
ታኅሣሥ 21/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው ተቋማት መካከል የጤና ተቋማት ተጠቃሾች ናቸው። የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም በሽብር ቡድኑ የወደሙ ተቋማትን ተዘዋውረው ምልከታ አድርገዋል። የጤና ተቋማት እና የጤና ባለሙያዎች በጦርነት ጊዜ ደኅንነታቸው መጠበቅ እንዳለበት ዓለም አቀፍ ሕጉ ይደነግጋል። ይሁን እንጅ የሽብር ቡድኑ እነዚህን የጤና ተቋማት ዒላማ በማድረግ አውድሟል።
የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኀላፊ መልካሙ አብቴ (ዶክተር) የሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል በወረራቸው አካባቢዎች 40 ሆስፒታሎችን፣ 453 ጤና ጣቢያዎችን፣ 1ሺህ 850 ጤና ኬላዎችን፣ አራት የደም ባንክ፣ በየወረዳዎች የሚገኙ የጤና ጽሕፈት ቤቶችን እና ለምስራቅ አማራ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባውን የኦክስጅን ማምረቻ ማውደሙን አንስተዋል። የሽብር ቡድኑ የሚችለውን የሕክምና መሳሪያዎች እና ግብዓቶች ዘርፏል፤ ማንቀሳቀስ ያልቻለውን ደግሞ አገልግሎት እንዳይሰጡ አውድሟል። የደረሰው ውድመትም ሰፊ እንደሆነ ነው ዶክተር መልካሙ የገለጹት።
አሁን ላይ መሠረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ለማስጀመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ ነው። በዚህም መሠረት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሆስፒታሎች እርስ በርሳቸው እንዲደጋገፉ፣ አዲስ አበባ እና ሌሎች ክልሎችም አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። ሌሎች አጋር አካላትም ለማገዝ ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል። በውጭ ከሚኖሩ ዲያስፖራዎች ጋርም በጋራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። በዘላቂነት የማቋቋሙ ሥራም እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል። የመልሶ ማቋቋሙ እንቅስቃሴ ተቋማቱ ሲሰጡ የነበረውን አገልግሎት ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን ቀደም ብለው ይሰጡት ከነበረው አገልግሎት በተሻለ መልኩ ሕዝብን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ታላሚ ተደርጎ እየተሠራ ስለመሆኑ አንስተዋል። መተባበር፣ መደማመጥ እና አብሮ መሥራት ከተቻለ ደግሞ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/
