ጀግኖችን እናክብር፣ እንዘክር፣ ጀግኖችም እንሁን!

250

ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ለሀገራቸው በጀግንነት መስዋእትነት ከፍለው ላለፉ ጀግኖች ተገቢውን ክብር መስጠትና በቋሚነት እንዲታወሱ ማድረግ እንደሚገባ ሀገራቸው ላቀረበችላቸው ጥሪ በጎ ምላሽ የሰጡ የቀድሞ አየር ኀይል አብራሪ የዲያስፖራ አባላት ተናገሩ፡፡
ኢትዮጵያ ከተፈተነችባቸው ታሪካዊ አጋጣሚዎች መካከል ዚያድባሬ ኢትዮጵያን በመውረር የተካሄደው ጦርነት አንዱ ነው፡፡ ታላቋን ሱማሊያ የመመሥረት ቀቢጸ ተስፋ የሰነቀው የዚያድ ባሬ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመውረር ሰፊ የሰው ኀይል፣ የትጥቅ፣ የስንቅ እና የሥነ ልቦና ዝግጅት አደረገ፡፡ በውጪ ኀይሎችም ድጋፍ ስላገኘ የተሟላ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታጥቆ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡ ከ1969 ዓ.ም የክረምት ወራት ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ያወጀው ዚያድ ባሬ በምሥራቅና በደቡብ በኩል የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ጥሶ ገባ፡፡
በታሪካቸው ለጠላት እጅ ሰጥተው የማያውቁት የኢትዮጵያ ልጆችም ሀገራቸውን ሊታደጉ ከያሉበት ተጠራርተው በካራማራ ሰንሰለታማ ተራራዎች ተገኙ፡፡ በዚያም ጠላትን መድረሻ አሳጡት፡፡ እኒያ ተራራዎች በኢትዮጵያ ምድር ጦር እሳተ ገሞራ የፈነዳባቸው መሰሉ፡፡ የጦር ጀቶችም በጀግኖቹ ላንቃቸውን ከፍተው የሮኬት እና የቦንብ መብረቃቸውን ማዝነብ ቀጠሉ፡፡ የዚያን ጊዜ ለወረራ የገባው የሶማሊያ ጦር አደጋ ውስጥ ወደቀ፡፡ ከ15 ቀናት ባልበለጠ ውጊያ የሶማሊያ የጦር ኀይል መመናመኑንም ታሪክ ከትቦታል፡፡
በጦርነቱ ታላቅ ጀብድ ከፈጸሙ እንቁ የኢትዮጵያ አየር ኀይል ተዋጊ ጀት አብራሪዎች መካከል ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህ ይጠቀሳሉ፡፡ በምዕራብ ጎጃም ዞን መራዊ ከተማ ተወልደው ያደጉት ኮሎኔል ታደሰ ከልጅነታቸው ጀምሮ በነበራቸው ፍላጎት የአየር ኀይልን ተቀላቅለዋል፡፡ የበረራ ትምህርታቸውን በሀገር ውስጥ፣ በእስራኤል እና በሶቭየት ኅብረት ከተከታተሉ በኋላ በርካታ ግዳጆችን በመወጣት ሀገራቸውን በጀግንነት አገልግለዋል፡፡
በምሥራቅም ሆነ በሰሜን ግንባር ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉ የኢትዮጵያ ባለውለታ ናቸው፡፡ በተለይ በዚያድ ባሬ ወረራ ጊዜ በአየር ላይ ውጊያ ሀገራቸውን ከጥቃት በመታደግ የማይረሳ ታሪክ ሠርተዋል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ የጦር ጀቶች የሶማሊያን የአየር ክልል ጭምር ጥሶ በመግባት የማሰስና የማደባየት ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ እናም ኢትዮጵያ የሶማሊያን ጦር ድል ስታደርግ የኮሎኔል ታደሰ ሚና ጉልህ ነበር፡፡
በኋላማ ሀገራዊ አንድነትን በማቀንቀናቸው ብቻ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ካሳደዳቸው የሀገር ባለውለታዎች መካከል አንዱ በመሆናቸው ወደ ኬንያ እና ዩጋንዳ ተሰድደዋል፡፡ ከዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ የስርዓት ለውጥ ለማድረግ የጀግኖች አርበኞች ግንባርን መሥርተው በኤርትራ በርሃ ሲታገሉም ቆይተዋል፡፡ ከዚያም ኢትዮጵያውያን ባቀጣጠሉት አመጽ ሀገራዊ ለውጥ በመገኘቱ ከዓመታት ትግል በኋላ ወደ ሀገራቸው ገቡ፡፡ ነገር ግን ሕመም ጸንቶባቸው ስለነበር ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ውጪ ሀገር በተጓዙበት ሕይወታቸው አልፏል፡፡
ኮሎኔል ታደሰን በቅርበት የሚያውቋቸው የትግል አጋሮች እና ተማሪዎቻቸው ፍጹም ሀገር ወዳድ፣ አስተዋይ፣ ደፋር፣ አርቆ አሳቢ እና መልካም ስብዕና የተጎናጸፉ እንደነበሩ መስክረዋል፡፡ በነበራቸው የሥራ ተነሳሽነት እና አፈጻጸም በተለይም በጦርነቱ በሠሩት ጀብድ ትልቁን ‹የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የጀግና ሜዳልያ› ሽልማት ማግኘትም ችለዋል፡፡ ለነበራቸው ተጋድሎ እና ለሠሩት ታሪክ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ በስማቸው ትምህር ቤትም ተሰይሟል፡፡
በአሜሪካ የሚኖሩት የቀድሞ የአየር ኀይል አባላት ካፒቴን ክንዴ ዳምጤ፣ ሻምበል ሶሎሞን መንግሥቱ እና ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ የኮሎኔል ታደሰ የትግል አጋሮች ናቸው፡፡ በምስራቁ የጦር ግንባር ጭምር አብረዋቸው የዘመቱ ሲሆን በመታሰቢያቸው ትምህርት ቤት ተገኝተው አስታውሰዋቸዋል፡፡ የሠሩትንም ታላቅ ሥራ ዘክረዋል፡፡ ታሪክ ለሠሩ የሀገር ባለውለታዎች ተገቢውን ክብር መስጠት፣ ታሪካቸውን መዘከርና በቋሚነት እንዲታወሱ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
በኮሎኔል ታደሠ በስማቸው ትምህርት ቤት መሰየሙ እንዳስደሰታቸውም በመግለጽ ታሪካቸው በሰነድ መልክ ተዘጋጅቶ ለትውልድ እንዲደርስ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉም አመላክተዋል፡፡
የቀድሞ የአየር ኀይል አባላቱ እንዳሉት የሕልውና ዘመቻው ተጀመረ እንጂ ገና አልተጠናቀቀም፡፡ ኢትዮጵያ ከፊቷ ብዙ ትግል ይጠብቃታል፡፡ እናም ወጣቱ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በመካተት በልዩ ልዩ ሙያ ዘርፎች ሰልጥኖ ሀገሩን ከማንኛውም ጥቃት ሊታደግ ይገባል፡፡ በተለይ በአየር ኀይል ውስጥ በመካተት የኮሎኔል ታደሰን ታሪክ እንዲደግም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous article“ከድል በኋላ ያሉ ድኅረ ድል መዛነፎችን ማረም እና የጋራ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ ነው” አቶ ተመሥገን ጥሩነህ
Next article“እርሳቸው ግን እውነተኛውን ተጋድሎ ተጋድለውታል”