
ታኅሣሥ 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በጦርነትና በግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የ 5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መዘጋጀቱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ገለጹ፡፡
በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራው የመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ታኅሣሥ 15/2014 ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ የመጀመሪያውን ውይይት አድርጓል።
በዚሁ ወቅት አቶ አሕመድ እንደገለጹት በገንዘብ ሚኒስቴር የተዘጋጀው የ 5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል። ተጨማሪውን በጀት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳጸደቀው በቀጥታ ወደ ሥራ ይገባል።
መንግሥት ከሚመድበው መነሻ በጀት በተጨማሪም ከልማት አጋሮች በተለይም ከዓለም ባንክ ለመልሶ ማቋቋሙ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ የመልሶ ማቋቋሙ መርኃግብሩ በመንግሥት የሚመራ፣ የተቀናጀ፣ በየደረጃው በፕሮግራም ተግባራዊ የሚደረግ፣ ተጠያቂነት ያለውና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚተጋ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በጦርነቱና በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት ለማውቅና በገንዘብ ለመተመን የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል የመነሻ ሐሳብ በገንዘብ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ለመልሶ ማቋቋም ሴክሬታያት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የቀረበ መሆኑን ተገልጿል።
የኮሚቴ አባላትም የመልሶ ማቋቋም መርኃግብሩ ከሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎች በተጨማሪ በሌሎች ክልሎች በግጭት የተፈናቀሉትንም እንዲያካትት፣ የሀብት አሰባሰብ ድግግሞሽ እንዲወገድና በአንድ ቋት እንዲሰባሰብ፣ ክልሎች ንቁ ተሳትፎ የሚደርጉቡት ምቹ ሁኔታ እንዲመቻች፣ ከሌሎች መሰል ብሔራዊ ኮሚቴዎች ጋር በቅንጅት እንዲሠራና የግሉን ዘርፍና ዲያስፖራውን እንዲያሳትፉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በውይይቱ የመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት የትምህርት፣ የጤና፣ የፕላንና ልማት፣ የውኃና ኢነርጂ፣ የኢንዱስትሪ፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ የሥራና ክህሎት፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መሥሪያ ቤት አመራሮች መገኘታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
