“የሽብር ቡድኑ ወረራ ከፈጠረው ዘርፈ ብዙ ችግሮች በፍጥነት ለመውጣት አመራሩ ቁርጠኛ እና የጋራ ግንዛቤ እንዲይዝ ተደርጓል” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

163

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ላለፉት ሦስት ቀናት ከአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር ሲካሄድ የነበረው የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቋል፡፡ የምክክር መድረኩ ዓላማ ከድል በኋላ የተፈጠሩ መዛነፎችን ለማረም እና በክልሉ ያለውን አመራር ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ ማድረግን ያለመ ነበር፡፡

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኅላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ የምክክር መድረኩ የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የፈጠረውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማረም አቅም የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። በመድረኩ በተፈጠረው የጋራ መግባባት ልክ ወደ ሕዝቡ ወርደው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩም አመራሩ ክልሉ በወረራው ምክንያት በተፈጠሩ መሰረታዊ ክፍተቶች ዙሪያ ተቀራራቢ አቋም ይዟል ብለዋል፡፡

እንደ ሀገር ኢትዮጵያ እንደ ክልል አማራ ከሽብር ቡድኑ ወረራ ጋር በተያያዘ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ ጉዳቶች አጋጥመዋል ያሉት የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳዳር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይትባረክ አወቀ በምክክር መድረኩ ክፍተቶቹ ተነስተው በቂ ውይይት ተደርጎበታል ነው ያሉት፡፡ የተፈጠረውን መሰረታዊ ጉድለት ለማከም ጊዜ የሚሰጥ አይደለም ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በየትኛውም አካባቢ ያለው የክልሉ አመራር ከጉዳቱ ለመውጣት ቀን ከሌት መሥራት እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ይትባረክ አወቀ የሚመሩት የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ሕዝብ ለኅልውና ዘመቻው ሰፊ ንቅናቄ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል። ክልሉ ሙሉ በሙሉ ከጉዳቱ እስኪወጣ ድረስ በመቀራረብ እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል ባይባልም በአጭር ጊዜ ዘመቻ እና ጥረት አመርቂ ድሎች ተመዝግበዋል ያሉት የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኅላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ከቀደመ ድክመቶች መማር እና ጥንካሬን ማስቀጠል ስለሚያስፈልግ አመራሩ ላለፉት ሦስት ቀናት በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ምክክር አካሂዷል ብለዋል፡፡ የአሸባሪው የትግራይ ቡድን ወረራ ዓላማ ከተቻለ ኢትዮጵያን ማፍረስ ካልተቻለ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የአማራን ሕዝብ አንገት ማስደፋት ነበር ያሉት አቶ ግዛቸው ይህ በኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ጥረት እውን አልሆነም ብለዋል፡፡ ነገር ግን ወረራው በርካታ ችግሮቹን ፈጥሮ እንዳለፈ ገልጸው፤ “የሽብር ቡድኑ ወረራ ከፈጠረው ዘርፈ ብዙ ችግሮች በፍጥነት ለመውጣት አመራሩ ቁርጠኛ እና የጋራ ግንዛቤ እንዲይዝ ተደርጓል” ነው ያሉት፡፡

በክልሉ በየትኛውም ደረጃ የመሪነት ሚና ያላቸው አካላት ተመሳሳይ ምክክሮችን በቀጣይ እንደሚደረግ የገለጹት አቶ ግዛቸው አመራሩ በቀጣይ ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ስጋቶች ቀድሞ ለመተንበይ እና የሚመጥን ዝግጅት እንዲያደርግ ያግዛል ነው ያሉት፡፡ በኅልውና ዘመቻው የተገኘው ድል የእያንዳንዱ ሕዝብ የጋራ ጥረት ድምር ውጤት በመሆኑ የክልሉ መንግሥት እውቅና ይሰጣልም ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleአመራሩ በተገኘው ድል ሳይኩራራ በቀጣይ ሊያጋጥሙ ለሚችሉ ፈተናዎች እንዲዘጋጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አሳሰቡ።
Next articleሕብረ ብሔራዊቷን ኢትዮጵያ የማጽናት እና የመጠበቅ አደራ ተብሲር –የንጉሱ ሽሩባ!