“ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የምንመለከትበት መነጸር ሊቀየር ይገባል” ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

343

ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 16/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር “የሀሰት መረጃ በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ያሳደረው ጫና እና መፍትሔው” በሚል ርእስ ምክክር እያካሄደ ነው። በምክክር መድረኩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ባስተላለፉት መልዕክት በኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋለው የሀሰት መረጃ ዘመቻ ምንጩ ስህተት ሳይሆን የድርሰቱ አካል ነው ብለዋል።
በቲያትር ዓለም ተመልካች የሚመለከተው ደራሲው የፈለገውን እና ቀድሞ ያዘጋጀውን ድርሰት እንጂ ተመልካቹ የፈለገውን ሁነት አይደለም ያሉት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እያየነው ያለው የሀሰት መረጃ ዘመቻ በደራሲያኑ ፍላጎት የሚዘወር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሀሰት መረጃ ዘመቻው በስለላ ድርጅቶች፣ በእርዳታ ድርጅቶች፣ በብዙኀን መገናኛ ተቋማት እና በፖለቲከኞች የሚተወን ቲያትር ሲሆን ዓላማውም እርስ በእርሳችን ማባላት፣ ማጋጨት እና ሀገር አልባ ማድረግ ነው ብለዋል። ዲያቆን ዳንኤል ዘመቻውን ለመቀልበስ እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን እይታ እንዲቀይሩ ከመጠበቅ ይልቅ እኛ ኢትዮጵያዊያን ስለእነርሱ ያለንን እይታ ልንቀይር ይገባል ነው ያሉት።
“ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የምንመለከትበት መነጸር ሊቀየር ይገባል” ያሉት ዲያቆን ዳንኤል “ቢቢሲ“ የእንግሊዝ ሚዲያ እንጅ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አይደለም፣ ሲኤን ኤን የባለሀብት እና የንግድ ድርጅት እንጂ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አይደለም፤ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን እና ድርጅት የሚል የክብር ስም መሥጠት የለብንም ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን የውጭ ኀይሎች የቲያትር ድርሰት ተመልካቾች መሆናችንን ትተን የራሳችንን የቲያትር ድርሰት ፀሐፊዎች የምንሆንበት ታሪካዊ ወቅት ላይ ነንም ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
#ተነሳ!!
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
#አካባቢህን ጠብቅ!!

Previous articleበሰላም ወቅት በጠመኔ፣ በጦርነት ወቅት በጦር መሳሪያ
Next articleበዲሽቃ ጠላትን ለቃሚው ጀግና!