋበች ሚዶ እና ጣቶቿ አሻራቸው ከተዘናፈለው ሽሩባው ላይ አልጠፉም። የጥሩወርቅ ቅቤ ወዙ በዘመናዊው ቅባት አልተቀየረም። ስለሀገሩ የነበረው ተስፋ በጨለመባቸው በእነዚያ የመጨረሻዎቹ ቀናት በእንክብካቤ ያልተዳበሰው ሽሩባ ቀን ዘምበል ሲልበት የነጮች ምላጭ በጀግንነት እና በክብር ከወደቀው አስከሬኑ ተለየ።
“ገደልንም እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው፣ ማረክን እንዳይሉ ሰው የለም በእጃቸው፣
ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ ሀገራቸው?” እንዲል የእኛው ሰው ጠያቂ የኮሶ መድኃኒት ያበረታው ሽሩባ ቀን ሲጥለው ለስስ ምላጭ ተረትቶ ከሩቅ አሳቢ ጭንቅላቱ እና ከብርቱ ክንዱ ተለይቶ ግዳይ የጣሉ ለመሰላቸው የእንግሊዝ ልዑላን ገጸ በረከት ባህር ማዶ ተሻገረ። አብራ መንገድ የጀመረችው ጥሩወርቅ አቅም አጥታ መንገድ ላይ ቀረች። ከአባቱ ሽሩባ ያልተለየ አንድ ሰው ቢኖር ልዑል አለማየሁ ነበር። እርሱም ቢሆን ከአባቱ እቅፍ እና ከወገኖቹ ፍቅር ተለይቶ የጀመረው የሰቀቀን ሕይዎት ብዙ አላኖረውም።
ያለዘመኑ የመጣው ካሳ ያለዘመኑ ሲመለስ አብረውት ክፉ እና ደጉን ያዩት ጥቂት ወዳጆቹ ቀድመውት ስለንጉሳቸው እምነት እና ስለሀገራቸው ፍቅር ሲዋደቁ አይቷል። በሕይዎት ዘመኑ የፈለገውን ሁሉ በኃይል እንጂ በልመና አሳክቶ የማያውቀው ካሳ በሕይዎቱ ፍፃሜ ስለፍቅር ዝቅ ብሎ መለመንን አይቷል። በእለተ አርብ በክርስቶስ የስቅለት እለት የተለየውን የሕይዎት ዘመኑ ምርኩዝ ፊታውራሪ ገብርየን አስከሬን በክብር አልቅሶ ይቀብር ዘንድ የእንግሊዝን ወታደሮች ጠየቀ። ግን ብዙ አልተልመጠመጠም ለልብ ወዳጁ ያለውን ክብር ዝቅ ብሎ ካሳየ ለሀገሩ ያለውን ክብር ቀና ብሎ ማስጠበቅ እንደነበረበትም ያውቃል።
በዘመነ መሳፍንት ተወልዶ የዘመነ መሳፍንት ማርከሻ ፍቱን መድኃኒት የነበረው ካሳ ኃይሉ ስልጣኔን ናፍቆ ሲታትር ቀድመው በሰለጠኑ ኃይሎች ራዕዩን ተነጠቀ። ዘመናዊዋን እና ገናናዋን ኢትዮጵያ ለማዋለድ ለድፍን 17 ዓመታት ያደረገው እልክ አስጨራሽ ትግል ከአንድ አምባ ላይ ተደመደመ። ከቋራ መነሻው እስከ ደረስጌ ማሪያም መናገሻው፤ ከጎንደር የፍትሕ አደባባዩ እስከ ጋፋት የሥልጣኔ መንደሩ የተንሰላሰለው የካሳ ጥረት መቅደላ አምባ ላይ ተደመደመ።
ከ150 ዓመታት በላይ በግዞት በእንግሊዝ ሙዚየም የነበረው ሽሩባ ፀጉር ብቻ አይደለም። ሽሩባው ጥልቅ ሀገራዊ ሚስጥር የተጎነጎኑበት ሕብር ነው። በእያንዳንዷ የፀጉር ዘለላ ለትውልድ የተሻገረ አደራ እና ለሀገር የተከፈለ መከራ አለበት። ከእያንዳንዱ የፀጉር ዘለላ ጀርባ የተደበቀው መከራ ሕብር ፈጥሮ በተዘናፈለው ሽሩባ ሀገራዊ ተስፍ፣ ፍቅር እና አንድነትን ጎንጉኗል።
ኢትዮጵያ ዛሬ በክብር ለሕዝብ እይታ ይፋ የምታደርገው የንጉሷ ሽሩባ አያሌ ፈተና ከፊቷ ለተደቀነባት ሀገር መሻገሪያ መንገዷ የልጆቿ ሕብረት እና አይበገሬነት ብቻ እንደሆነ ማሳያ ነው። ጎንደር ዛሬ በክብር የምትቀበለው የንጉሷ ሽሩባ ቁንዳላ ብቻ ሳይሆን ሕብረ ብሔራዊቷን ኢትዮጵያ የማጽናት እና የመጠበቅ አደራ ተብሲር ነው።
ያ ክንደ ብርቱ ንጉስ ካለፈ አያሌ ዓመታት ተቆጥረዋል። በተናጠል ለመቁጠር የማይቻሉት የፀጉር ዘለላዎቹ፣ በአንጓ በአንጓ የተዋቀሩት ቁንዳላዎቹ እና በሕብረት የጸናው ሽሩባ ግን ያንን የግዞት ዘመን አልፎ ለዚህ ትውልድ እቅፍ በቅቷል። በዘርፈ ብዙ መስዋእትነት ኢትዮጵያን እና ታሪክን ማሻገርም የዚህ ትውልድ እዳ ነው። ከሽሩባው ጋር የምንቀበለው እዳም ይህ ነው።
በታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
