በዲሽቃ ጠላትን ለቃሚው ጀግና!

552

ታኅሣሥ 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ምድሩ ጀግና አይታጠበትም፣ በረከት አይጠፋበትም፣ ፈሪና ጠላት ውሎ አያድርበትም፣ በየዘመናቱ ጀግኖች ይወለዳሉ፣ በጀግንነት ያድጋሉ፣ በጀግንነት ይኖራሉ፣ የጀግና ታሪክ ያወርሳሉ። እሳቶች ናቸው ያቃጥላሉ፣ ማዕበሎች ናቸው ያጥለቀልቃሉ፣ መብረቆች ናቸው ጠላት በቆመበት ሁሉ ያደርቃሉ፣ ተራራዎች ናቸው አይገፉም፣ የማይነቃነቁ አጥሮች ናቸው አይታለፉም።
የገባን ጠላት በገባበት መጨረስ፣ ለቃቅሞ መደምሰስ፣ ለልጅ አኩሪ ታሪክ ማውረስ ይችሉበታል። ግንባራቸው ከባድ ነው አይደፈርም፣ ጀግንነታቸው ኀይል ነው አይመረመርም፣ ልባቸው ሙሉ ነው አይጠረጠርም።
ኢትዮጵያ ጀግና ልጆችን መውለድ ታውቅበታለች፣ በእነርሱ ትኮራለች፣ በእነርሱ ትመካለች፣ ጀግና እየወለደች፣ የሚነኳትን እየቀጣች ያልተደፈረ ሀገር፣ ያልረከሰ መንደር ይዛ ዘመናትን ኖራለች። ዘመናትን ተሻግራለች። የአሸናፊነቷ ዘመን አይቋጭም፣ ዘለዓለም አሸናፊ ብቻ ናት። ማሸነፍ በእርሷ ያምራል። ድል አድራጊነት በእርሷ ይጠራል። ትውልድ ሁሉ በእርሷ ይኮራል። አሸናፊ ሁሉ በእርሷ ይኖራል። ጀግና የሚያፈልቀው ምንጯ አይደርቅም፣ ከከፍታው ላይ በክብር የተፃፈው ኀያል ስሟ አይፋቅም።
ጀግንነት በኢትዮጵያ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚፈስስ፣ ዘመናትን የሚያረሰርስ፣ የጠላትን ትብታብ ገመዶች የሚበጣጥስ፣ ጠላትን አፈር አድርጎ የሚደመስስ ነው። የትናንቶቹ ጀግኖች አያሌ የጀግንነት ሥራዎችን ሠርተው፣ የማትደፈር፣ የምትታፈር ሀገር አፅንተው ለዛሬዎቹ አስረክበዋል። የዛሬዎቹ ጀግኖች በተቀበሉት አደራ መሠረት በዘመናቸው የተነሳውን ጠላት እየደመሰሱ ለሚተካቸው ትውልድ ለማስረከብ ሀገራቸውን እየጠበቋት ነው።
ከዚህ ዘመን ጀግና ጋር ተገናኝቻለሁ። የአባቶችን አደራ ተቀብሎ፣ ሀገሬን በጠላት አላስደፍርም ብሎ ውሎና አዳሩ ምሽግ ላይ ነው። ስለ ኢትዮጵያ የተመቻቸ ሕይዎት ትቷል፣ የተደላደለ ኑሮ ረስቷል። ሕይዎቱም፣ ደስታውም እናት ሀገሩ የሚጣፍጥ ስም ያላት፣ ጀግንነት ያከበራት ኢትዮጵያ ናት። ስለ እርሷ ሁሉንም ያደርጋል። ሁሉንም ይሰጣል።
ዋና ሳጅን ጌታነህ ማሩ ይባላል። የአማራ ልዩ ኃይል አባል ነው። የዲሻቃውን አፈሙዝ ካዞረ ነገር ተከከተ ነው ይሉታል። እየመረጠ ይጥላል፣ እያነጠረ ይነጥላል፣ የሚልካቸው ጥይቶች ከጠላት ላይ እንጂ ስተው መሬት አይመቱም ይባልለታል። እርሱ በሚተኩስበት አቅጣጫ ያለ ጠላት ሁሉ አማራጩ የሚወድቅበትን ወረፋ መጠበቅ ብቻ ነው። ከእርሱ ዲሺቃ አምልጦ መሮጥ፣ ማምለጥም አይችልም። እጣው በዲሻቃ ጥይት እየተበሳ መውደቅ ነው።
ጓደኞቹ የክፍለ ጦሩ የጀርባ አጥንት ነው ይሉታል። በዲሽቃ ተኳሽነቱ ብቻ ሳይሆን በሥነ ምግባሩም የተመረጠ ተዋጊ መሆኑንም ይመሰክሩለታል። አዛዦቹ አድርግ የሚሉትን በመስማት፣ አድርግ ያሉትን በመፈፀም የተዋጣለት ጀግና ነው ሲሉ ያደንቁታል። በተሰለፈባቸው አውደ ውጊያዎች የጠላትን ድሽቃዎችና የአየር መቃወሚያ (ዙ) ከጥቅም ውጭ እንዳደረገም ነግረውኛል።

ልክ እንደ እርሱ ሁሉ በልዩ ኀይሉም ውስጥ ያልታወቁ ነገር ግን አያሌ ጀብዱዎችን የሠሩ ጀግኖች መኖራቸውንም ነግረውናል። እሱን መሰል ጀግኖች በርካቶች ናቸው። ጦሩ በጀግኖች የሞላ የጀግኖች ነውና። ሳጅን ጌታነህ የአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም የምትኮራበት ልጅ ነው ሲሉ ይመኩበታል። በአንድ አውደ ውጊያ ጌታነህና ጓደኞቹ በጠላት ከበባ ውስጥ ገብተው በራሱ ኀይል ጠላትን ሰብሮ መውጣቱንም ጓደኞቹ ነግረውኛል።
በሥሩ ያሉ ልጆችን በማብቃት አርዓያ የሆነ፣ ተወዳጅ ስለመሆኑም ይናገሩለታል። በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ 12 ዓመታትን ከ6 ወር በመቆዬት ኢትዮጵያን አገልግሏል። አሁን ክደው ኢትዮጵያን የሚወጓትን ጠላቶች በሚገባ ያውቃቸዋል። በሀገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጀኔራሎች በደሎችን ፈፅመውበታል። አምስት ጊዜ ሰላም አስከባሪ ተመልምሎ አትሄድም ብለው አስቀርተውታል። ከሚወደው ሙያም ወጣ።
ከመከላከያ ሰራዊት ከወጣ ከወራት በኋላ የአማራ ሕዝብ ሲበደል ስላየውና የአሸባሪው ቡድን አካሄድ ሕዝብን የሚያጠፋ መሆኑን አስቀድሞ ስለ ተረዳ ልዩ ኀይሉን ተቀላቀለ። አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በስሜን እዝ ላይ ጥቃት ሲያደርስ የእርሱ ጓደኞች የጥቃቱ ሰለባ ነበሩ። በዚያ ወቅት የእነርሱን በግፍ መገደል የሰማው ጌታነህ በጣም እንዳዘነ ተናግሯል። ጥቁር ማተቡን አውልቆ ነጭ ክር አስሮ እንደነበር አስረድቷል። “እንደ ቤተሰብ የምመለከታቸው ጓደኞቼ ሲሞቱ ስሜቴ ተጎዳ። ተቆጨሁም። አሁን ላይ ልጅህ ሞተች፣ እናትህ ታመመች፣ ብባል ይችን ሀገር ትቼ የመሄድ እቅድ የለኝም” ሲልም የሀገሩን፣ የጓደኞቹን እና የሕዝቡን ጠላቶች ሳያጠፋ የትም ንቅንቅ እንደማይል ነው የነገረን።
”በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ጀብዱዎችን ሠርተናል፣ ጠላትን ደምስሰናል፣ አንገቱንም አስደፍተናል”ነው ያለን ዋና ሳጅን ጌታነህ። ዲሽቃን በዲሽቃ፣ በዲሽቃ ዙ ማቃጠሉንም ነግሮናል። ዲሺቃ በዲሽቃ ውጊያ ከተደረገ በሚያስደንቅ ፍጥነት፣ በሚገርም የአተኳኮስ ስልት የጠላትን ዲሽቃ አመድ ያደርገዋል። የተሠራው ጀብዱ ለጦሩም ለክልሉም ኩራት ነው፣ እኔ ውስጤ ረክቷል ነው ያለው። በገቡበት አውደ ውጊያ በሲኖ አስከሬን አስጭነው እንደሰደዷቸውም ገልጿል።
በአውደ ውጊያ ማኅበረሰቡም ስንቅና ትጥቅ እያቀበለ አይዟችሁ እያለ ያዋጋቸው እንደነበርም ገልጿል። ከዚህ በኋላ በጭቆና የሚኖር የለም፣ ጠላትን ከምድረ ገፅ አጥፍተን፣ በሰላም የምናወራበትን ጊዜ እናመጣለን የሚለው የሳጅን ዓላማ ነው። “በፅናት የሚያዋጋን የአማራነት ስሜት ነው። ድሮ አባቶቻችን ያመጡትን ገድል እናስቀጥላለን። የአባቶቻችንን ውርስና ታሪክ ይዘን እናሸንፋለን። የአባቶቻችንን ታሪክ አሳልፈን አንሰጥም። ሀገራችን አስደፍረን አንሰጥም። የእነ አጤ ቴዎድሮስን ታሪክ እኛም እንወርሳለን” ብሎናል ሳጅን። እኛ ድሽቃን በድሽቃ እየመታን እያወደምን፣ ሬሳ በመኪና እንዲጭን አድርገነዋል ነው ያለው።
ከሁሉም የሚገርመው ሳጅን ጌታነህ አደረግነው እንጂ አደረኩት ብሎ አይናገርም። ጀግንነቱን እና ጀብዱን ሌሎች ይናገሩለት እንደሆነ እንጂ እርሱ እንዲህ አደረኩ ማለትን አይወድም። ጀግና ይሠራል እንጂ አይናገርም እንደሚባለው። “ስንዋጋ ሌሊቱን አጋምሰን። እኩለ ሌሊት ላይ በጠላት ከበባ ውስጥ ገባሁ። ወደታች መውጫዬን በዲሽቃ ዘግተውታል። ወደ ላይ ወጣን። ስንወጣ መንገድ ላይ ከጠላት ጋር ተገናኘን። በቀኝም በግራም በብሬን እና በስናይፐር ተከብቤያለሁ። በዚህ ጊዜ ጓደኛዬን ለጠላት እጄን አልሰጥም አልኩና ከጓደኛዬ ቦንብ ወስጄ ፈትቼ ያዝኳት። ሽጉጥም ነበረው። እርሱንም ወሰድኩ። ነገር ግን ነገሮችን ቀይረን። ሰብረን ከወገን ጦር ጋር ተገናኘን። ያን በማድረጌ ትልቅ ደስታና ኩራት ይሰማኛል፤ ለሠራዊቱም እንደዛው” ብሎናል። ያደረጋቸው ተጋድሎዎች እና ፈተናዎች የበለጠ እንዲጠነክርና ከድል ላይ ድል እየጨመረ እንዲሄድ አበረታቶታል። ‟እኔና ጓደኞቼ እያለን ሀገር አትፈርስም። ጠላትም ይጠፋል ነው ያለው። አንድነታችን አስቀጥለን፣ ሀገር እናጸናለን። የአማራ ሕዝብ ከጎናችን ነውም“ ብሏል።
እኛ በባሕላችን የተገኘውን እንስሳ እሳር አብልተን እናሳድጋለን፣ እነርሱ ግን በተቃራኒው የአማራን በሬዎች፣ ላሞች፣ ፍየሎችና በጎች፣ ፈረስና በቅሎዎች እየገደሉ ሄደዋል። ትንሿ የምትባለውን የደሮ ሀብት ሳይቀር ዘርፈው በልተዋል ነው ያለን፡፡
ሳጅን ጌታነህ ከዲሽቃዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው። እንከን ቢገጥማቸው ያስተካክላቸዋል። በውጊያ ሰዓትም እያነጣጠረ ይለቅምባቸዋል። ዲሽቃዎች ከእርሱ ጋር መሃላ የገጠሙ ይመስላሉ። እንደ ፈለገ ያዝዛቸዋል፣ ይታዘዙለታል። ይለቅምባቸዋል። ይለቅሙለታል። እርሱ ብቻ ሳይሆን ከእርሱ በታች ያሉትን ጓደኞቹን እያሰለጠነ መራዥ ተኳሽ አድርጓቸዋል። ጠላትን በዲሽቃ እየገረፈ አሰቃይቶታል። የዲሽቃ ድብደባውን የሚመክተው አይገኝም። እንደ ፈለገው ይለቅማቸዋል እንጂ።
በታርቆ ክንዴ
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!

Previous article“ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የምንመለከትበት መነጸር ሊቀየር ይገባል” ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
Next article“አነጣጥረው የማይስቱ ዓይኖች፣ የማይታክቱ እጆች”