የሰሊጥ ምርቱ ጉዳት ሳይደርስበት እየተሰበሰበ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

298

ባሕር ዳር፡ መስከረም 25/2012 ዓ/ም (አብመድ) በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ሠላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን እና የሰሊጥ ሰብል በጥሩ ሁኔታ እየተሰበሰበ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ አስታውቀዋል። በተለይም ሰብሉ ቀድሞ በደረሰባቸው ምዕራብ አርማጭሆ እና ቋራ ወረዳዎች አካባቢ በቂ ሠራተኛ መግባቱን ተከትሎ ሰብሉ በተገቢው መንገድ እየተሰበሰበ እንደሚገኝ ዋና አስተዳዳሪው ለአብመድ ተናግረዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ205 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኢንቨስትመንት የተሸፈነ የሰሊጥ ሰብል ይገኛል። ከዚህ ውስጥ ወደ 100 ሺህ ሄክታር የሚጠጋው ተሰብስቧል። ከ270 ሺህ በላይ ሠራተኞች ደግሞ በሰሊጥ ሰብል ስብሰባ ሥራ ተሰማርተው እየሠሩ እንደሚገኙ ታውቋል። የዞኑ ከተማ ወጣቶችም በሰብል ስብሰባ ሥራው ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ አቶ አደባባይ አስታውቀዋል።

ምንም እንኳን የደረሰው ሰብል ጉዳት ሳይደርስበት እየተሰበሰበ ቢሆንም ተጨማሪ ሠራተኛ ወደ አካባቢው ቢመጣ የበለጠ ጉልበት እንደሚሆንም ተናግረዋል። እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ ለሰሊጥ ምርት አጨዳው ከ100 ሺህ በላይ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ። በተለይም ሰፊ ኢንቨስትመንት ባለበት ደለሎ አካባቢ የሰሊጥ ሰብሉ እየደረሰ ስለሆነ ጉዳት ሳይደርስበት ለመሰብሰብ ተጨማሪ የሰው ኃይል ለማስገባት እንደሚሠራም አስታውቀዋል። የዞን አስተዳደሩ ሠራተኞችን አጅቦ ወደ እርሻ ቦታው ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከመስከረም 27 እስከ ጥቅምት 1/2012 ዓ.ም ድረስ ተማሪዎች ሰበል በመሰብሰብ ወላጆቻቸውን እንዲያግዙ በማሰብ ለተማሪዎች እረፍት እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleበነዳጅ ማመላለሻ ቦቴ ተጭኖ የነበረ ከ2 ሺህ 200 በላይ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች እና አሽከርካሪው ጎንደር ከተማ ላይ ዛሬ ማምሻውን በቁጥጥር ስር ውለዋል።
Next articleሰብዓዊነት እንዲህ ነው!