በአሸባሪው ትህነግ የወደመው የአለውሃ ድልድይ የግንባታ ሥራ ተጀመረ።

341

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን የጥፋት ተግባር ተሰብሮ የነበረውን የአለውሃ ድልድይ የጥገና ስራ ተጀምሯል። የጥገናው ስራ ከስምንት እስከ አስር ቀናት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ለትራፊክ ክፍት እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡

የድልድዩ ፕሮጀክት ሳይት መሃንዲስ ኢንጂነር ዮሐንስ አያሌው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን እንደተናገሩት፤ የተሰበረውን ድልድይ ወደስራ ለማስገባት የብረት ድልድይ ለማስቀመጥ የሚያስችለው የግንባታ ስራ ተጠናቅቋል፡፡ ከነገ ጀምሮ ባሉት ቀናት ደግሞ ድልድዩን የመገጣጠምና የማጠናቀቅ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡

እንደ ፕሮጀክት መሐንዲሱ ኢንጂነት ዮሐንስ ገለጻ፣ የብረት ድልድዩ አጠቃላይ ርዝመቱ 54 ነጥብ 86 ሜትር ነው። የድልድዩ መቀመጫ (ፓድ) ተሰርቶ ተጠናቅቋል፡፡ ቀጣዩ ሥራ ብረቶቹን መገጣጠምና ማስቀመጥ ነው ብለዋል። የብረት ድልድዩን የመገጣጠም ስራ ከአምስት እስከ ሰባት ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን ከስምንት እስከ አስር ቀናት ውስጥ የድልድይ ሥራው ተጠናቅቆ ለትራፊክ ክፍት ይሆናል፡፡

የሚሰራው የብረት ድልድይ እስከ 600 ኩንታል ወይም 60 ቶን ድረስ መሸከም የሚችል አቅም ያለው ነው፡፡ የአገልግሎት ጊዜውን በተመለከተም ማስቀመጫውን(ፓዱን) መቀየር ካልሆነ በስተቀር ለረዥም ጊዜ ማገልገል የሚችል ነው፡፡

በመሆኑም ድልድዩ ሲጠናቀቅ ያለምንም የትራፊክ መስተጓጎል እስከ 600 ኩንታል እንዲያልፍበት ተደርጎ የተሰራ፤ ከወልዲያ እስከ ቆቦም ሆነ ከዚያ በኋላ የሚኖረው ጉዞ ያለምንም መስተጓጎል የሚካሄድ ይሆናል፡፡ ድልድዩም በፊት ከነበረው ድልድይ ምንም የተለየ ነገር የለውም፡፡

ከአለውሃ ድልድይ በተጓዳኝ ሌሎች በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸው ድልድዮች መሰል ሥራ እየተከናወነላቸው መሆኑን የጠቆሙት ኢንጂነር ዮሐንስ ከደሴ እስከ ዋጃ ባለው መስመር ብቻ ሁለት ድልድዮች ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደመሆኑ ከአለውሃ ድልድይ በተጓዳኝ ውጫሌ መግቢያ ላይ ያለን ካልቨርት ድልድይ ለመጠገን የሚያስችል ቁሳቁስ መቅረቡን እና ይሄም ከነገ ጀምሮ ወደስራ የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ከወልዲያ መገንጠያ ወደ ጭፍራ ጅቡቲ የሚወስደው መንገድ ላይ ድሬ ሮቃ አከባቢ ያለውን ትልቅ ድልድይ ለመስራት የሚያስችል የሰርቬየንግ አማራጮችን በመውሰድ ለድልድዩ ሊሆን የሚችለውን ስራ በመምረጥ ላይ መኮኑን በመጠቆም፤ ይህ ድልድይ ትልቅ እና በሸለቆ ውስጥ ያለ እንደመሆኑ ስራው በጥንቃቄ ሊሰራ እንደሚገባው እና እስከዛው ድረስ አማራጭ/ተለዋጭ መንገድ ተበጅቶ ተሽከርካሪዎች እንዲተላለፉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ባለስልጣኑ በአሸባሪው ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን መንገዶችና ድልድዮች ጠግኖና ገንብቶ ወደስራ ከማስገባት አኳያ በትኩረት እየሰራ መሆኑን እና በሁሉም ሳይቶች ወደስራ መገባቱን ነው ኢንጂነር ዮሐንስ የተናገሩት፡፡

አሸባሪው ትህነግ ከአማራ እና አፋር ክልሎች በወረራ ከያዛቸው አከባቢዎች አከርካሪውን ተመትቶ ወደኋላ ሲፈረጥት መንገዶችንና ድልድዮችን አውድሟል። የአለውሃ ድልድይም ከወልዲያ ተመትቶ ሲፈረጥጥ በፈንጅና በከባድ መሳሪያ አፍርሶት መሄዱ ይታወሳል። ዘገባው የኢፕድ ነው

#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous articleአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት ካደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 11ዱ ሥራ ጀመሩ።
Next article“እናቱን የበላውን ከሃዲ ቡድን ጨርሶ መቅበር ይገባል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ጀግኖች