ጎንደር ለእንግዶቿ ንጉሣዊ አቀባበል ለማድረግ ሽር ጉድ እያለች ነው፡፡

170

ታኅሣሥ 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) እምቅ ታሪካዊ፣ መንፈሳዊ እና ተፈጥሮአዊ የመስህብ ሃብቶች ባለቤት የሆነችው ጎንደር ለእንግዶቿ ንጉሣዊ አቀባበል ለማድረግ ሽር ጉድ እያለች ነው፡፡ መንግሥት ባቀረበው ጥሪ መሠረት ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች የሚኖራቸው ቆይታ መልካም እና አይረሴ እንዲሆን በቂ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማም ይህንን ታሳቢ ያደረገ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡

አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ያነጋገራቸው የዞብል ሪዞርት ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሮቤል ታዬ ጎንደር ለጉብኝት ተመራጭ ከመሆኗ አንጻር በርካታ እንግዶች ይመጣሉ ተብሎ እንደሚታሰብ ተናግረዋል፡፡ የሚመጡ እንግዶችን ታሳቢ ያደረገ እና ጎንደርን በሚመጥን መልኩ ለእንግዶቻቸው የንጉሣዊ የክብር አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

የልደት እና ጥምቀት በዓል በጎንደር በድምቀት የሚከበሩ ሃይማታዊ በዓላት መሆናቸውን ገልጸው እንግዶቻቸው አይረሴ ጊዜ እንዲያሳልፉ በቂ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በቅናሽ ዋጋ እንጂ ዋጋ ጭማሪ የማይታሰብ መሆኑንም ነው ሥራ አስኪያጁ የነገሩን፡፡

የሄርፋዚ ሪዞርት ሥራ አስኪያጅ አቶ ለምለሙ ነጋሽ እንዳሉት የሀገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ለሚመጡ እንግዶች ደማቅ አቀባበል ለማድረግ የላቀ አገልግሎት ለመስጠት በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል፡፡ በላቀ የእንግዳ አቀባበል የምትታወቀው ጎንደር በተለይ የልደት እና ጥምቀት በዓልን በጎንደር ለማሳለፍ የሚመጡ አንግዶች ቁጥር በርካታ በመሆኑ ይህንን የሚመጥን አቀባበል እናደርጋለን ብለዋል፡፡ የእንግዶቹ መምጣት በተለይ በኮሮና ቫይረስ እና በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ ሁነኛ መፍትሔ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ ይህንን ዕድል ለመጠቀም እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የጎንደር ከተማ አስጎብኚዎች ማኅበር ጸሐፊ በለጠ ታረቀኝ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በሽብርተኛው የትግራይ ቡድን ወረራ የጎብኚዎች ቁጥር ተቀዛቅዞ እንደነበር አንስተዋል፡፡ ይህንን ዘርፍ ለማነቃቃት ለኢትዮጵያውያኑ የተደረገው ጥሪ መልካም እንደሆነ እና የአስጎብኚ ማኅበራቱም ይህንን እድል ለመጠቀም የተሻለ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ጎብኝዎቹ ወደ ጎንደር ሲመጡ ምንም አይነት እንግልት እንደማይደርስባቸው እና ስለ ሀገራቸው ታሪክ፣ ባህል እና ዕሴት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ይደረጋል ብለዋል፡፡ ለዚህም ሙያዊ እና በሥነምግባር የታነጸ አገልግሎት እንደሚሰጡ አስታውቋል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አቶ ቻላቸው ዳኘው እንዳሉት እንግዶች በጎንደር ቆይታቸው ያማረ እንዲሆን ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ውይይት ተደርጎ በቂ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ለእንግዶቹ ጎንደር የምትታወቅበትን የንጉሣዊ አቀባበል ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡

የአጼ ቴዎድሮስ ሽሩባ ወደ ጎንደር የሚመጣበት ወቅትም በመሆኑ ለዲያስፖራው ሌላ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ዲያስፖራው የተፈናቀሉ ወገኖቹን በመጠየቅ እና መሰል የበጎ ተግባራትን በማከናወን መልካም ጊዜ እንዲያሳልፉ ኀላፊው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡-የማነብርሃን ጌታቸው

#ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleበራያ ቆቦ ወረዳ በሚገኘው የሮቢት 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት በሽብር ቡድኑ የተፈጸሙ 19 የተናጠልና የጅምላ መቃብሮች ተገኙ።
Next article❝እኔ ከራያ ልጅ እኔ ከዲቢ ልጅ ፈሪ ቢገኝብኝ፣ በመኪናው መንገድ ኦራል ይነዳብኝ❞