ጎንደር አካባቢ ተከስቶ የነበረው ችግር የተቀነባበረ ሴራ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ተናገሩ፡፡

236

ባሕር ዳር፡ መስከረም 25/2012 ዓ/ም (አብመድ) ሰሞኑን በማዕከላዊ ጎንደር ዞንና በጎንደር ከተማ የተከሰተው የፀጥታ ችግር የክልሉን ሠላም በማይፈልጉ ኃይሎች የተቀናበረ ሴራ መሆኑን በጎንደር የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ገለጹ፡፡

ሐሳባቸውን ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹‹ችግሩ ሆን ተብሎ የክልሉን ሠላም ለማደፍረስ በሦስተኛ ወገን የተጠነሰሰ ሴራ ነው›› ብለዋል።

ከፖርቲዎች መካከል የአማራ ብሔር ንቅናቄ (አብን) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተባባሪ አቶ ደሞዝ ካሴ በደረሰው የሕይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደልና የንብረት መውደም የተሰማቸውን ሐዘን ገልፀው ‹‹የአማራና የቅማንት ሕዝብ ለዘመናት አብረው የኖሩ ናቸው። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአማራን ሕዝብ አንድነት በማይፈልጉ ኃይሎች በተቀነባበረ ሁኔታ አሳፋሪ ግጭት እንዲከሰት ሆኗል፤ ይህም ለረጅም ዘመናት ሲሰራ የኖረ የሴራ ውጤት ነው›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሥራ አስፈፃሚ አርበኛ መዓዛው ጌጡ ደግሞ ትርምሱ በሦስተኛ ወገን ተንኳሽነት የመጣ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ችግር በመተማና አካባቢው ሲፈጠር ምንም ዓይነት እርምጃ ባለመወሰዱ አሁንም ቀውሱ እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳድር አዴፓ ጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ መስፍን ዓለምነው ደግሞ ተልዕኮ የተሰጣቸው ጽንፈኛ ኮሚቴዎች ምንም ዓይነት ልዩነት የሌለውን ሕዝብ ለመነጠል የሚያደርጉት እንቅስቀሴ መሆኑን ጠቅሰው ‹‹ሦስተኛ ወገን የሚባለው የሚሸፋፈን ሳይሆን ትህነግ (ህወኃት) ነው›› ብለዋል። አዴፓ ከወጣቶች ጋር በመቀናጀት የተሻለ ሠላም እንዲመጣ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።

‹‹ችግሩ በአጭር መቆም እየቻለ እዚህ ደረጃ መድረስ አልነበረበትም›› ያሉት አርበኛ መዓዛው ‹‹አሁንም አዴፓ ከሕዝቡ ጋር ተቀራርቦ መሥራትና አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ ይጠበቅበታል›› ብለዋል። አያይዘውም ወጣቱ ከስሜት ነፃ ሁኖ አካባቢውን እንዲጠብቅና የሴረኞች ዓላማ አስፈፃሚ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርበት አሳስበዋል።

አቶ ደሞዝ ደግሞ ‹‹መንግሥት የሦስተኛ ወገን እጅ እንዳለበት ማስረጃ አለኝ ብሏል፤ ስለዚህ እነማን እንደሆኑ በመለየት ይፋ በማውጣት አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስድና ሴራውን በመረዳት ችግር ያለባቸውን ሰዎች ለሕግ ማቅረብም ይገባል›› ብለዋል። ወጣቶችም ስትራቴጂክ ከሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩና አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡- እመቤት ሁነኛው

Previous articleበአማራ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሃይማኖት ተከታዮች ሰልፍ አካሄዱ፡፡
Next articleኤፍራታና ግድም አካባቢ አሁንም የፀጥታ ችግር መኖሩን ነዋሪዎቹ ተናገሩ፡፡