
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ዲያስፖራዎችን ቆይታ የተሳካ ማድረግ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ መርኃ ግብሮች መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ዛሬ ለዲያስፖራው ማኅበረሰብ የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሃ ግብር አዘጋጅቷል፡፡ በመርኃ ግብሩ ዲያስፖራዎች ሀገራቸው ላቀረበችላቸው ጥሪ የሰጡት በጎ ምላሽ የሚያስመሰግን መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲቫ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያቀረበችው ጥሪ ሀገርን መውደድ በተግባር የሚረጋገጥበት የጀግንነት ጥሪ ሲሆን የተሰጠው ምላሽም የሚያስደስት ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ የተነሱ የውስጥና የውጪ ኀይሎች እውነቱን አዛብተው የሀሰት ክስ መስርተው ጦርነቱን ዘርፈ ብዙ ቢያደርጉትም ኢትዮጵያውያን ከያሉበት ተሰባስበው ‟በቃ“ በማለት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል፡፡ ጉዳዩን አፍሪካዊ ንቅናቄ በማድረግም ታሪክ የማይረሳው አሻራ መጣላቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በመላ ልጆቿ ጥረትና ተጋድሎ አሸንፋለች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው ሀገሪቱን ለቅቃችሁ ውጡ የሚል ሀሰተኛ መረጃ በሚሰራጭበት ጊዜ የማይበገሩት ልጆቿ ወደ ሀገራቸው ገብተው የሀሰት ንግግሩን አምክነዋል፤ ይህም የሀገራቸውን ተጨባጭ ሁኔታ ለመመስከር ያስችላል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ የተሠራችበት ውቅር ከዓለም አቀፍ መገለጫዎች የተለዬ ያደርገዋልም ብለዋል፡፡ ከንቲባዋ “ዲያስፖራው ባይተዋርነት ነግሶበት ወደ ሀገሩ ለመግባት ፈተና የነበረበት ጊዜ አልፏል፡፡ አሁን ድልድዩ ተገንብቶ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በእናት ሀገራቸው ጉዳይ በጋራ ቆመዋል፡፡ በአድዋ ጦርነት ወቅት በአንድነት ዘምተው ድል አድርገዋል፡፡ ዛሬም ከመላ ዓለም የተንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያን የፍቅር ጥሪውን ተቀብለው መግባታቸው ለትውልድ የሚተላለፍ ልዩ ታሪክ ነው” ብለዋል፡፡
አዲስ አበባም እጆቿን ዘርግታ እንግዶቿን በሰላም እየተቀበለች ሲሆን ቆይታቸው የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ ልዩ ዝግጅት መደረጉንም አብራርተዋል፡፡ የአፍሪካ መናገሻ በሆነችው አዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ ደስተኛ እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተዘጋጀ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ በስምንት ቦታዎች ኤግዚቪሽን እና ባዛር ተዘጋጅቷል፡፡ ልዩ ልዩ ቦታዎችን እንዲያዩ፣ በኢንቨስትመንት እና በልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች እንዲሳተፉ ለማድረግም እቅድ ተይዟል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
