
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጦርነት ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳቶችን ፈጥሮ ያልፋል፡፡ ነገር ግን ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ እውን አይሆንምና ምድር አያሌ ጦርነቶችን አስተናግዳለች፡፡ በጦርነት ደብዛቸው የጠፋ ጥንታዊ ስልጣኔዎች፣ የሰው ልጅ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ሃብቶች፣ የፈረሱ ከተሞች እና የወደሙ የመሰረተ ልማት አውታሮች ቢኖሩም አንዳንዶቹ ግን በመልሶ ግንባታ ለለውጥ እና ለእድገት የጀርባ አጥንት ሆነው የተሠሩ የድኅረ ጦርነት ትሩፋቶችን አይተናል፡፡
አሜሪካኖቹ ከሰባት አስርት ዓመታት በፊት ከአውዳሚ እና አድቃቂ ጦርነት በኋላ የገነቡት ሁቨር ዳም አሜሪካን እንዴት ከሞት አፋፍ እንደመለሳት ማሳያ ነው፡፡
ከ1931 እስከ 1936 እንደ ጎሪጎሪሳዊያኑ የዘመን ስሌት የተገነባው ሁቨር ዳም የፕሬዚዳንቷ ፍራንክሊን ሩዝቬልት እና ከጦርነቱ ማግስት ወገባቸውን ታጥቀው ለለውጥ የተነሱት አሜሪካዊያን ውጤት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ስያሜውንም ከሩዝቬልት በፊት ለነበሩት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኸርቨርት ሁቨር ማስታወሻ እንዲውል ተደርጓል፡፡ አሜሪካም አስከፊ ከሆነው የጦርነት ጉዳት ፈጥና ለመመለስ ይኽ ለመስኖ፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለጎርፍ መከላከያ እና ለውኃ እቀባ ዘርፈ ብዙ ግልጋሎት ያለው ግድቧ አይተኬ ሚና እንደተጫዎተ ይነገራል፡፡
ከጦርነት ማግስት እንደገና ለመነሳት መንገድ መሪ መንግሥት እና ቁርጠኛ ሕዝብ ብቻ ያስፈለጋቸው ሀገራት የመኖራቸውን ያክል ከቁዘማ ሳይወጡ ዘመናትን ያለፉም ታይተዋል፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች በከፈተው ጥላቻ የወለደው ጦርነት በርካቶችን ገድሏል፤ ተቋማት ወድመዋል፣ ተዘርፈዋል፡፡
በወረራው የደረሰው ውድመት አስከፊ ብቻ ሳይሆን አስተማሪ፤ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አነሳሽም ነው ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጉዳቱ ከአማራ እና አፋር ሕዝቦች አቅም ጋር ከታየ ግን ፈጥኖ ለመሳት ከባድ አይደለም ነው ያሉት፡፡
ከጦርነት በኋላ ካለፈ ድክመት ትምህርትን፣ ካለፈ ጥፋት ልማትን እና ካለፈ ጉዳት ብርታትን ማሳየት የጠንካራ ሕዝቦች እና መንግሥታት መለያ ነው የሚሉት ዲያቆን ዳንኤል ኢትዮጵያ ከዚህ ጦርነት በኋላ ጥንካሬዋ የሚታየውም በዚህ ዘርፍ እና ማዕቀፍ ነው ይላሉ፡፡
የወደሙ የመሰረተ ልማት ተቋማትን መልሶ መገንባት እና ወደ ቀደመ ማንነታቸው መመለስ አሸናፊ አያደርገንም፤ ይልቁንም ዳግም በማይወድሙበት ደረጃ ከቀድሞ ማንነታቸው በላይ ገንብቶ አሸናፊነትን መሳየት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
ዲያቆን ዳንኤል  ካለፈ የተጎጂነት ስሜት ወጥቶ በፍጥነት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ድርሻ የማይኖረው ኢትዮጵያዊ የለምና ሁሉም በየዘርፉ የራሱን አስተዋፅኦ በማበርከት ኢትዮጵያ የማትፈርስ ሀገር መሆኗን በተግባር ማሳየት ይገባል ነው ያሉት፡፡
ጥፋተኛ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ጥፋት ሆኖ የተሠራው የሽብር ቡድኑ  ሊያፈርሳት የሚፈልጋትን ኢትዮጵያ በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት የሚሻ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በጦርነቱ ወደተጎዱ አካባቢዎች በመዝለቅ ዐሻራውን ማስቀመጥ ይጠበቅበታልም ነው ያሉት ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
 
             
  
		