
ወልድያ፡ ታኅሣሥ 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) መልካም መምህር ፣ ድንቅ መሪ፣ ተስፋን አብሳሪ፣ በክፉ ቀን በፅናት የሚኖሩ፣ የሚከተሏቸውን ሳይታክቱ ወደ መልካሙ ሥፍራ የሚመሩ፣ ለምስጋና የበረቱ፣ ብርቱ፣ መልካምነት፣ ደግነት ፣ አዛኝነት የማይለያቸው። በሰርክ ለፈጣሪያቸው ምስጋና ያቀርባሉ፣ ለምድርና ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ይመጣ ዘንድ ይማፀናሉ፣ ስለ እውነት ይኖራሉ፣ በእውነተኛው መንገድ ይጓዛሉ፣ በእውነተኛው መንገድ ተከታዮቻቸውን ይመራሉ። ሰው በሰውነቱ የተከበረ ነው ይላሉ። ፈጣሪ ክብሩን ሊገልጥባቸው፣ ደግነቱን ሊያሳይባቸው፣ መልካምነትን ሊያስተምርባቸው ገና ከእናታቸው ማሕፀን እያሉ ጠበቃቸው፣ አስቀድሞ መረጣቸው፣ በመልካሙ መንገድ ብቻ እንዲጓዙ አደረጋቸው፣ በፀጋው ከለላቸው፣ በረከትን በእርሳቸው ላይ አወረደላቸው።
መልካም ነገር ብቻ ይናገራሉ፣ መልካም ነገር ብቻ ያደርጋሉ፣ የተቸገሩትን ይደግፋሉ፣ የታረዙትን ያለብሳሉ፣ የተጠሙትን ያጠጣሉ፣ የተራቡትን ያጎርሳሉ፣ በመንፈስ የተጨነቁትን በተሰጣቸው መንፈሳዊ ፀጋ ያፅናናሉ፣ አላፊዋና ጠፊዋ ዓለም አታውቃቸውም፣ እርሳቸውም አላፊዋን ዓለም አያውቋትም። የእርሳቸው ዓለም የማያልፈው ነው። ሳይታክቱ የሚተጉትም ለማያልፈው ዓለም ነው። እርሷቸው ከማሕፀን ጀምሮ ተጠብቀዋልና ጊዜያቸውን በክንቱዋ ዓለም በምትባዝነዋ ጎዳና አላሰለፏትም። በልጅነታቸው የጥበብን መንገድ ተከተሉ። በእርሷም ሳያቋርጡ ተመላለሱባት፣ ወጡ ወረዱባት፣ ፍሬዋን አሽተው ቃሙባት፣ ከፈጣሪያቸውም ጋር ተገናኙባት፣ መልካሙን ነገር ሁሉ በእርሷ አገኙባት፣ ጥበብን ተከትለዋልና ከፈጣሪያቸው ፍሬዋን ተቀበሉ። ትዕዛዛቱን ጠብቀውታል፣ ስሙን ሳያጓድሉ በሠርክ አንስተውታል፣ ለምስጋና አይቦዙኑም፣ በሠርክ ያመሰግናሉ፣ በሠርክ ስሙን ይዘክራሉ፣ በረከቱን ለምድር ይሰጥ ዘንድ ይማፀናሉ።
ያገኘ ሁሉ አባታችን ይላቸዋል፣ ከልቡ ያከብራቸዋል፣ አጥብቆ ይወዳቸዋል፣ በክፉ ቀን መልካም ኾነው፣ ሰው በጠፋበት ጊዜ ፀንተው ክፉውን ቀን አሻግረዋቸዋልና አሻጋሪ፣ መልካም አባት፣ የክፉ ቀን መውጫ ይሏቸዋል። መልካሙን ነገር አድርገውላቸዋልና። እርሳቸው ልምላሜ የማይለየው ታላቅ ዛፍ ናቸው። የደከመው የሚያርፍባቸው፣ መጠለያ ያጣ የሚጠለልባቸው፣ መንፈሱን የሚያበረታባቸው፣ እርሳቸው ምርኩዝ ናቸው ደካማ የሚደገፋቸው፣ እርሳቸው መሻገሪያ ናቸው ሕዝብ ሁሉ የሚያልፍባቸው፣ እርሳቸው መኩሪያ ናቸው የሚከተላቸው ሁሉ የሚኮራባቸው። በክፉ ቀን ደራሽ፣ ሲርብ አጉራሽ፣ ሲታረዙ አልባሽ ናቸውና አባታችን ይሏቸዋል። በክፉው ቀን ሰው የሆነን ሁሉ ልጆቼ ብለዋልና እኛም አባታችን እንላቸዋለን ይላሉ። ሃይማኖት አልመረጡም፣ ዘር አልጠየቁም፣ ቋንቋ አልመረመሩም ሰው የሆነውን ሁሉ ልጄ እያሉ ደገፉት፣ ልጄ እያሉ አፅናኑት፣ የተስፋውን መንገድ አሳዩት፣ ልጄ እያሉ አጎረሱት፣ ልጄ እያሉ አጠጡት፣ ከችግር አወጡት። ለዚያም ነው ሁሉ በኩራት አባታችን የሚላቸው። እውነተኛ አባት ኾነው ተገኝተዋልና። የመነኩሴ ሀገሩ አይጠየቅም፣ እናቱ ቤተክርስቲያን፣ ልጆቹ ምዕመናን ናቸው ይላሉ። መነኩሴ ነብሴን ለስላሴ ብሎ ከመነነ በኋላ ዓለሙ ምድራዊ አይደለም። ዓለሙ የማይጠፋው፣ የማያንቀላፋው ያኛው ዓለም ነው። በተባረከች ቀን የተባረኩት ወደዚች ምድር መጡ። በጥበብና በሞገስ አደጉ። ከብቶችን ማገድ፣ ፍየሎችን ማሰማራት የሚችሉበት እድሜ ላይ ሲደርሱ ከብቶችን እያገዱ፣ ፍየሎችን እያሰማሩ በዱርና በገደል መዋል ጀመሩ። እርሳቸው ግን ከእንስሳት ለበለጡት፣ ከፍጥረታት ሁሉ ለከበሩት እረኝነት አስቀድመው ተመርጠው ነበር። በቅንነት ወላጆቻቸውን እየታዘዙ አደጉ። በየቀኑም ምርቃት ይወርድላቸው ነበር። እድሜያቸውም እየጨመረ መጣ። ይጓዙበት ዘንድ አስቀድሞ የተዘጋጀላቸውን መንገድ ጀመሩት።
ታላቅ የሚሆኑ ተማሪ ለማስተማር የታደሉት አባት ተቀብለው ፊደል አስቆጠሯቸው። እኒያም አባት አባ ገብረ እግዚአብሔር ይባሉ ነበር። በድንግልና የሚኖሩ ደግ አባት ነበሩ። ደገኛው አባት ደገኛዋን ተማሪ ተመለከቷቸው፣ አስቀድመው የተመረጡ ናቸውና የፊደል አያያዛቸው ግሩም ያሳኛል። ወደ አባታቸውም አቅንተው “ይህን ተማሪ እንዳታስቀረው፣ ጥሩ ተሰጥኦ አለው፣ ነገ ጥሩ ካሕን ይሆናል” ሲሉ ነገሯቸው። እኒያ አባት የተናገሩት ሁሉ የሚደመጥላቸው፣ ያሉት ሁሉ የሚፈፀምላቸው የሚከበሩ ሰው ነበሩና የዚያኔው ተማሪ አባት የመምህሩን ቃል አከበሩ። የተባሉትንም ተገበሩ። በቄስ ትምህርቱ ቀጠሉ። የዚያኔው ተማሪ የአሁኑ ታላቅ አባት ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ። ቀለም ቆጠሩ፣ ዳዊት ደገሙ፣ ውዳሴ ማርያምን አዜሙ፣ ቅኔውን ተቀኙ፣ መፃሕፍትን መረመሩ። ፈጣሪ ለመልካም ነገር አዘጋጅቷቸዋል እና በመልካም ነገር ይመራቸው ነበር።
በየአድባራቱ እና በየገዳማቱ እየተዘዋወሩ ከመምህራን እግር እየተቀመጡ ጥበብን አጣጣሙ፣ ጥበብን በቀመሩ፣ መፃሕፍትን በመረመሩ ቁጥር ፀጋው እየበዛላቸው ሄደ። በለጋ እድሜያቸውም መሪጌታ ኾኑ። ወደ ደቡብ ኢትዮጵያም ሄደው ያለ ድካም ያገለግሉ ጀመር። ነብሳቸው መንኩሳ መኖርን ትመርጣለች፣ የመነኩሴ ሕይወትን አጥብቃ ትወድዳለችና መመንኮስ አሰቡ። ነገር ግን በለጋ እድሜያቸው ይሆናል ብለው አላሰቡትም ነበር። ሰው ያስባል እግዚአብሔር ይፈፅማል ኾነና ነገሩ በአንድ ወቅት ከአንድ ጳጳስ እግር ሥር ተቀምጠው ሲማሩ በልጅነት መመንኮስ የሚችሉበት እድል እንዳለ ተገነዘቡ። በ28 ዓመታቸውም ሥርዓተ ምንኩስናቸውን ፈፀሙ። ዓለምን ፈፅመው ተለዩዋት። ፈፅመውም ናቋት። ፈጣሪያቸውን ጥበብህን ልወቅ እያሉ ይማፀኑታል። እርሱም በጥበቡ መንገድ ይመራቸዋል። በጥበቡ ዓለም ውስጥ ያመላልሳቸዋል። ከጥበብ ጥበብ እየተጨመረላቸው፣ መልካም ነገርም እየተሰጣቸው ለታላቁ አገልግሎት ታጩ። ብፁዕ ናቸውና ሊቀ ጳጳስ ኾኑ።
የቤተክህነት ሰው አካበቢ የለውም፣ ያሳደጉት ኢትዮጵያውያን ናቸው። እንጀራ እየቆረሱ ኢትዮጵያውያን አስተምረውታልና ይላሉ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ። እኒህ ብፁዕ አባት አቡነ ኤርሚያስ ያሰደገቻቸው፣ በክብር ያኖረቻቸው፣ የሚመኩባት፣ በጥበብ ያደጉባት ቤተክርስቲያን ኃላፊነት ሰጠቻቸው። ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አህጉረ ስብከቶችን በሊቀ ጳጳስነት ይመሩ ዘንድ ተሾሙ። በዚህ የሹመት ዘመናቸው ታዲያ ምዕመኖቻቸውን የሚፈትን እርሳቸውንም ጊዜ የሚያሳጣ ችግር ገጠማቸው። አሸባሪውና ወራሪው ቡድን እርሳቸው በሊቀ ጳጳስነት የሚመሩትን አካበቢ ወረረ። ዜጎችን አፈናቀለ። ሀብትና ንብረታቸውን ዘረፈ አወደመ። በተወረሩት አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችም ችግር ላይ ወደቁ። ብፁዕነታቸውም በጎቻቸው እንዳይራቡ፣ እንዳይበተኑ ይመግቧቸው፣ ይሰበስቧቸው፣ ከተኩላ ንጥቂያ ይጠብቋቸው ዘንድ ተነሱ። ወራሪዎቹ ሕዝብን እንዳያንገላቱ፣ ዜጎችም በረሃብ እንዳይሞቱ ይታትሩ ጀመር። ሁሉም ነገር የተዘጋባቸው ዜጎችም አባታችን ረሃበን፣ ጠማን፣ ታረዝን፣ ተከፋን እያሉ አስጨነቋቸው። እርሳቸውም በችግር ውስጥ ኾነው የሚጮሁትን ዜጎች ልመና ይመልሱ ዘንድ ያለ እረፍት ኳተኑ። ሳይሰለቹ ደከሙ። እኒያ በነጋ በጠባ ድምፃቸውን ለሚያሰሟቸው ሰዎች ችግሩን መሻገሪያ መንገድ የሚቻላቸውን ሁሉ አደረጉ።
“ገጠሩም ከተማውም በጦር ቀጠና ውስጥ ኾኖ፣ የትኛውም የእርዳታ ድርጅቶች አድመው የማይገቡበት አካባቢ፣ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የማንገናኝበት አካባቢ ተፈጥሮ የሰው ዘር ይተርፋል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። እኔ ይሄን አደረኩ ብዬ የምነግርህም የለኝም። ሕዝቡ ያደረገውን ብናገር ነው የሚያምርብኝ የኾነውም ይሄው ነው።” ነው ያሉኝ አቡነ ኤርሚያስ። ተደጋግፈን እንኑር የሚለውን አስታወስናቸው፣ እነርሱም ያንኑ አደረጉት እንጂ እኔ ምንም አላደረኩም ነው የሚሉት። ትሁት ናቸውና ስለ ትህትና አደረኩ ማለት አይወዱም። “የሚለምኑትም ሲያስለቅሱ፣ የሚሰጡትም ያስለቅሳሉ ያለምንም ዋስትና የሚሰጡት ማመናቸው ነው።” አባ ኤርሚያስ የሕዝቡ ቸርነት ያስደንቃቸዋል። ሕዝቡ ሃይማኖት ሳይለየው ያለውን ይሰጥ ጀመር። እኒህ አባታችን ርሃብን ጠማን ሲሉ የነበሩ ዜጎች በአቡነ ኤርሚያስ ተጋድሎ በሕዝቡ ለጋስነት የሚጎርሱት አገኙ። ዘላቂ ግን አልነበረም። የተሰበሰበው ዱቄትና ሌላው ስጦታ አለቀ። ሌላ ረሃብ መጣ። አባታችን ርሃብን ጠማን የሚለው በድጋሜ በረታ። ብፅዕነታቸው ሳይሰለቹ ተነሱ፣ ባንክ ሳያስገቡ በየቤታቸው ብር ያስቀመጡ ካሉ ይሰጧቸው ዘንድ ጠየቁ። እርሳቸው ጠይቀው እምቢ እይባልምና ያለው እያወጣ እንደ አቅሙ ሰጣቸው። እርሳቸውም ለተቸገሩት ሰጧቸው። አቡነ ኤርሚያስ ለመጣው ሁሉ ስጡ እያሉ ለማንም ሳይለዩ ለተቸገሩት ሁሉ እንዲሰጡ አዘዙ። ለመስጠት የማይሰስቱ ኢትዮጵያውያን ሞልተዋልም ነው የሚሉት። ካጣነው ይልቅ ያገኘነው ይበልጣል። መረዳዳትን አይተናል፣ ኢትዮጵያንም አውቀናል ይላሉ አቡነ ኤርሚያስ የፈተናውን ጊዜ ሲያስታውሱ።
ኢትዮጵያ ማናት የሚለውን አውቀንበታልም ብለውናል። በተዘጋጋ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ንፁሐን የሕክምና ችግርም ፈተናቸው። ዜጎች በመድኃኒት እጦት ሞቱ። ለአቡነ ኤርሚያስም ይደርሱላቸው ዘንድ ጥያቄ አቀረቡላቸው። እሳቸው በጨለማ ቀን የተገኙ መብራት ናቸውና መንገዱ የጨለመበት ሁሉ ወደ እርሳቸው ይሄዳል። በእርሳቸው አማካኝነት መሻገሪያ መብራት ያገኛልና። እርሳቸውም ጠየቁ። ለክፉ ቀን እያለ በየቤቱ መድኃኒት ያስቀመጠው ሁሉ እየከፈለ ይሰጣቸው ጀመር። ፍርሃትም ድፍረትም ጠርዝ ሲለቅ መልካም አይደለም። በአግባቡ መድፈር በአግባቡም እንደ ሁኔታው መፍራት መልካም ነው ይላሉ። እነዚያ ወራሪዎች እየወረሩ ወደ ወልድያ ሲጠጉ አቡነ ኤርሚያስ እንግልት እንዳይደርስባቸው የሚፈልጉ ምዕመናን አባታችን አካባቢውን ለቀው ይውጡ እያሉ የሚጠይቋቸው ብዙዎች ነበሩ። በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም የሚኖሩ አባታችን ይውጡ እያሉ ለማሳመን ይጥሩ ነበር። “መራብና መጠማት መንገላታት እንደሚኖር ባስብም ምንም ቢሆን ስሜ እረኛ ነው። እረኛ የተባልኩት ደግሞ በእነዚህ በጎች ነው። የማገለግለው ሕዝብ በበግ ተመስሎ፣ እነርሱን እንዳገለግል የተላኩት ደግሞ በእረኛ ተመስዬ ነው። እናም በጎቹ በእንደዚያ አይነት አስደንጋጭ፣ የሀዘን፣ የጭንቀት ድባብ ውስጥ ኾነው፣ ኧረኛው ወጥቼ ብሄድ ምንድን ነው የሚሰማቸው? እኔስ ምንድን ነው የሚሰማኝ? በስጋ እፎይታ ላገኝ እችል ይኾናል ሕሊናዬ እንዴት ያርፋል?። “በፍፁም አላደርገውም አልኩ።” “የአቡነ ኤርሚያስ የማይሻር ፅኑ ቃል ነው። ቃላቸውን አሠሩ፣ ሳያዛቡ ተገበሩ። አቡነ ኤርሚያስ ዒላማ ይኾናሉ ተብለው በሌላ ቦታ የሚኖሩ ምዕምናን ሰጉ። እርሳቸው ግን አይኾንም አሉ። የሚመጣውን ስለ እውነት ሊቀበሉ በፅናት ቆሙ። “መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ ያኖራል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የርሱ ያልኾኑ ሞያተኛ ግን ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል ። ተኩላም ይነጥቃቸዋል። በጎቹንም ይበትናቸዋል። ሞያተኛ ስለሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል” እንዳለ መፅሐፍ መልካም እረኛ ናቸውና ስለ በጎቹ ኖሩ፣ በጎቻቸውን ተኩላ እንዳይነጥቅባቸው ሳይታክቱ ታተሩ። ነጣቂው ተኩላ ቢበረክትም እርሳቸው ግን በትጋት ጠበቁ።
አቡነ ኤርሚያስ በትህትና፣ በታላቅ አባታዊ ፍቅር አገለገሉ። የማይተኛውን አምላካቸውን እየተማፀኑ ሳይተኙ አገለገሉ። በሕዝብ ላይ የተነሱት የሚጎዱት እራሳቸው መሆናቸውን አቡነ ኤርሚያስ ይናገራሉ። የሽብር ቡድኑ አባላት መጀመሪያ ሲገቡ ከሕዝብ ጋር ፀብ የለንም፣ እኛ መንግሥትን ይዘን ሥርዓቱን መቀየር ነው ይላሉ። ቆይተው ግን ክፋታቸውን ያመጣሉ። እንግልቱን ያበዙት ነበር፣ የቤተክህነት ተማሪዎች ሳይቀር ተገደሉ። የቤተ ክህነት ተማሪዎችን በእቃ ላይ እንደሚጫወቱ እየተሳሳቁ ገደሏቸው። ሀብት እየተዘረፈ ወደ ትግራይ ተጫነ። የእርሳቸውን መኪናም ጫኑት። አቡኑም ሀብት እንዳይዘረፍ፣ ልጆቻቸው በረሃብ እንዳያልቁ፣ በግፍ እንዳይገደሉ ታገሉ። መከራውን ማየት መስማት ለመልካሙ እረኛ ከባድ ነበር። ከአዕምሮዬ የማይጠፋ በደሎችን አይቻለሁም ነው ያሉት። ለእርሳቸው ግን ትልቁ ሕመም የዜጎች መጎዳት ነበር።
አቡነ ኤርሚያስ በዘመናቸው እንደዚህ አይነት ፈታኝ ጊዜ አላዩም። በጦርነት ውስጥ ብዙ ንፁሐን በተለያየ መንገድ ሊሞቱ ይችላሉ። በጦርነቱ እጃቸው የሌለበት ንፁሕንን የሚያጠቃ በደል ግን አይቼ አላውቅም፣ አላነበብኩምም ነው የሚሉት። ከሽብር ቡድኑ አባላትም በግዴታ የሚመጡ ነብሳቸውን ለማውጣት ሲከዱ መመልከታቸውንም ያስታውሳሉ። በፈጸሙት ግፍ የትግራይን ሕዝብ ነው የጎዱት። እነርሱ ለትግራይ ሕዝብ እሳት ጭረው እሳት ጭነው ወሰዱለት። የእኔን መኪና ሲወስዱት የአንዲትን ቤተ ክርስቲያን ሀብት መውሰድ አይጠቅማችሁም፤ ኪሳራ ነው የሚያደርስባችሁ ብዬ ለምኜ ነበር። ከገንዘብ ጋር ባላቸው አቋም ፍንክች የማይል ነውም ነው ያሉት። ቀናት ተቆጠሩ፣ ሳምንታት ተከተሉ፣ ወራት ቀጠሉ፣ መልካሙ እረኛ በተጋድሏቸው ቀጠሉ። በፅናት እና በትጋት ጊዜውን አሳለፉት።
አባታችን እያሉ ከሥራቸው የማይጠፉትን ወገኖች ልጆቼ እያሉ አፅናኗቸው፣ በፈጣሪያቸው መልካም ረዳትነት ክፉውን ቀን አሻገሯቸው። በሰላም ቀንም ተገናኝተው አባታችን ልጆቼ ተባባሉ። ፍቅራቸው በማይረሳ፣ በማይሻር ማሕተም ላይ አርፏልና። በፅናት እንዳገለገሏቸው ሁሉ ሳይሰስቱ ይወዷቸዋል። በወልድያ ጎዳናዎች እየተመላለሰ ወጎችን ለሚሰማ ሁሉ የወግ መጀመሪያም የወግ መጨረሻም የሆኑ፣ በሁሉም ዜጎች ምስጋና የሚቸራቸው አንድ አባት አሉ። እርሳቸው ባይኖሩ እናልቅ ነበር፣ እርሳቸው ባይኖሩ መከራውን ባላሰለፍነው ነበር፣ መከራውን እናሳልፈው ዘንድ እርሳቸው ተሰጡን የማይላቸው የለም።
ሃይማኖት ሳይለዩ አባታችን ይሏቸዋል። ክፉዎች ከክፉ ልባቸው መዝገብ ክፉ ነገር አደረጉ፣ በደልን ፈፀሙ፣ እርሳቸው ግን እውነተኛውን ተጋድሎ ተጋድለውታል። ትዕዛዛቱን ጠብቀውታል። የመከራውን ቀን በፅናት አሳልፈውታል። መጠለያ ላጡት መጠለያ፣ መሻገሪያ ላጡት መሻገሪያ ኾነው አሻገሩ። ስለ ትህትና ፣ ስለ እውነት በእውነት፣ የእውነት አደረጉ። ያንም ቀን አሳልፈው ለመልካሙ ቀን ደረሱ። ክፉውን ጊዜ በመልካምነት አሸነፉት። በትህትና በደግነት ተሻገሩት። ተከታያቸውን ሕዝብ አሻገሩት። ከአጠገባቸው ተቀምጬ በቆየሁባት ጊዜ እልፍ ትህትናቸው ደነቀኝ፣ አክብሮታቸው አስደመመኝ። እንደ እርሳቸው አይነት ታላቅ ዋርካ ኢትዮጵያ እንዲበዙላት ተመኘሁ።
በታርቆ ክንዴ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
