ከጥንታዊቷ እስከ ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ በተለያየ ዘርፍ ለተጉ የሀገር ባለውለታዎች “የአጼዎቹ” ሽልማት ይበረከታል፡፡

260

ታኅሣሥ 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በመላው ዓለም ያሉ የባለተስፋዋ ምድር ልጆች የመሪያቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ነው፡፡ መከራን በጽናት፤ ፈተናን በትዕግስት እየተሻገረች የምትገኘው ኢትዮጵያ በድል ማግስት ልደትን እና ጥምቀትን ከልጆቿ ጋር በጋራ ለማክበር “ኑ አብረን እንዋል” ብላቸዋለች፡፡ ጥሪዋን የተቀበሉት ልጆቿ እና ወዳጆቿም ወደ ሀገራቸው መግባት ጀምረዋል፡፡ በዚህ የአብሮነት እና የአጋርነት መርኃ ግብር ትናንት ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲዖል ለመውረድ ያለሙትን ባንዳዎች እኩይ ተግባር ያመከኑ ጀግኖች ከሀገር ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እውቅና ያገኛሉ፡፡ ስለሀገራቸው ነፃነት ሲሉ ዋጋ የከፈሉ ጀግኖች የወደቁባቸው እና የተነሱባቸው የትናንት የጦርነት አውድማዎች ከውጭ በመጡ ልጆቿ እና ወዳጆቿ ነገ ይዘከራሉ፡፡
ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር ኢትዮጵያን ለመፈተን ቆርጠው የተነሱ የትሮይ ፈረሶችን ምኞት ያመከኑ እነዚያ በውጭ ያሉ የሳይበር አርበኞች ነፍጥ አንስተው ጠላቶቻቸውን ድባቅ ከመቱት የዘመኑ ጀግኖች ጋር በሀገራቸው ምድር ላይ ተገናኝተው በፍቅር ይተቃቀፋሉ፡፡
ከማይካድራ እስከ ጭና፣ ከድሬ ሮቃ እስከ ኮምቦልቻ፣ ከሽዋ ሮቢት እስከ ነፋስ መውጫ፣ ከሰቆጣ እስከ ቆቦ ለሀገራቸው ነፃነት ሲሉ ክቡር ሕይዎታቸውን የሰጡ ሰማዕታት በወንድሞቻቸው ይዘከራሉ፡፡
ኢትዮጵያዊያኑ እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በመጀመሪያው ዙር መርኃግብር ጉብኝታቸው መነሻቸውን በመዲናቸው አዲስ አበባ አድርገው ከሽዋ እስከ ወሎ፣ ከየጁ እስከ ዋግ፣ ከላስታ እስከ በጌምድር አካለው በውቢቷ ባሕር ዳር ለረፍት ይከትማሉ፡፡
የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኅላፊ አቶ ጣሂር ሙሐመድ ሁለተኛው ዙር የጉዞ መርኃ ግብር ጥር 9/2013 ዓ.ም እንደሚጀምር ገልጸው ኢትዮጵያዊያኑ እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ጎንደር ለፍቅር እና ለምስጋና ያቀናሉ ብለውናል፡፡ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ቀያሽ እና ጥበበኛ መሪ የነበሩት የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ሹሩባ ወደ መናገሻቸው ጎንደር በሚገባበት ማግስት ጎንደርን እና አካባቢዋን የሚጎበኙት ኢትዮጵያዊያኑ “ጥምቀትን በጎንደር” ጨምሮ በበርካታ ዝግጅቶች እና በበርካታ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡
ከጎንደር ወደ ዳባት፤ ከዳባት ወደ ደባርቅ ጉዞ የሚያደርጉት ኢትዮጵያዊያኑ እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በአፍሪካ ጣሪያ ራስ ደጀን አካባቢ ተሰባስበው “የአፍሪካ ካሜሎት” ያንን ወርቃማ ዘመናቸውን በሐሴት ይዋጃሉ፡፡
ጭናን አይተው ወገኖቻቸውን አጽናንተው ማደሪያቸውን ጎንደር ካደረጉ በኋላ የለውጡ መነሻ እና የአማራ ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ወደ ሆነችው ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በቀጣዩ ቀን ያቀናሉ፡፡ ከተከዜ ወንዝ ዳር የከተመችውን የፍቅር ከተማ ሁመራን ማዕከል አድርገው ከማይካድራ እስከ ወልቃይት፤ ከዳንሻ እስከ ወፍ አርግፍ አካባቢውን ጎብኝተው፣ ጀግኖቻቸውን አግኝተው እና ስለሀገራቸው የተሰውትን ሁሉ ዘክረው ዳግም ወደ ጎንደር ይመለሳሉ፡፡
ጥር 11/2014 ዓ.ም ምሽት ከምንትዋብ ግምብ ግርቤ፣ ከጃንተከል ዋርካ፣ ከመይሳው ሰማይ ስር እና ከፋሲል መናገሻ ማማ ላይ ሆነው ጎንደሮች “በንጉሥ እራት” እንግዶቻቸውን ይቀበሏቸዋል፡፡ እንግዶቹም በጎንደር አጋፋሪዎች የተጉበት የንጉሥ እራት ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡ በዚሁ መርኃ ግብር ላይ “የአጼዎቹ ሽልማት” ይከናወናል ያሉት አቶ ጣሂር ከጥንታዊቷ እስከ ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ በተለያየ ዘርፍ ለተጉ የሀገር ባለውለታዎች ሽልማት ይበረከትላቸዋል ነው ያሉት፡፡ መርኃ ግብሩም እስከ ጥር 13/2014 ዓ.ም በይፋ እንደሚዘጋ አቶ ጣሂር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleዳያስፖራው የተለያዩ መረጃዎች የሚያገኝበት ማዕከል ወደ ሥራ ገባ።
Next articleየጦላይ የከፍተኛ ባለ ሌላ ማዕረግተኛ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሰልጣኝ ምልምል ወታደሮችን የሥልጠና ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት አካሄደ፡፡