
ወልድያ፡ ታኅሣሥ 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ወሎ ዞን ግዳን ወረዳ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በየአቅጣጫው የዘረፈውን ሃብት ለማሸሽ እንደመሿለኪያ ሲጠቀምበት የነበረ ስትራቴጂካዊ ቦታ ነው። ጠላት በሕዝብ ማዕበል ቢንቀሳቀስም የወገን ጦሩ በጋሸና፣ በላል ይበላ፣ በደሴ እና በወልድያ  ያደረገውን መጠነ ሰፊ የማጥቃት እርምጃ መቋቋም ሲያቅተው በግዳን ወረዳ ለመሹለክ ጥረት አድርጓል፡፡ ይሁን እንጅ የግዳን ወረዳ ጀግኖች ከወገን ጦር ጋር የገባውን ጠላት መደምሰሳቸውን ነው የአካባቢው ጀግኖች የሚናገሩት፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን ግዳን ወረዳ ነዋሪው እና በትግሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው አቶ ገሰሰ ይርዳው እንዳሉት አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ ለሚያደርገው ወረራ ግዳን ወረዳን እንደመውጫ በር እየተጠቀመበት መሆኑን የተረዳው የአካባቢው ጀግና ጠላትን እረፍት በመንሳት በገባበት እንዲቀር በማድረግ ታሪክ የሚከትበው ሥራ ሠርቷል፡፡
አቧሃይ ጋራ እና ዞብ አምባ የተባሉ ቦታዎችን ሰብሮ ለመግባት ሙከራ ያደረገው ጠላትም በዛው መቅረቱን ነው አቶ ገሰሰ የነገሩን፡፡ በሕዝባዊ ማዕበል ወደ አካባቢያቸው የገባው ወራሪ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ እስኪወጣ በቀየው የግል እና የመንግሥት ተቋማት ላይ ዝርፊያ እና ውድመት በማድረስ የበቀል እና የጥላቻ በትር ማሳረፉንም አስረድተዋል፡፡
ወራሪ ቡድኑ የሚፈጽመውን ዝርፊያ እና ውድመት ለመከላከል የአካባቢው ጀግኖች ለአካባቢው ወጣቶች አጭር ስልጠና በመስጠት ጠላት በገባበት ገብቶ እንዲቀበር ትልቅ ትግል ማድረጋቸውንም ነው ያስረዱት፡፡
ሌላው የአካባቢው ነዋሪ እና የትግሉ አንቀሳቃሽ ሃምሳአለቃ አብርሃም ያረጋል ወጣቶቹ ከግዳን ወረዳ በቅርብ ርቀት በሚገኙ አካባቢዎች ማለትም በድልብ፣ ቦንዳይ፣ አሮጌ አምባ እና በመሳሰሉ ቦታዎች ጠላትን  እረፍት በመንሳት እንዲደመሰስ የተጫወቱት ሚና ትልቅ እንደነበርም ነው የነገሩን። በመደራጀት የተንቀሳቀሱት የግዳን ወጣቶች መኪና ማርከዋል፣ በርካታ የግል እና የቡድን መሣሪያ ነጥቀው መታጠቃቸውንም አብራርተዋል።
የግዳን ጀግኖች ከሞት የተረፈው ጠላት ለማምለጥ ያደረገውን ጥረት በቀበሮ ሜዳ ጠብቀው ከፍተኛ ኪሳራ እንዲደርስበት አድርገዋል። አቶ ገሰሰ መደራጀት፣ መሰባሰብ እና በጋራ መጓዝ ጠላትን ድል ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበረው  በትግሉ መገንዘባቸውንም ነው የጠቆሙት። ጀግንነት፣ ወኔ፣ ትጥቅ እና ስንቅ ላስታጠቁ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ባለሃብቶች፣ ነጋዴዎች እና የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ምስጋና እንደሚገባቸውም ነው የገለጹት።
አሚኮ ያነጋገራቸው አብዛኛዎቹ የግዳን ወረዳ ወጣቶችም ሃምሳአለቃ አብርሃም እና ጓደኞቹ በትግሉ ሲያደርጉት የነበረው እገዛ ለወጣቱ ጀግንነት እና ወኔ ያበረከተው አስተዋጽኦ ትልቅ ነበር ብለዋል።
ዘጋቢ፦አዳሙ ሾባባው-ከግዳን ወረዳ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
            
		