አሻጋሪው አባት ብፁዕ አቡነ በርናባስ

610

ታኅሣሥ 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን ከሚታወቁበት እሴት አንዱ በችግር ወቅት በመረዳዳት ችግርን መሻገር ነው። የኢትዮጵያዊያን የመረዳዳት እሴት ከግብረ ገባዊነት ባለፈ በሃይማኖታዊ አስተምሕሮውም ትልቅ ቦታ አለው። የመረዳዳት እሴት ሃይማኖታዊ ቦታው ምን ያክል መንፈሳዊ ዋጋ እንዳለው ለማመላከትም “በሃይማኖት ለሚመስሏቹህ ብዙ ብታደርጉም ማንኛውንም ሰው ግን መርዳት ይገባል” ሲል ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚያስተምር የዋግኽምራ እና የምዕራብ ካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ ነግረውናል።

ብፁዕ አቡነ በርናባስ በሰቆጣ ከተማ አስተዳደር በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ችግር ውስጥ የወደቁ ወገኖችን ሕይወት ለመታደግ ያደረጉት አባታዊ ኃላፊነት ተወጥተዋል። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ዋግን በወረረበት ወቅት አቡነ በርናባስ አዲስ አበባ ነበሩ። በወቅቱ የሽብር ቡድኑን ወረራ እንደሰሙ ግን ሽሽትን አልመረጡም፤ ይልቁንም በማኅበረሰቡ ላይ የሚደርሰውን ችግር ኹሉ ለመጋፈጥ ወዲያውኑ ሰቆጣ ገብተው ከሚወዱት ሕዝብ ጋር ተቀላቀሉ እንጂ።

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በዋግኽምራ በፈጸመው ወረራ ሀብትና ንብረት በመዘረፉና የንግድ እንቅስቃሴ በመቆሙ ማኅበረሰቡ ለከፍተኛ ርሀብ ተጋለጠ። በተለይም ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙት የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕይወት አደጋ ላይ ወደቀ። አቡነ በርናባስ ይህ ችግር እንደተከሰተ ከቤተክርስቲያኗ አባቶች ጋር መመካከር ጀመሩ። የመፍትሔ ሐሳብም አስቀመጡ፤ በውጭ ሀገር እና ከሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ያን በሰላሙ ጊዜ ቡራኬ የሰጡትን ሕዝብ ድጋፍ ጠየቁ። ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ በቤተክርሲያኗ ሥም ገቢ ተሰበሰበ። ይሁን እንጂ በወቅቱ የባንክ አገልግሎት በመቋረጡ የተላከውን ገንዘብ በቀላሉ መጠቀም አልተቻለም። ቤተ ክርስቲያኗ ግን ሌላ ዘዴ ዘየደች፤ በተላከው ገንዘብ መጠን ልክ ከባለሀብቶች በመበደር የእህል ግዥ በመፈጸም እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ደግሞ በማሰባሰብ ድጋፍ ተደርጓል። የተሠበሰበው ገንዘብ ለመንግሥት ሠራተኛው በብድር፣ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ በቀጥታ ድጋፍ መደረጉንም ነግረውናል።

ብፁዕነታቸው እንዳሉት ቤተ ክርስቲያኗ 30ዐ ሰዎችን ለማገዝ ብትነሳም የችግሩ መጠን እየሰፋ በመሄዱ ከ2 ሺህ በላይ አባዎራዎችን፣ በቤተሰብ ደረጃ ደግሞ ከ10 ሺህ 100 በላይ ሰዎችን በመርዳት በርሃብ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን እልቂት መቅረፍ ተችሏል። የተፈጠረውን ችግርም “ያለፉት አራት ወራት ብዙ ሐዘን፣ ጥቂት ደስታ ያየኹበት ወቅት ነው። የደረሰው ድብደባ፣ ስደት፣ ሞት በሕይወት ዘመኔ ያየኹት ከባድ ሐዘን ሲኾን የሚያጠቡ እና ነፍሰ ጡር እናቶችን እንዲኹም የተቸገሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መታደግ መቻሉ ደግሞ ጥቂት ደስታ ያየኹበት ነው” ብለዋል አቡነ በርናባስ።

መረዳዳት እና መተሳሰብ ካለ የማይታለፍ ችግር አለመኖሩን ከባለፉት ወራት በተግባር የታየበት ወቅት መኾኑን ያወሱት አቡነ በርናባስ ኢትዮጵያውያን የቆየ የመረዳዳት እና የሥራ ባሕላችንን በማጎልበት የቀደመ ገናናነታችንን የምንመልስበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው የከተማዋ ነዎሪዎች መካከል ወይዘሮ ፀጋ ገብሩ በወቅቱ ችግር ውስጥ ከወደቁት ነዋሪዎች አንዷ ናቸው። ወይዘሮ ፀጋ ለእናት ሀገሩ ዘብ ከቆመ ጀግና ወታደር ሦስት ልጆችን አፍርተዋል። ካሁን ቀደም አሸባሪው ቡድን በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ በፈጸመው ጥቃት ምክንያት ከአዲግራት ተፈናቅለው ኑሯቸውን ከልጆቻቸው ጋር በሰቆጣ አድርገዋል። የሽብር ቡድኑ ሰቆጣን ሲወር ባለቤታቸው ለቤተሰቡ በባንክ የሚልኩት ገንዘብ ተቋረጠ፡፡ ይህም ችግር ውስጥ እንዲገቡ አደረጋቸው፡፡ ወደ ጎረቤት እንዳይጠጉም የአካባቢው ማኅበረሰብ የእርሳቸው እጣ ፈንታ ገጥሞታል። የእርሳቸውንና የልጆቻቸውን ሕይዎት ለማትረፍም ብቸኛው አማራጭ ወደ አቡነ በርናባስ መሄድ ነበር። ብፁዕ አቡነ በርናባስ የወይዘሮ ፀጋን ጥያቄ ተቀብለው ድጋፍ በማድረግ የእርሳቸውን ጨምሮ የልጆቻቸውን ሕይወት መታደግ መቻላቸውን ወይዘሮዋ ነግረውናል።

አቶ አደም ኑር እንዳሉት ደግሞ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን አካባቢውን ከወረረ ጀምሮ ንብረት በመዘረፉ እና እንቅስቃሴ በመቆሙ ባላቸው ጥሪት ልጆቻቸውን እና የሚደግፏቸውን ወላጆቻቸውን መምራት ተሳናቸው። ችግሩም እየተባባሰ በመሔዱ መፍትሔው ያለው ከሌለው መረዳዳት ነውና እሳቸውም ቤተክርስቲያኗ ካሰባሰበችው ሀብት ተካፋይ እንደኾኑ ነግረውናል። በወቅቱም በማኅበረሰቡ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመሻገር ዘርና ሃይማኖትን ሳይለይ ሰው በሰውነቱ ድጋፍ እንደተደረገለት ነግረውናል።

ብፁዕ አቡነ በርናባስ ያከናወኑት ሥራ ሕዝብን ከርሀብ መታደግ ብቻ አልነበረም። የሽብር ቡድኑ በሕዝቡ ላይ ያደርስ የነበረውን ግድያ፣ ድብደባ፣ የንብረት ማውደም እና ዘረፋን ለማስቆም ግንባራቸውን ለጥይት ሰጥተው ፊት ለፊት ተጋፍጠዋል።

ለሽብር ቡድኑ ዕብሪተኞችም መጨረሻቸው ውድቀት መኾኑን በመግለጽ ይህንን ሰይጣናዊ ተግባራቸውን እንዲያቆሙ በይፋ ተናግረዋል።

ብፁዕ አቡነ በርናባስ በአባታዊ ተግባራቸው የብዙ ሰዎችን ሕይወት በመታደግ ክፉ ወቅትን አሻግረዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

Previous article“መገን የራያ ልጅ መገን ጉራ ወርቄ የጀግኖቹ ቦታ ተመልከት እያለ ሠላሳ ተኮሶ ሠላሳ ሚመታ “
Next articleሕዝቡ ከሐዘን ወጥቶ ለትውልድ የሚተርፍ የጀግንነት ሥራ እንዲከውን ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አሳሰቡ።