
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራ እና በአፋር ክልል ባደረገው ወረራ በርካታ ንጹሃንን ገድሏል፤ አፈናቅሏል፤ ንብረት ዘርፏል፣ አውድሟል፡፡
መንግሥት ባካሄደው የሕልውና ዘመቻ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ተደምስሶና ሽንፈትን ተከናንቦ በመመለሱ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋምም በርካታ ድጋፍ በማስፈለጉ መንግሥት ለሚመለከተው ሁሉ የድጋፍ ጥሪ አስተላልፏል፡፡ ጥሪውን ተከትሎ በርካቶች ከያሉበት ተጠራርተው ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይልም ለተፈናቀሉ እና በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች 3 ሚሊዬን ብር በገንዘብ እና 4 ሚሊዬን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ ድጋፉ የዓይነት እና የገንዘብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቀደም ብሎ ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በቀጣይም የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመዘርጋት የተሻለ አገልግሎት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አቶ አሸብር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል በርካታ መሠረተ ልማቶቹ ውድመት የደረሰባቸው ቢሆንም በአፋጣኝ ለመገንባት ጥናቶች እየተደረጉ ነው፤ በቀላሉ የሚስተካከሉትን ደግሞ በማስተካከል አገልግሎት እየሠጠ ነው ብለዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ኮሚሽነር ዘላለም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ርብርብ አጋዥነታችሁን እና አብሮነታችሁን ለማሳየት ያደረጋችሁት ርብርብ በክልሉ እና በተፈናቃዮች ሥም ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል፡፡ ሌሎችም ዓርዓያነቱን ተከትለው በማቋቋም ሥራው የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ግዛቸው ሙሉነህ ኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን ችግር ለመቀልበስ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ሠራተኞች ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አቶ ግዛቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል እንደሌሎች መስሪያ ቤቶች ሁሉ አገልግሎት ለመስጠት ቀድሞ ሥራ በመጀመሩ ሊመሰገን ይገባዋል ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሕልውና ዘመቻው ያደረገውን ትብብር በመልሶ ግንባታውም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
