
ወልድያ፡ ታኅሣሥ 22/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጎህ መቅደድ ጀምሯል። አዕዋፋት ከእየጎጇቸው ተነስተው ማለዳውን በዝማሬ አድምቀውታል። የአዕዋፋት ዝማሬ፣ እያባበለ ከእንቅልፍ የሚያነቃ ዜማ ነው፣ ማን እንደ አዕዋፋት ዝማሬ፤ ምንም ሳይጨመርበት በተፈጥሮ ፀጋ ብቻ ነብስን በሚያማልል ዜማ ይዘምራሉ። ማለዳውን በዝማሬ ያደምቃሉ። ጨለማው ተገፎ የብርሃን ወጋገን መታየት ሲጀምር ዝማሬያቸውን ያቀርባሉ። ጀንበር ጠልቃ ጀንበር በዘለቀች ጎህ በቀደደ ቁጥር በሕብረት ይዘምራሉ።
የአዕዋፋት ዝማሬ በከባድ ጥሎኝ ከነበረው እንቅልፍ እያባበለ አነቃኝ። እንቅልፍ ራስን ስቶ መቆዬት፣ ከድካምና ከጭንቀት ማምለጥ ነው ይላሉ። ጀሮዬን ወደ ዝማሬው አዘንብዬ ቆየሁ። ለነብስ ሀሴትን የሚሰጥ ጥዑመ ዜማ። በቅርቡ ሰላምና ነፃነቷን ያገኘችው የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች የአዕዋፋቱን ዝማሬ እያዳመጡ ይመስል ዝምታን መርጠዋል። በማለዳ የአዕዋፋቱን ዝማሬ የሚያደበዝዝ ድምፅ አይሰማም። አዕዋፋቱ ግን በጥዑመ ዜማቸው ዝማሬያቸውን ቀጥለዋል። እኔም ዝማሬውን መስማቴን ቀጥያለሁ። ማታ ከአልጋቸው ላይ በሰላም እንዳረፉ ያልተነሱ አሉና በሰላም አሳድሮ በሰላም ያስነሳኝን አምላክ አመስግኘው አልጋዬን ለቅቄ ተነሳሁ። አዲስ ቀን ለአዲስ ነገር መሰጠት መታደል ነውና ተጨማሪ ቀን ለሚሰጥ አምላክ ምስጋና ይገባዋል። እርሱም የሚፈልገው ምስጋና ብቻ ነው። በቀዝቃዛ ውኃ እጄንና ፊቴን ታጥቤ ለጉዞ ተዘጋጀሁ።
በአዕዋፋት ዝማሬ ታግዤ በጠዋት የተነሳሁት አንድ ብርቱ ጉዳይ ለመሥራት ቀጠሮ ይዤ ስለነበር ነው። በማለዳ ተነስቼ ወደዚያ ሥፍራ ለመሄድ ጉዞ ጀመርኩ። ዝምታን መርጠው የነበሩት የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች እየተነሱ ቤቶቻቸውን መክፈት ጀምረዋል። በነፃነት የሚያሳልፉት ሌሊት ያማረ ነውና የሰላም እንቅልፍ ተኝተው አድረዋል። ሰላማዊ ሕይወት ጀምረዋል። በመንገዱ ዳር በረድፍ የተሰደሩትን ቤቶች ግራና ቀኝ እየተመለከትኩ ከተማዋን ለቅቄ ወጣሁ። መንገዴ ወደ ቆቦ አቅጣጫ ነው። ጥቂት እንደተጓዝን ወደ ቆቦ የሚወስደውን መንገድ ወደ ግራ ትተን ወደ ቀኝ ታጥፈን ወደ ሐራ ገሰገስን። ጀንበር በምሥራቅ ንፍቅ ብርሃኗን መፈንጠቅ ጀምራለች። በማለዳ የተነሱት አርሶ አደሮች ግመሎቻቸውን ጭነው በጎዳናዎች ሲጓዙ ይታያሉ። የቀኑ ሕይወት ቀስ በቀስ እየተጀመረ ነው። ጀንበርም ብርሃኗን ከመፈንጠቅ ወጥታ ሙቀቷ ጨምሮ መፍለቅለቅ ጀምራለች። ጉዟችን ቀጥሏል። ሐራ ከተማ ደረስን። ሐራን ቃኝተናት ወደ ፊት ገሰገስን። ለዓይን የሚስብ ውብ መልከዓምድር ይታያል። በግራና በቀኝ ያለውን ውብ ተፈጥሮ እየቃኘን መንገዳችን ቀጠልን። በመካከል በአሸባሪው ቡድን የተሠበረ ድልድይ አገኘን እና በወንዙ ውስጥ በተሠራው ተለዋጭ መንገድ ተሻግረን መዳረሻ ወደ አልነው አካባቢ አቀናን። በዚያ አካባቢ አሸባሪው የትህንግ ቡድን ከባድ ምት ሲገጥመው መንገድ መቁረጥ፣ ድልድይ ማፍረስ ከሞት ያድነው ይመስል እያፈረሰ ሮጧል።

አካባቢው ቋጥኞች የበዙበት ነው። መዳረሻችን እየቀረበ ነው። ለአይን የሚስቡ ውብ ኮረብታዎች ወደ አሉበት ቦታ እየተጠጋን ነው። ሽርጣቸውን የታጠቁ፣ የሚያበራ መሳሪያቸውን ያነገቱ፣ መልካም ጥርሳቸውን በረጅም መፋቂያ እያሳመሩ የሚጓዙ ጎረምሶች ቀልብ ይስባሉ። ከመዳረሻችን ሥፍራ ደርሰናል። ለጦርነት የተመቻቸ የሚመስል፣ ኮረብታዎች የበዙበት፣ ጀግኖች የተፈጠሩበት፣ ፈሪ የማይኖርበት፣ ጠላት የማይሰነብትበት ድንቅ ሥፍራ። በዚህ ሥፍራ ጠላት የማይነካቸው፣ አብዝቶ የሚፈራቸው፣ ወዳጅ የሚያከብራቸው፣ አብዝቶ የሚወዳቸው ጀግና ሕዝብ የሚመሩ ጀግና መሪ አሉ። በማለዳ ተነስተን ወደዚያ ማቅናታችንም እኒህን ጀግና መሪ ለማግኘት ነበር። የድሬ ሮቃውን ጀግና ሐሰን ከረሙን።
ድሬ ሮቃ ደረስናል። ድሬ ሮቃ ወጣ ገባ የበዛባት የደስ ደስ ያላት ጀግኖች የተፈጠሩባት ውብ ሥፍራ ናት። ጀግናው ሐሰን ከረሙ በቁርጥ ቀን ቆርጠው፣ በጀግንነት ተዋግተው፣ በጀግንነት አዋግተው፣ በዱር በገደል ተንከራትተው በጀግንነት ጠላትን መትተው፣ ነፃነት አምጥተዋልና ይሞገሳሉ፣ ይወደዳሉም። ሀገር ያደነቃቸውን፣ ወገን የኮራባቸውን ጀግና ሰው አገኘናቸው። ደስ በሚል ለዛ ተቀበሉን። ፊታቸው ቆጣ ያለ፣ ረዘም ያለ ቁመና ያላቸው ግርማ ሞገስ የተቸራቸው የተደላደሉ ጀግና ናቸው። መረጋጋት ይስተዋልባቸዋል። ከአንደበታቸው የሚወጣው ቃል ተመርጦ ነው። የጀግና ፊቱ ኮስታራ ነውና ኮስተር ማለት ያበዛሉ።
የድሬ ሮቃው ጀግና ሐሰን ከረሙ አርሶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ናቸው። ሐሰን ከረሙ የድሬ ሮቃ አስተዳደር እና ፀጥታ ሆነው ሕዝባቸውን አገልግለዋል። በመካከል ግን በቃኝ ብለው ከኀላፊነት ራሳቸውን አግልለው ነበር። ወደ ሊቀመንበርነት የመጡትም ጦርነቱ ከመጀመሩ ከጥቂት ወራት በፊት ነበር። ሕዝብ ስለሚወዳቸው እባክዎን ሊቀመንበር ይሁኑ ሲባሉ አልፈለጉም። በወረዳና በዞን መሪዎች ተጠየቁ አይሆንም አሉ። ሕዝቡ፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እባክዎን ቀበሌዋን ይምሯት ብለው ጠየቋቸው። ያን ጊዜ ሐሰን ከረሙ እሺ ብለው ኀላፊነት ተቀበሉ። ብልህ የሆነ ሕዝብ ብልህ መሪ መርጧልና በጭንቅ ቀን በጥበብ መርተው አሻገሯቸው። መካሪና ዘካሪ ናቸው፣ ቀን ሰጠኝ ብለው ሰው አይበድሉም። ሁሉንም በፍቅርና በጥበብ ይፈታሉ እንጂ።

በቤታቸው አቅራቢያ ጥቂት ካወጋን በኋላ ጀብዱ ሲሰሩባቸው ወደ ነበሩት አንደኛው ተራራ ይዘውን ወጡ። ተራራው በቤታቸው በምሥራቅ ንፍቅ ይገኛል። ከእኛ ጋር እየተጓዙ ሳለ በአሻገር አንዲት ጎረቤታቸውን ተመለከቱና “እንደምን አደርሽ? ሉባባ” አሉ ሀሰን ከረሙ፣ በአካባቢው ለዛ በአሻገር ያለችውን ሉባባ የተባለች ሴት እየተመለከቱ። “እንደምን አደርክ የእኛ? አንበሳ” አለች ሉባባ ደስ በሚል የአካባቢው ቅላፄ፣ “ደህና ነኝ ደህና አድራችኋል?” አሉ ሐሰን ከረሙ። “ደህና ነን እንኳን በኸይር አቆዬን፣ እንኳን በደህና አገናኘን” አለች ሉባባ። በሁለቱ ሰዎች የሰላምታ ልውውጥ ደግነት፣ ደስ የሚል አካባቢያዊ ለዛ፣ ጨዋነት እና የሐሰን ከረሙን ጀግንነት ታዘብኩ። ሐሰን ከረሙ ሰላምታ ባቀረቡ ቁጥር የእኛ አንበሳ እየተባሉ የሚሞገሱ ጀግና መሆናቸውን ተረዳሁ።
ወደ ተራራው ወጣን። በዙሪያ ገባው የሚገኘውን ተራራ እያመላከቱን ጠላትን ድባቅ ይመቱበት እንደነበር ነገሩን። የአካባቢው ጀግኖች ሐሰን ከረሙን ጠርተው አይጠግቧቸውም። የእውነት ይወዷቸዋል። ጀግንነታቸውን ይመሰክሩላቸዋል። ጠላት ወረራ በፈፀመ ጊዜ እነ ሐሰን ከረሙ ኩቢ፣ ቂላዋ፣ ሁጅራ፣ ዲኮ፣ ሙጢ፣ ጣኢላ፣ ቀረዲማ፣ ጮቢ፣ ቂለንቲ፣ ሀማሮ በተባሉ ኮረብታዎች ነበር አጥምደው እየጠበቁ ድባቅ የመቱት። ሀገር ስትነካና ወንድ ልጅ ሲብሰው አይመለስም። ወደፊት ብቻ ነው የሚገሰግሰው እኛን ያስነሳን ብሶት ነው። የድሬ ሮቃ ጀግኖች መነሻቸው ከአባት የመነጨ ነው። ጀግንነታችን ከአባት የመጣ ነው። የቀየው ሰው በልጅነት ጀምሮ ከመሳሪያ ጋር የሚኖር ነው ይላሉ።
“ግና ሲወለድ እራሱን ሲላጭ፤
ይቅለበለባል እጁ ከምላጭ” የሚባል ልጅ ነው ከድሬ ሮቃ የሚፈጠረው። ገና በልጅነቱ የአተኳኮስ ዘዴ ይማራል፣ ዒላማ ይመታል፣ በጥሶም ይጥላል። በውጊያ ጊዜ ሐሰን የሚመሯቸው ጀግኖች ጠላትን ሲደመስሱ “አበጃችሁ እሰይ እንኳንም የእኔ ልጆች ሆናችሁ” እያሉ ያበረታቱናል ይሏቸዋል።
የድሬ ሮቃ ጀግኖች ጀኔራላችን እያሉ ይጠሯቸዋል። ጠላት ገና በአፋር በኩል በከላዋ እያለ የድሬ ሮቃ ጀግኖች እየሄዱ ይዋጉ ነበር። በላይ በራያ በኩል ሲመጣም ወደ ራያ እየዘለቁ ጠላትን ይመቱ ነበር። “ይሄ ወራሪ ቡድን ለሰው እንደማይበጅ ግንዛቤ አለ። በዘመኑ የራሱን ፍላጎት ነው ሲጭንብን የኖረው፡፡ ጋሽ ሐሰን ከረሙ የሽብር ቡድኑ ወረራ ከመፈፀሙ በፊትም ይጠሉትና ይታገሉት እንደነበር ነግረውናል። ጠላት ተመልሶ ሀገር አይመራም፣ አካባቢያችንንም አይረግጥም በሚል ተነስተው ትግል አደረጉ። የድሬ ሮቃ ጀግኖች በተጠንቀቅ ነውና የሚኖሩት አደረጃጀት አላቸው። በተደራጁበት መንገድ ይዋጉት ጀመር። ለወራትም ታገሉት። የቡድን መሣሪያ ያልነበራቸው ጀግኖች ጠላትን እየማረኩ መታጠቅ ጀመሩ። ተተኳሽም ከጠላት ይማርኩ ጀመር። ጀግኖቹ በጠላት ላይ ድል እየተቀዳጁ በሄዱ ቁጥር ትግላቸው የበለጠ ገነነ። የሽብር ቡድኑ አባላት ጥይት አይመታቸውም እየተባለ የውሸት ዝና ይነገርላቸው ነበር። የሐሰን ልጆች ግን እንተያያለና ብለው ጠበቋቸው። አንጥረው ሲተኩሱ የማይሳቱ በገፍ እየመጡ የሚሞቱ መሆናቸውን ሲያዩ አስቀድመው ባስወሩት ወሬ እየሳቁ ይለቅሟቸው ጀመር። የሚመጣው ሁሉ በድሬ ሮቃ ጀግኖች ይረግፍ ጀመር። የመሳሪያ ምርኮም እየጨመረ መጣ። የድሬ ሮቃ ኮረብታዎች በጠላት አስከሬን ተሞሉ። ለወራት ያላቋረጠ ጀግንነት አደረጉ። በመካከል የጠላት ኀይል በዛባቸው እና ኪሣራ ለመቀነስ ሥፍራቸውን ለቀቁ። ለቅቀው ግን አልቀሩም። ዳግም ወደሚያውቋቸው ኮረብታዎች ተመለሱና ውጊያቸውን ቀጠሉ። ጀግኖቹ ጥንቅሽ አገዳ እየበሉ ጫካ ለጫካ እየተመላለሱ ጠላትን ይመቱት ጀመር። በአንደኛው ኮረብታ ታዩ ሲባል በሌላኛው ኮረብታ እየተምዘገዘጉ ጠላትን እረፍት አሳጡት። የተገኘው ጠላት ሁሉ በአለበት እየተገደለ፣ መሳሪያውም እየተማረከ እረፍት አጣ። ድሬ ሮቃ የእሳት ምድር ሆነችባቸውና እየራቋት ሄዱ። ጠላት አስከሬኑን እንኳን መቅበር አልቻለም።
“ለመኖር ስንል በሬዎቻችንን እየሸጥን ነው መሣሪያ የገዛን። ጥንድ በሬ ካለን አንዱን ሸጠን መሣሪያ እንገዛለን። በገንዘባችን በገዛነው መሣሪያ ጠላትን መታንበት” ነው ያሉን ጀግናው ሐሰን ከረሙ። “እኛ የተዋጋነው በአማራነታችን በደል ስለደረሰብን ነው። ጀኔራል ሲሉኝ ደስ አይለኝም። እናት እና አባቴ ባወጡልኝ ስም ስጠራ ነው ደስ የሚለኝ። ጄኔራልነት በቀላሉ አይመጣም። በዋዛ አይገኝም። እኔ የተዋጋሁት ጄኔራል እንድባል አይደለም። እንዴት ይህችን ሀገር ጠላት ይደፍራታል? ብዬ ነው፣ ግንባሩን ቢሉት የማይመለስ ብዙ የአማራ ልጅ ሞልቷል” ይላሉ ሐሰን ከረሙ። እርሳቸውን ያስነሳቸው አትንኩኝ ባይነት ነው። እርሳቸውን ያስነሳቸው ከአባት ከቅድመ አያት የወረሱት አልደፈርም ባይነት ነው። እርሳቸውን ያስነሳቸው የልባቸው ጀግንነት ነው።
ጠላት ሐሰን ከረሙና እርሳቸው የሚመሯቸው ጀግኖች እንዳይዋጓቸው በመልእክተኛ ይማፀኗቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ። እሳቸው ግን ሀገር አልሸጥም ብለው አሳፍረው መለሱት። ጀግናው ሐሰን ከረሙ ንቅንቅ አልል ሲሉ ማርኩት የሚል ሀሳብ ከጠላት ሠፈር መጣ። የእሳቸው እጅ ግን የሚያቃጥል እንጂ የሚማረክ አልነበረምና የሚመጣውን ሁሉ በጥይት እሳት እያነደዱ ጣሉት።
“ሐሰን ከረሙ የቆላው መብረቅ፣
ጎራ ለጎራ አባሮ እማይለቅ” ጎራ ለጎራ አባረው የማይለቁ፣ የቆላ መብረቅ ናቸውና ማንም አይደፍራቸውም። ማንም አያመልጣቸውም። ወደፊትም ለአፍታም ቢሆን እንደማይዘናጉ ነው የተናገሩት። እርስቱን፣ ሚስቱን፣ ሀብቱን ጥሎ የሸሸ ሰው ኃጢያተኛ ነው፣ ጀግንነት መልካም ስም ያመጣል እያልኩ ጀግኖችን አበረታታቸዋለሁ ይላሉ ሐሰን ከረሙ። “የኢትዮጵያ አፈር ብንኖርም ቁርሳችን ናት። አርሰን፣ ሰርተን በልተን ነው፣ ብንሞትም ደግሞ ልብሳችን ናት። ከእርሷ ላይ ነው የምንተኛው፣ ለዚህች ሀገር እንዴት ዝም ይባላል? እንዴት ሆኖ ይተኛል? ሞት እንደሆነ ቢፈሩት አይቀርም። እናቱን፣ ሀገሩን የሸጠ ከኢትዮጵያ አፈር ያልተፈጠረ ነው። ከኢትዮጵያ አፈር የተፈጠረ እርሷን አይከዳም” የጀግናው ፅኑ እምነት ነው።
የፀና አቋም አላቸው። ወጣቶቹ እኔ ሊቀመንበር ስለሆንኩ ብቻ ሳይሆን እንደ አባትነቴ ይከተሉኛል። ይሰሙኛል። እኔም አላርቃቸውም። ወጣቱ ሀገርና ሃይማኖቱን እንዲወድ፣ እናት አባቱን እንዲያከብር እንደሚመክሩም ነግረውናል። ሐሰን ከረሙ በሠሩት ሥራ አይረኩም። አሁንም ቁጭት አለባቸው። ሌላ ድል ይከጅላሉ። መሥራት እየቻልን ሳንሠራ የሚያፀፅቱ ነገሮችን አሳልፈናል፤ ያለፈው አልፏል ለቀጣይ መማር አለብን ነው ያሉት።
ጀግና ሰው በጥቂት ነገር አይረካም። ሐሰን ከረሙም በጀግንነታቸው ፈፅመው አይኩራሩም። ገና አልሠራሁም ነው የሚሉት። ግን እኮ በድሬ ሮቃ ተራራዎች በጠላት ላይ ተጫውተዋል። ሀገር ነፃ አድርገዋል። ጀብዱ ፈፅመዋል። የሚደንቅ ጀግንነት፣ የሚገርም ልበ ሙሉነት በእርሳቸው ላይ ተመለከትኩ። የድሬ ሮቃ ጀብዱ የፈፀሙባቸው ተራራና ሸንተረሮች በአግራሞት ቃኝቼ ጀግናው ሐሰን ከረሙና ጦራቸውን አመስግኘ ከነበርኩበት ተራራ ወደ ግርጌው ወረድኩ።
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
