ሰብዓዊነት እንዲህ ነው!

278

ባሕር ዳር፡ መስከረም 25/2012 ዓ/ም (አብመድ) ድርጊቱ የተፈጸመው በስፔን የባሕር ዳርቻዎች ነው፡፡ ሦስት ፖሊሶች ተጠርጣሪ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን ለመያዝ እያሳደዱ ነው፤ ፖሊሶቹ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የሚያሳድዷቸው ደግሞ በጀልባ ነበር፡፡
ተጠርጣሪዎቹም ፖሊሶችም በየራሳቸው ጀልባ ለማምለጥና ለመያዝ እየተሯሯጡ ነበር፡፡

የፖሊሶቹ ጀልባ ፍጥነቷን ጨምራ የተጠርጣሪዎችን ጀልባ ገጨቻት፤ ነገር ግን ተገጭ ከገጭ የበለጠ ጥንካሬ ነበራትና የፖሊሶች ጀልባ ተጎዳች፡፡

የፖሊሶች ጀልባ በደረሰባት ጉዳት መስመጥ ጀመረች፤ ፖሊሶቹም አብረው ወደ ጥልቁ ሊወርዱ ሆነ፡፡ ይኼኔ ተሳዳጆቹ ተጠርጣሪ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ወደኋላ ተመልሰው የፖሊሶቹን ሕይወት ታደጉ፤ ወደ ጀልባቸውም ስበው አወጧቸው፡፡

ከዚያም ሄሊኮፕተር መጥቶ በተሳዳጆቻቸው ሕይወታቸው የተረፉትን ፖሊሶች እና ተጠርጣሪዎችን ይዞ ሄደ፡፡ ፖሊሶቹ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው የተገለጸ ሲሆን አራቱ ተጠርጣሪዎችም ከሦስት ሺህ ኪሎ ግራም አሽሽ ጋር በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ሰብዓዊነት አይሎባቸው ፖሊሶቹን ታደጉ፤ ፖሊሶቹን ለመታደግም ራሳቸውን ለሕግ አሳልፈው ሰጡ፡፡

ምንጭ፡- ዩፒአይ
በአብርሃም በዕውቀት

Previous articleየሰሊጥ ምርቱ ጉዳት ሳይደርስበት እየተሰበሰበ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
Next articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ነገ ይጀምራል፡፡