
ታኅሣሥ 17/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ማጌጫቸው መውዜር፣ መጠጣቸው ወተትና ማር የሆነ፣ ትጥቃቸው የማይላላ፣ ዝናር ከወገባቸው፣ ጠመንጃ ከትክሻቸው የማይለያቸው፣ ፍቅርና ደግነት ፣ አልሞ መምታትና ጀግንነት የማይለያቸው ጀግኖች። በጀግኖቹ ጎራ ተኩሶ መሳት አይታወቅም። አፈሙዝ ከዞረ፣ ጀግናው ካነጣጠረ በኋላ ነገር አለቀ። ከአንገት በላይ ለይቶ ይቀነጥሳል፣ ግንባር መርጦ ይበሳል። ለሚወዱት ጮማ ይቆርጣሉ፣ ጤፍ እንጀራ በእርጎ ያቀርባሉ፣ ፍርንዱስ ያወርዳሉ፣ ጠጅ ይጥላሉ፣ ጠላ ይጠምቃሉ። በልቶ የጠገበ አይመስላቸውም። በእነርሱ መንደር ጎራ ያለ ሁሉ ያቀማጥሉታል። ከጠሉት ደግሞ ጮማ በቆረጠ እጃቸው መውዜራቸውን አንስተው ይመቱታል። በአፍ ጢሙ ይደፉታል። በአፈቀረ ልባቸው አምርረው ይጥሉታል።
“ይምጣ የራያ ልጅ ፊት ፊት እየመራ
ጀግና የጀግና ዘር ሃሞተ መራራ” እንዳለ ዘፋኙ የራያ ልጅ ጀግና የጀግና ልጅ ነው። የራያ ልጅ ሃሞተ መራራ ነው። የራያ ልጅ ተፈትኖ በአሸናፊነት የወጣ ነው። የራያ ልጅ መራዥ ተኳሽ ነው። የራያ ልጅ ፍርሃት ያልፈጠረበት፣ ልቡን ያመነ ነው። ዝናር ከወገባቸው፣ መውዜር ከትክሻቸው፣ ጩቤ በሽንጣቸው ይዘው፣ ጎፈሬያቸውን ነቅሰው ሲራመዱ ልብን ያሞቃሉ። አጀብ ያሰኛሉ። ራያ ወተትና ማር የሚፈስስበት፣ ጀግና እንደ ቡቃያ የሚበቅልበት፣ ደግነት እና ፍቅር እንደ ወንዝ የሚፈስስበት ፣ የተራበ የሚጎርስበት፣ የተጠማ የሚጠጣበት፣ ያዘነ የሚረጋጋበት፣ የታረዘ የሚለብስበት፣ የመሸበት የሚያድርበት ሁሉም የሚገኝበት መልካም ምድር።
በራያ ምድር የተገኘ ሁሉ ምነው ከእናንተ ጋር ባይለየኝ ይላል። ፍቅራቸው ፣ ደግነታቸው ፣ ጀግንነታቸው ፣ ሀገር ወዳድነታቸው፣ ለዛቸው፣ ሥርዓታቸው፣ ሕግ አክባሪነታቸው ይገርማል። ራያ ለወዳጅ እንጂ ለጠላት አይመችም። በፍቅር እንጂ በጦር አይቻልም። ከወደደ ነብሱን ይሰጣል። ከጠላ በጥሶ ይጥላል። ራያን የሚያሸንፈው ፍቅር ብቻ ነው።
እኔም በአሻገር ከሚናፈቁት፣ በጀግንነት ከሚታወቁት ፣ ተኩሰው ከማይስቱት ራያዎች ጋር ነኝ። በፍቅራቸው ባሕር እየዋኘሁ፣ በጀግንነታቸው እየተደነቅኩ በራያ ቆላማ አካባቢዎች ጉራ ወርቄ ውስጥ ነኝ። ጉራ ወርቄ ስትነሳ ጀግንነት ፣ እንቢተኝነት ፣ አትንኩኝ ባይነት ፣ አሸናፊነት ትውስ ይላል።
የትግራይ ወራሪና አሸባሪ ቡድን ባደረሰው ወረራ እምብኝ ፣ አይደረገም ብለው አካባቢያቸውን ያላስደፈሩ ፣ በምሽግ ውለው በምሽግ እያደሩ ቀያቸውን ያስከበሩ ጀግኖች ናቸው። እነዚህ ጀግኖች ሕግ ያከብራሉ፣ ሕግ የሚጥስን ይቃወማሉ። መሪያቸውን ይሰማሉ፣ አጥብቀው ይወዳሉ። በአንድነት ይሠራሉ። ለዚያም ነው በአንድነታቸው ጠላት ያልደፈራቸው። በዚህ አካባቢ ሥማቸው ከፍ ብሎ የሚነሳ፣ ጀግኖች የሚወዷቸው፣ መሪያችን የሚሏቸው አንድ ብርቱ ጀግና አሉ። በወርቄዎች ዘንድ እጅግ ይወደዳሉ ፣ ይጅግ ይከበራሉ። ይሳሳላቸዋል። በእነዚያ የመከራ ቀናት፣ በእነዚያ ፈታኝ ሳምንታት ፣ በእነዚያ አስቸጋሪ ወራት ውስጥ በጀግንነት መርተው፣ በጀግንነት አዋግተው፣ በጀግንነት ተዋግተው፣ በጀግንነት አደራጅተው በአሸናፊነት ተወጥተው መልካም ጊዜ አምጥተዋልና በእጅጉ ይወደዳሉ። እሳቸው ሕዝባቸውንም አብዝተው ይወዳሉ። አብዝተው ያከብራሉ። ከልባቸው ያገለግላሉ። ወርቄዎች የእኛ የጦር ጄነራል ይሏቸዋል። ጦር መምራት መዋጋትና ማዋጋት ይችሉበታልና።
ለእናት ሀገራቸው፣ ለተከበረችው ሠንደቃቸው ሁሉንም ያደርጋሉ። ሳይሰስቱ ይሰጣሉ። ስናይፐራቸውን ይዘው፣ ሲንጎማለሉ ደስታን ይሰጣሉ። ልብን ያሞቃሉ። ወኔ ይጨምራሉ። ከጀግንነታቸው ጋር ፍቅር፣ ከድፍረታቸውና ከብልህነታቸው ጋር የሕዝብ ክብር አላቸው። በካሪስ ጎቤ ይባላሉ። እናትና እና አባቶቼ ስሜን በካሪስ ጊቤ ሽብሽ ብለው ነው ያወጡልኝ። አሁን ግን በካሪስ ወርቄ በሉኝ ይላሉ። የወርቄ ቀበሌ አስተዳዳሪ ናቸው። ጀግና ናቸው። መምራት ይችሉበታል። ስለዚያን ጊዜ ሲያስታውሱ “ጠላት እየወረረ ሲመጣ በፍፁም ወርቄን አይነካትም ብዬ ወሰንኩኝ። ሕዝቡም ተቀበለኝ። ወጣቱም ተደራጀ፣ ጠላት እስኪመጣ ብቻ ሳይሆን ከመምጣቱ በፊት እየሄደ ወጣቱ ይዋጋ ጀመር። ጠላት ውጊያ ከፈተብን። አሸንፈን መለስነው። ደጋግሞ ሞከረን በታላቅ ኪሣራ አሸንፈን መለስናቸው። ጠላት ከእኛ ጋር ሲገጥም ሬሳውን ሳያነሳ ነው የሚሄደው። ዓላማችንን ፈፅመናል” ነው ያሉት።
በካሪስ ጎቤ የሚመሩት ጦር ለቀናት ወይም ለሳምንት ብቻ አይደለም የተዋጋው። የተዋጋው ትጥቅ እንደፈለጉ በማይገኝበት፣ ቁስለኛ የሚያክም ሐኪም ባልነበረበት፣ ከጋራ ጋራ እየተሸጋገሩ ለወራት ነው የተዋጉት። ለጦርነት ተመቻችተው የተፈጠሩ በሚመስሉት የወርቄ ተራራዎች ጀግኖች እየተመላለሱ ጠላትን ድባቅ መቱት። በጀግንነት ክንዳቸውን አሳዩት። እኒያ ቆለኛ የራያ ጀግኖችን ማን ደፍሮ ይለፋቸው፣ አንጥረው እየተኮሱ አሰቃዩት። አንገቱን አሰደፉት፣ መንጋውን ጨረሱት።
“መገን የራያ ልጅ መገን ጉራ ወርቄ የጀግኖቹ ቦታ
ተመልከት እያለ ሠላሳ ተኮሶ ሠላሳ ሚመታ ” የወርቄ ጀግኖች ሠላሳ ተኩሰው ሠላሳ ነው የሚጥሉት። ጠይት በዋዛ አይተኮስም። ምላጭ ዝም ብሎ አይሳብም ነው የሚሉት። ከፈለጉት ቦታ ላይ ለይተው ይመታሉ እንጂ በወርቄዎች ዘንድ መሳት አይታሰብም። ተኩሶ መሳት የሚሆን አይደለም አነጣጥረው ይመታሉ። ተመልከት እያሉ ይነጥላሉ። የአንበሶች ትንፋሽ ማን ይነካቸውና። ለወራት የዘለቀው ጦርነት በእነ በካሪስ አሸናፊነት ተደመደመ። ጠላት ቆላማዋ ወርቄን ናፍቋት ቀረ። ብቅ ሲል በጥይት እየለቀሙ አልቀመስ አሉት። እነ በካሪስ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እየተናበቡ በጀግንነት ተዋጉት በጀግንነት አሸነፉት።

የወርቄዎች የጦር መሪ ስለ አሸነፉበት ምስጢር ሲናገሩ “ጠላትን ለማሸነፍ የቻልነው፣ ሜካናይዝድ የታጠቀውን የተቋቋምነው በአንድነታችን ነው። ሕዝባችን በሃይማኖት አልተከፋፈለም አንድ ነው። የፖለቲካ ልዩነት የለውም አንድ ነው። አንድነት ሲደመር የተኩስ ልምድ ጠላት እንዳይደፍረን አድርጎናል። በባሕላችን ወንድ አሥራ ሁለት አመት ከሆነው መሳሪያ ይይዛል። ተኩስ ይለምዳል። ያን ከአባቶቻችን ያገኘነውን ልምድ በማካበት የአባቶቻችን ፈለግ በመከተል ወጣቱ በአንድነት በመሰለፍ ጠላትን መደምሰስ ችለናል” ነው ያሉት። ጀግኖቹ ጠላት ሰላም እንዲያጣ በሽምቅ እየተዋጉ በራያ ምድር እየተመላለሱ መሳሪያውን ያቃጥሉበት፣ ተዋጊውን ይገድሉበት፣ ይማርኩበት እንደነበርም ነግረውናል። ጠላት በየቀኑ ብዙ የሚከዳ ታጣቂ ስለነበረው የሚከዳው ጦር መሳሪያ እና የተዘረፈ ንብረት ይዞ እንዳይሄድ ያደርጉት እንደነበርም አስታውሰዋል።
“የእኛ ቃለ መሓላችን አደረጃጀትን አጠንክረን ጠላትን እስከመጨረሻው መደምሰስ ” ነውም ብለውናል በካሪስ ጎቤ (በካሪስ ወርቄ)። እንኳን እነርሱ ግመሎቻቸውንም ጠላትን ለመምታት ዝግጁ እንዳደረጓቸው ነው የተናገሩት። ለተገኘው ድል የወርቄ እናቶች ጀብዱ ከፍተኛ እንደነበርም ነግረውናል። ሴቶች መረባ እያሉ ዱዓ እያደረጉ፣ ስንቅ እያቀበሉ፣ አይዞህ ግፋ በለው፣ በለው እያሉ ያዋጉ እንደነበርም ነግረውናል። እሰይ እንኳን ልጄ ለሀገር ሞተ እያሉ ያበረታቱ እንደነበርም በካሪስ የጀግና እናቶችን ታሪክ ያስታውሱታል።
በወርቄ ተራራዎች ለወራት በተደረጉት ውጊያዎች ዘመናዊ መገናኛዎች አልነበሩም። በአንደኛው ጋራ ያለውን ተዋጊ በሌላኛው ጋራ ያለውን ተዋጊ የሚያገናኙበት የመገናኛ ራዲዬ አልነበረም። እነ በካሪስ ግን አልተቸገሩም። ባሕላዊ ዘዴ ነበራቸውና። ጥበብ የእነርሱ ናትና። “ባሕላዊ ጥሩምባ አለን፣ መሪዎቹ ጥሩምባ ይይዛሉ። ጥሩንባው የሚነፋበት መንገድ አለ። ውጣ ወጥቻለሁ፣ ግፋ ፍጠን ጠላት ሊያመልጥህ ነው ፣ ወደ ቀኝ አዘንብል፣ ወደ ግራ ሁን፣ ተቀመጥ፣ ተነስ፣ ቦታ ያዝ ለሁሉም የመግባቢያ ምልክት አለ። በዚያ ምልክት እየተረባረብን እንዋጋለን” ነው ያሉት። የሚገርም ጥበብ ነው። ዘመናዊ መገናኛውን ቢያጡት በባሕላዊ ጥበብ ያን ቀን አለፉት።
ጠላት ድምጥማጡን እያጠፉ ሲያስቸግሩት በሽማግሌ እና በሃይማኖት አባት እንዲያሳልፉትም ጠይቋቸው ነበር። እነ በካሪስ ፈቃደኛ አልነበሩም። ጠላትን ፈፅሞ እንደማያሳልፉት፣ ቀያቸውንም እንደማያስደፍሩት ቃል ገብተዋልና። አይሆንም አሉት። አይሆንም ከማለት አልፈው ለሽምግልና የመጣውን ሰው ጠላት ነህ እያሉ በአካባቢው ሕግ መሠረት እየቀጡ መለሷቸው። የጠላትን ሐሳብ ይዞ የመጣው ተቀጥቶ ተመለሰ። በዚያው የጠላት ማተላያ መረቡ ተበጠሰ ነው ያሉት በካሪስ ጎቤ።
“ጠላት በገፋ ቁጥር የበለጠ ጠነከርን እንጂ ተስፋ አልቆጠርንም። ለምን ከተባለ አሥር ጥይት ካለን አሥር ጠላት ስለምንመታ። አንድም ጠላት አንስትም። ጥይት አግድሞ አይተኮስም። ጠላት ተኩስ አይችልም። የአማራን ያህል ውጊያ የሚችል የለም። ወላሂ በጨበጣ ውጊያ በክላሽ የተመታ ወገን የለንም። በጨበጣ ውጊያ ተኩሰው አይመቱም። በከባድ መሳሪያ የርቀት ተኩስ ካልሆነ በስተቀር በክላሽ ሰው አይመቱም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ ያለበት ጠላት ወኔ የሌለው መሆኑን ነው፣ ሲያጠብቋቸው አይችሉም። እያቀመስናቸው ስንሄድ ወርቄ መጣ ሲባል መሮጥ ነው የጀመረው” ነው ያሉን። ወርቄዎች ለወራት የተዋጉት ጠላትን የደመሰሱት ከጠላት እየማረኩ በማረኩት ጥይት ሳይስቱ እየመቱ ነው።
የወርቄ ጀግኖች በአንድነት በጀግንነት ቀያቸውን ሳያስደፍሩ አለፉት። በካሪስ በወርቄዎች ዘንድ አብዝተው ይወደዳሉ። የሚሉት ሁሉ ይተገባራል። እሳቸውም ሕዝብ የማይጠቅም ነገር አያመጡም። ለሕዝብ ፍቅር ለሕዝብ ክብር ሳይሰስቱ፣ ሳያመነቱ ይሠራሉ። ስናይፐራቸውን ይዘው ሲመላለሱ ወኔ ይሰጣሉ። ወርቄዎች ያከብሯቸዋል፣ ይወዷቸዋል፣ ከፍም ያደርጓቸዋል። እኔም በጀግንነታቸው ተደምሜያለሁ። በልበ ሙሉነታቸው ኮርቸባቸዋለሁ። የወርቄዎች የጦር መሪ በወርቄዎች የአጠራር የወርቄዎች ጄነራል በካሪስ መቼም ቢሆን ኢትዮጵያ እኛ እያለን አትደፈረም ብለዋል። ጀግና አካባቢውን አይለቅም። በጀግንነት ይዋጋል፣ በጀግንነት ጠላትን ይመታል፣ ከሞተም በተወለደበት ቀዬ ነው ብለውም ያምናሉ በካሪስ ጎቤ።
ለአሸናፊነት እንደ በካሪስ በብልሃት ፣ በጀግንነት በአርቆ አሳቢነት መምራት፣ ማዋጋት፣ መዋጋት። እንደ ወርቄዎች በአንድነት ፣ በጀግንነት በመደማመጥ ፣ በመከባበር መዋጋት ነው። ወርቄ በጠላት ያልተደፈረች የጀግናዎች ምድር። በካሪስ ስናይፐራቸውን ይዘው፣ ሠንደቃቸውን ለብሰው ለሌላ ድል ይገሰግሳሉ። ጀግኖቻቸውንም በጥበብ ይመራሉ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
