
ከ2 ሺህ 200 በላይ የጦር መሳሪያዎች እና ሲያጓጉዝ የነበረው አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ዋሉ።
በነዳጅ ማመላለሻ ቦቴ ተጭኖ የነበረ ከ2 ሺህ 200 በላይ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች እና አሽከርካሪው ጎንደር ከተማ ላይ ዛሬ ማምሻውን በቁጥጥር ስር ውለዋል።
አሽከርካሪው የጦር መሳሪያዎቹን በመጫን መነሻውን ከሱዳን አድርጎ ወደ ጎንደር ሲገባ እንደተያዘ ከስፍራው የሚገኙት ዘጋቢዎቻችን ያገኙት መረጃ ያመላክታል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በተደረገ ቆጠራ 2 ሺህ 221 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ፣ 34 ባለ ሁለት እግር ታጣፊ ክላሸንኮቭ፣ አንድ ባለ አንድ እግር ታጣፊ ክላሸንኮቭ፣ 35 ባለሰደፍ ክላሸንኮቭ እና አንድ ጄ ኤም-3 እንደተያዘ ታውቋል።
ቆጠራው አልተጠናቀቀም፤ ይህ መረጃ በተጠናቀረበት ሰዓት በድምሩ 2 ሺህ 221 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ እና 71 ክላሽ እንደተያዘ ተረጋግጧል።
አሽከርካሪውም በቁጥጥር ስር መዋሉን አብመድ ተመልክቷል።
የጦር መሳሪያዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ሰራተኞች እና በአማራ ክልል የሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ በጥምረት እንደሆነ ተገልጿል።
ኅብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ፣ ለፀጥታ አስጊ እና አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከትም ለፀጥታ ኃይሉ እንዲያሳውቅ የክልሉ የሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ጥሪ አቅርቧል።
ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ