
ታኅሣሥ 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ የሀገር ቤት ጉዞ ጥሪ” ተቀብለው ለመጡ ዳያስፖራዎች የአቀባባል ሥነ ሥርዓት በወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል፡፡
በእንኳን ደህና መጣችሁ መርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በየዘመኑ በውድ ልጆቿ ትብብር እና አይበገሬነት ፈተናዎችን የምትሻገረው ኢትዮጵያ ዛሬም በትውልድ ቅብብሎሽ በእናንተ ጥረት ታፍራ እና ተከብራ ቀጥላለች ብለዋል፡፡
“#በቃ” ወይም “#NoMore” በሚል ትብብር እና አይበገሬነት በመላው ዓለም ያደረጋችሁት ትግል አድሏዊ የሆነውን የዓለም ክፍል እራቃኑን አስቀርታችሁታል ያሉት አቶ ደመቀ ለዳግም የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መንስኤ በመሆናችሁ ሀገራችሁ ኮርታለች ነው ያሉት፡፡
ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተናበው የኢትዮጵያን ክብር እና ኩራቷን ለማርከስ የሞከሩ የውስጥ ከሃዲዎች ሁሉ ከሕይዎታቸው ይልቅ ለሀገራቸው ቅድሚያ በሚሰጡ ውድ ልጆች ስጋቱ ተቀልብሷል ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት የመጡ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ሁሉ የሽብር ቡድኑ ያደረሳቸውን አሳዛኝ፣ አስነዋሪ እና ጸያፍ ድርጊት እንደሚመለከቱ ገልጸው በየአካባቢው የሚኖሩት ወገኖቻችሁ በመልሶ ግንባታው ሂደት የእናንተን ድጋፍ ይሻሉ ነው ያሉት፡፡
በሐሰት የሽብር መርዶ ስትናጥ የሰነበተችው ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ እንዴት በፍቅር እና በመከባበር እንደሚኖሩባት ትታዘባላችሁ ያሉት አቶ ደመቀ “በቆይታችሁ የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም የፍትሕ አደባባይ የሚገልጽ የዲፕሎማሲ ስንቅ ታገኙበታላችሁ” ብለዋቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
