አነጣጥሮ ተኳሽ ጀግና የምትወዱ ከእነ አጅሮች ሀገር ራያ ውረዱ”

489

“አነጣጥሮ ተኳሽ ጀግና የምትወዱ
ከእነ አጅሮች ሀገር ራያ ውረዱ”

ታኅሣሥ 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አበው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደሃ ይሆናል፣ ነገር ግን የባርነት ጠባይ አለበት ብለው ጠላቶቹም ቢሆኑ አይመሰክሩም ይላሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በማጌጥ አይኮራም፣ የእርሱ ኩራት ከልብ የሚመነጭ ነው። የእርሱ ኩራት እንቁ መደርደር አይደለም፣ የእርሱ ኩራት ደካማነቱን ለመሸፈኛ የተዘጋጀ መጋረጃ አይደለም ። እርሱ ያለው በእምነት ላይ የተመሠረተ ጀግንነት ነው። ኢትዮጵያዊ ሰብዓዊ ክብርና ኩራት የጎደለው ሕይወት ለአፍታም እንኳን ለመኖር አይቀበልም ። ኩራት ከማይሰጥ ኑሮ ሞትን እመርጣለሁ የሚል ነው ኢትዮጵያዊ ይላሉ።

ኢትዮጵያውያን ከተዋረደ ሕይወት የኮራ ሞት ይሻላል ይላሉ። በክብር ወደ ሚሞቱበት እንጂ ተዋርደው ወደሚሸሹበት ፊታቸውን አያዞሩም። የክብር ሞት ወደ አለበት የገሰገሱት ሁሉ በጀግንነት ተዋድቀው ደማቅ ታሪክ ጽፈዋል፣ ጠላትን አሸንፈው የድል ችቦ አብርተዋል፣ በነፃነት ኖረዋል። ለልጅ ልጅ የሚያኮራ ታሪክ አስቀምጠዋል። ለክብር እና ለሀገር ፍቅር ሲሉ ጠላት ወደ አለበት ይገሰግሳሉ። ከጠላት ጋር ይተናነቃሉ፣ በድል ይመለሳሉ። ኢትዮጵያውያን በተሰለፉበት አውደ ውጊያ ሁሉ አሸንፈዋል። በድል አድራጊነት በኩራት ተመላልሰዋል።

አባቱ የሠራውን ታሪክ ልጁ እየደገመው፣ የልጅ ልጁ እየተቀበለው እና እያስቀጠለው የጀግንነት ታሪክ በኢትዮጵያ እንደ ምንጭ ውኃ ይፈስሳል። ጀግንነት ከሞላበት፣ ፍቅር ከሚፈልቅበት፣ ደግነት ካለበት፣ አንድነት ከሰፈነበት፣ ድል አድራጊነት ከልጅ ልጅ ከሚተላለፍበት ራያ ነኝ። ራያ ውስጥ ፈሪ አይፈጠርም። ፈሪም በሀገሩ አይኖርም። ራያ የሚኖረው በጀግንነት ፣ በአንድነት ፣ በአሸናፊነት ፣ በቆራጥነት ነው። ከነኩት እምብኝ ይላል። ከደፈሩት አንጥሮ ይተኩሳል፣ ግንባር ለይቶ ይበጥሳል።

ራያ ትዕግስቱ ጥልቅ ነው ይችላል፣ ራያ ፍቅር ነው ከጥል በፊት ሰላም ይቅደም ይላል፣ ራያ ሀገር ወዳድ ነው ቅድሚያ ለሀገር ፣ ቅድሚያ ለክብር ይላል። ይህን ሁሉ አድርጎ ትዕግስቱን ከተዳፈሩት በታገሰው ልክ ይቆጣል፣ ነብር ሆኖ ከየጎራው ይወጣል፣ ከትክሻው በማትለየው መውዜርና ክላሽ ባሩድ ያጠጣል። እንደ አንበሳ የጀገኑ፣ እንደ ነብር የፈጠኑ የራያ ጀግኖች ተቆጥተው ከተነሱ በኋላ የሚያቆማቸው እንደ ልማዳቸው ድል አድርጎ “ጉማ ” እያሉ መጨፈር ነው። ራያ እንኳን በክላሻቸውና በመውዜራቸው በመዋጣቸው አይቻሉም። ለዛም ነው
“በመዋጣ ዱላ ቢሰብረው ጉልበቱን ፣
ምነው ባልወለድሽኝ ብሎ አላት እናቱን” የተባለላቸው። በመዋጣ ዱላ ጉልበት ይሠብራሉ። በመዋጣ ዱላ ክንድ ያፈዝዛሉ።

ራያ ክላሻቸውን ወይም መውዜራቸውን፣ መዋጣቸው፣ ጩቤያቸው አይለያቸውም። በራያዎች ዘንድ ባዶ እጁን የሚንቀሳቀስ የለም። የአባቶቻቸው የራያ ልጆች ዛሬም የቀደመውን ጀግንነት አስቀጥለውታል። በቀያቸው የዘለቀውን ጠላታቸውን እያነከቱ መልሰውታል። ቀጥተውታል፣ በገባበት አስቀርተውታል። ጀግንነታቸውን አስቀጥለዋል። ወንድነታቸውን አሳይተዋል። ጠላታቸውን አሳፍረዋል።

አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በአካባቢው ወረራ ፈፀመ። ራያዎችም ቤታቸውን ረስተው ፣ መኖሪያቸውን በዱር፣ በምሽግ አድርገው ከጠላታቸው ጋር ተናነቁ። ጠላት በአካባቢው ተረጋግቶ እንዳያልፍ፣ ተረጋግቶ እንዳይኖር ፣ ተረጋግቶ እንዳያድር አደረጉት። በጨለማ እየተጓዙ ከጠላት ምሽግ እየገቡ ጠላትን እስኪበቃቸው ይደመስሱታል። ትጥቁን ይማርኩታል፣ የተረፈውን አውድመው ከጥቅም ውጭ ያደርጉበታል። ከዞብል ተራራ እየተነሱ ራያን እያካለሉ ጠላትን ድባቅ ይመቱታል። የትግራይ አሸባሪ ቡድንም ወደ ፊት መውጫ፣ ወደኋላም መመለሻ ፣ በዚያም መሰንበቻ አጣ።

“አነጣጥሮ ተኳሽ ጀግና የምትወዱ
ከእነ አጅሮች ሀገር ራያ ውረዱ” አነጣጥሮ ተኳሽ፣ ጀግኖችን የምትወዱ ወደ ራያ ሂዱ፣ ወደራያ አቅኑ፣ ራያ ውስጥ ፎክሮ ገዳይ፣ ሀገር አደላድይ ሞልቷልና። በጀግንነት የሚኖሩ፣ ኮርተው የሚያኮሩ ጀግኖች አሉና በጀግኖቹ ወኔ ይደሰታሉ። በጀግኖቹ ኩራት ይደመማሉ። በራያ ተራራዎች እየተመላለሱ፣ ሲሻቸው በሽምቅ ውጊያ ሲሻቸው በፊት ለፊት ውጊያ ጠላትን ከመቱ ጀግኖች ጋር ተገናኝቻለሁ።

ጀግኖቹ አማራ በተለያየ አቅጣጫ በጦር ሊወጋ ነው፣ ሁሉም አማራ ጦሩ እንዳይመታው ጋሻ መሆን አለበት ነው ያሉት። በአማራ አልፎም በመላው ኢትዮጵያ ላይ ጦር ሊወረውሩ የተዘጋጁ ጠላቶች ሞልተዋል። ሁሉም ጦሩን መመለሻ ጋሻ መያዝ እና የጠላትን ጦር በጋሻው እየመከተ ወደ ጠላት ጦር መወርወር አለበት ነው የሚሉት። የራያ ጀግኖች ለወራት በራሳቸው ትጥቅ፣ በራሳቸው ስንቅ ነበር ጠላትን ረፍት የነሱት። ራያዎች ጠላት ሲመጣ ሚስትህ ከቤት እንድትተኛ አትፈቅድም ተነስ፣ ተታኮስ፣ ጠላትህን መልስ ትልሃለች ይላሉ። እልል እያለች ታዋጋለች፣ ልጇንም ሂድና በጀግንነት ተዋደቅ ብላ ትልካለች። ፈርቶ የሚኖር፣ ሸሽቶ የሚያድር አይገኝም በራያ ምድር።

የራያ ሕዝባዊ ሠራዊት ሚሊሻ የፖለቲካ ጉዳይ መሪው ሞገስ አማረ የራያ ጀግኖች ውስጥ ለውስጥ በመገናኘት እና በማስተባበር ጠላትን ማጥቃታቸውን ነግረውናል። የመጀመሪያው ሥራቸው መዋጋት የማይችለው ጠላትን እንዲያኮርፍ፣ አቅም ያለው ደግሞ የሽምቅ ውጊያውን እንዲቀላቀል ማድረጋቸውን ነው የነገሩን። እነዚህ ጀግኖች ውይይት በማድረግ ጠላትን በሚመቻቸው ቦታ እየተዘዋወሩ ያጠቁት ጀመር። የጠላትን ንብረቱን እያወደሙ፣ እዙን እያፈረሱ ማሰቃየቱን ተያያዙት። በጀግንነት እያጠቁ፣ ጠላትን እየለበለቡ ቆቦንም ይቆጣጠሩ ነበር። ተተኳሽ ይዘው ዳግም ያጠቃሉ፣ እስኪበቃቸው ጠላትን ይደመስሳሉ፣ በፍርሃት እንዲኖር፣ ስንቅና ትጥቅ እንዳይኖረው ያደርጋሉ። ጠላት አልችላቸው ሲል ከባድ መሳሪያ ይተኩስባቸው ነበር ራያዎች ግን ፍንክች አይሉም። በጀግንነት ይዋጉታል። ከባድ መሳሪያ የያዘውን በክላሽ ያቀምሱታል።

ማጥቃት ባደረጉ ቁጥር ጠላት አስከሬን እየጎተተ ሲሄድ እነርሱ ግን በጀግንነት ድል አድርገው ይመለሳሉ። የዘረፈውን ይዞ እንዳይወጣ ይገድቡታል። ጠላት በሌሊት እንዳይጓዝ አደረጉት። በጀግንነት ያቀምሱት ነበር። አባቶቻችን ለጠላት አይበገሩም፣ ሚስቴን ርስቴን አሳልፌ አልሰጥም እያሉ በጀግንነት ኖረዋል የሚሉት ሞገስ የእነዚያ ጀግኖች ልጆች ዛሬም በድል ተወጥተዋል ነው ያሉት። ራያ ውስጥ ጠላት ያቀደውን እንዳያደርግ ማድረጋቸውንም ገልፀዋል።

የራያ አርሶ አደር ጠላትን ድባቅ የሚመታ ጀግና እንደሆነም ነግረውናል ። በቅንጅት፣ በአንድነት ፣ የበቆሎ ንፍሮ እየበሉ ወራትን በጦርነት አሳለፉ፣ በጀግንነትም ትግላቸውን ፈፀሙ። በድል አጠናቀቁ። መሪና ተመሪ ተግባብተው መሥራታቸው ለድሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበርም ገልፀዋል። የራያ ጀግኖች ከመዋጋት ባለፈ የጠላትን እንቅስቃሴ ጠልቀው እየገቡ ለመከላከያ ሠራዊት መረጃ ይሰጡ ነበር፣ እነርሱ በሰጡት መረጃ መሰረትም ጠላት ድባቅ ይመታ ነበር።

የራያ ጀግኖች ትግላችንም ድላችንም አላለቀም ፣ ጠላትን እስከመጨረሻው ሳንደመስስ አናርፍምም ነው ያሉት። የራያ ጀግኖች በመገናኛ ሬዲዮ የሚመራውን ጠላት በባሕላዊ መንገድ እየተግባቡ ነበር ድባቅ የመቱት። ማኅበረሰቡ ጠላት መረጃ እንዳያገኝ ከማድረግ ጀምሮ በእጃቸው እየፈጩ ምግብ ያቀርቡላቸው እንደነበርም ነግረውናል። ውጊያ ሲደረግ እሰይ ልጄ እያሉ ምሽግ ድረስ እያጎረሱ ያዋጉ እንደነበርም ገልፀዋል ። ጠላት በራያ ጀግኖች መመታቱ ሲመረው የተዋለድን፣ የተዛመድን ሰዎች ነን እባካችሁ ተውን እያለ ምልጃ ይልክ እንደነበርም ሞገስ ያስታውሳሉ። ጠላት ከፊት እየተመታ ሲሸሽም የራያ ጀግኖች መንገድ ላይ እየጠበቁ ይደመስሱት እንደነበርም ገልፀዋል።

የራያ ሚሊሻ የሻምበል መሪ አድማሱ ይመር ሴቶች ለጠላት ምግብ እንዳይሰጡ፣ ወንዶች እንዴት ዋላችሁ ሲሏቸው መልስ እንዳይሰጡ በማድረግ ትግላቸውን መጀመራቸውን ነው የነገሩን። ከጀግኖቹ ጋር እየመከሩና እየዘከሩ ጠላትን ድባቅ ይመቱ እንደነበርም ነግረውናል። ጠላት ሲሸሽ በኮምቦይ ታጅቦ እንዳይሄድ እያደረጉ ይደመስሱት እንደነበርም ነግረውናል። አሁን ላይ በጀግንነት በመጣው ድል መደሰታቸውንም ገልፀዋል። ሕዝብ የሚያጠፋን ጠላት በአንድነት ማጥፋት እንደሚገባም ተናግረዋል። ተዘጋጅቶ መጠበቅ ካልተቻለ የአባቶቻችንን ታሪክ እናበላሻለን ነው ያሉት።

የራያ ጀግንነት ከአባት የተወረሰ፣ ከልጅ ልጅ እየተቀባበለ ከዚህ የደረሰ መሆኑንም ነግረውናል። የትግራይ ወራሪና አሸባሪ ጠላት እያለ ከምሽግ አንወጣም ፣ በጀመርንበት መንገድ እናጠፋቸዋለንም ብለዋል።

ሌላኛው የሻምበል መሪ ሲሳይ ደሳለው ጀግኖችን በማደራጀት ከጠላት ጋር መፋለማቸውንና ጠላትን መምታታቸውን ነው የገለፁልን። ጠላት በሕዝብ ላይ ያደረሰው ግፍ እምብኝ ብለው እንዲወጡ እንዳደረጋቸውም ነግረውናል። ራያ በጠላት አይነካም በማለት ሸፍተው መውጣታቸውን እና ጠላትንም ድባቅ መምታታቸውንም ገልፀዋል። ልባችን የሞላ ነው፣ ሞት አንፈራም ፣ ቁም ተብሎ የማይቆም፣ የጠላትን አንገት ለማነቅ የሚሮጥ ጀግና ሞልቷልም ነው ያሉት። ጠላት ከጥቃት ለማምለጥ ጊዜና ቦታ እየመረጠ ቢሸሽም ከራያዎች ጥቃት አለማምለጡንም ነግረውናል።

የራያ ጀግኖች ትግል እንደማይቆምም ነግረውኛል። በጀግኖች ወኔና ኩራት ተደምሜያለሁ። አንነካም ባይነታቸው ፣ ጀግንነታቸው ፣ አንድነታቸው፣ ግርማ ሞገሳቸው የሚደነቅ ነው። ጠላትን ለማድቀቅ እንደተዘጋጀ አንበሳ በኩራት እየተንጎማለሉ ጠላትን #ለማጥፋት በኩራት ቆመዋል። አዳርና ውሏቸውን በምሽግ አድርገዋል። ጠላትን ጨርሰው ሊደመስሱ ቃል ኪዳን አሥረዋል።

በታርቆ ክንዴ

#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous article“እናቱን የበላውን ከሃዲ ቡድን ጨርሶ መቅበር ይገባል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ጀግኖች
Next articleአካባቢያቸውን በጠላት ላለማስደፈር በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኙ በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙ የወገን ጦር አባላት ገለጹ።