
ታኅሣሥ 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) “የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ የሕይወት መስዋእትነት ለከፈሉ ጀግና ወገኖች ምስጋና ልናቀርብ ይገባል” ሲሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ የተባበረ የዳያስፖራ ጥምረት ‘የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ የሀገር ቤት የጉዞ ጥሪ’ እና የጥምረቱ ምስረታ አስመልክቶ ያዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ትናንት ተካሂዷል።
ዳያስፖራው ወደ ሀገር ቤት የሚያደርገው ጉዞ የምስጋና ጉዞ መሆኑን አምባሳደር ታዬ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ የሕይወት መስዋእትነት ለከፈሉ ወገኖች ምስጋና ልናቀርብ ይገባል፤ ጀግኖችን ማበረታትና ማድነቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
“ጀግኖች ስቃይና መከራን ተሸክመው የመጣባቸውን መዓት ተቋቁመው ሕይወታቸውን ገብረው ሀገር አልባ ከመባል አድነውናል” ያሉት አምባሳደሩ፥ እነዚህ ጀግና ወገኖች ምስጋና እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
የዳያስፖራው የሀገር ቤት ጉዞ የተስፋ ጉዞ እንደሆነና ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ የሕልውና ዘብ መሆናቸውን ለዓለም የሚታይበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል።
“ጉዞው ለኢትዮጵያ መድኅንና ጽናት የሚደረግ ነው፤ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ የሚደረግ ጉዞ ነው” ብለዋል አምባሳደር ታዬ።
የዳያስፖራው ጉዞ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና ለሚያደርጉና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሳይታክቱ ለሚሠሩ ኃይሎች ትልቅ ፖለቲካዊ መልዕክት እንዳለው አመልክተዋል።
የምንሄደው ተስፋና እውነት ወዳላት ኢትዮጵያና ሐቀኛ ወደ ኾነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ ለዓለምም ኢትዮጵያ በችግር ጊዜ ጸንታ የምትቆምና የምትቀጥል ሀገር መሆኗም በተግባር እናሳያለን ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ሲፈልጉ የሚሠሯት ሲፈልጉ የሚጠግኗት የሚፈልጉትን የሚግቷት አይደለችም፤ የእኛ ኢትዮጵያ ክብራችንንና ሉዓላዊነታቸውን አስከብራ ቆይታለች አሁንም አስከብራ ትቀጥላለች” ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዚህ ጉዞ በመሳተፍ በኢትዮጵያ ጉዳይ የማንደራደር መሆናችንን ማሳየት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ይህ ጉዞ የመዳን ጉዞ ነው ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ አሁን ቁስሉ የሚሸርበትና የሚድነበት ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያዊነት ትዕግስት አርቆ አሳቢነት ጽናትን የተላበሰ ማንነት ነው፤ የኢትዮጵያዊነት የአፍታ ደስታ የቅጽበት ጊዜ ትካዜ አይደለም” ብለዋል አምባሳደሩ።
የኢትዮጵያ ጽናት የሚመነጨው ከኢትዮጵያውያን ሰላም ወዳድነት እንደሆነና አለመግባባቶችን በመነጋገርና በመወያየት ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከፉክክር ይልቅ ትብብር ከመገፋፋት ይልቅ መተባበር ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደር ታዬ ከተባበርን እንድናለን ከተከፋፈልን እንወድቃለን ብለዋል።
ደጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚታወቀው ትህትናውና እንግዳ አቀባበሉ ዳያስፖራውን እንደሚያስተናግድ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ ኑ ሀገራችሁን ታደጓት” ሲሉ አምባሳደር ታዬ ጥሪያቸውን ማቅረባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
