በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ማዕከል ጽሕፈት ቤት የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን አስመልክቶ የያዘውን ፖሊሲ ዳግም እንዲያጤነው ጠየቀ።

247

ታኅሣሥ 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ማዕከል ጽሕፈት ቤት የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን አስመልክቶ የያዘውን ፖሊሲ ዳግም እንዲያጤነው ጠይቋል።

ጽሕፈት ቤቱ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ደብዳቤ ጽፏል፡፡

በደብዳቤውም በሰሜን ኢትዮጵያ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የአሜሪካ መንግሥት እየተከተለ ያለው አካሄድ ለሽብር ቡድኑ ሕወሓት የወገነ አድሏዊ አካሄድ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የጣለው ማእቀብ እንዲሁም ሀገሪቱን ከአጎዋ (ከቀረጥ ነጻ የንግድ ሥርዓት) ዝርዝር የማስወጣት ተግባር ዳግም መታየት እንዳለበት ጠይቋል።

አሸባሪው ሕወሓት የፈጸመው ወንጀል ዓለም አቀፍ ሕጎችን የጣሰ መሆኑንም በደብዳቤው ተነስቷል።በአለፉት ጊዜያት አሸባሪው ሕወሓት በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ወንጀል ከሀገር ውስጥና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ዓለምአቀፍ ተቋማት ካወጧቸው ሪፖርቶች ሲከታተል የቆየ መሆኑን በደብዳቤው የገለጸው አህጉረ ስብከቱ የሽብር ቡድኑ ጅምላ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የመሰረተ ልማት ውድመት፣ ሕጻናትን መግደል፣ ሕጻናትን ለውጊያ ማሰማራት፣ እናቶችን፣ አቅመ ደካሞችንና የሃይማኖት አባቶችን እንደ አጠቃላይ በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን ገልጿል፡፡

የሽብር ቡድኑ የፈጸመው ወንጀል በግልጽ የሚስተዋል ሆኖ ሳለ የአሜሪካ መንግሥት እንዳላየ መሆኑ ሰብዓዊነትን ችላ ያለ ድርጊት መሆኑን በደብዳቤው አመላክቷል።

በደብዳቤውም፡-

– ዘግናኝ ግፎችን እየፈጸመ ያለው የሽብር ቡድን በተመለከተ የአሜሪካ መንግሥት ድርጊቱን ለምን እንደማያወግዝና ለምን ማእቀብ እንደማይጥል ጠይቋል

– አሸባሪ ቡድኑ በአማራና በአፋር ክልሎች የፈጸመውን ወንጀል አስመልክቶ የሚደረገውን ምርመራ የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን/አለመሆኑን

– የአፍሪካ ሕብረት ነጻና ፍትሐዊ በሚል እውቅና የሰጠውን ሀገራዊ ምርጫ ውጤት አሜሪካ ለምን እንደተቃወመች

– የብዙዎችን ኢትዮጵያዊያን ህይወት እንደሚጎዳ እየታወቀ የአሜሪካ መንግሥት ለምን ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት እንደሰረዘ

– አዲስ አበባ ሰላም እንደሆነች እየታወቀ ለምን የአሜሪካ መንግሥት አዲስ አበባ እንደተከበበች በማስመሰል ዜጎች ለቀው እንዲወጡ በተደጋጋሚ እንደጠየቀ

– በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ሕወሓት ከአማራና ከአፋር ክልሎች በደረሰበት ሽንፈት ተጠራርጎ ወጥቷል። በመሆኑም በሁለቱ ክልሎች ለደረሰው ጉዳት የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ ስለመሆኑም ተጠይቋል፡፡

አህጉረ ስብከቱ ቀደም ሲል የተጠየቁ ጥያቄዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የያዘውን አቋም ድጋሚ በማጤን አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራትን ወዳጅነት ለማስቀጠል ሰፊ እድል ያለ መሆኑን አህጉረ ስብከቱ ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በላከው ደብዳቤ ገልጿል።

በፈረደ ሽታ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ 4 ሚሊዬን ብር ድጋፍ አደረገች፡፡
Next articleበሽብር ቡድኑ የወደሙ የጤና ተቋማት ቀደም ብሎ ይሰጡት ከነበረው አገልግሎት በተሻለ መልኩ ሕዝብን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ገለጸ።